ክብረ በዓላት በመጽሐፍ ቅዱስ

timket

በዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ

የካቲት ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዓል ማለት ‹‹አብዐለ – አከበረ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ‹‹መታሰቢያ ማድረግ፣ ማክበር›› ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላታቸው ‹‹በዓል (ላት) በቁሙ፣ የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት የሚከበር፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፤ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት እና ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘፍንበት የሚዘምርበት፤ ዕልል የሚልበት፤ ሽብሸባ፣ ጭብጨባ የሚያደርግበት፤ ሲያረግድ እስክስታ ሲወርድ ባንገቱ የሚቀጭበት እንደ ጥጃ የሚፈነጭበት ነው›› በማለት የበዓልን ትርጕም ገልጸውታል፡፡ በአጠቃላይ በዓል ማለት ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ የሚል ትርጕም አለው፡፡

የበዓላት ዑደት

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ይህም ቀን መታሰቢያ ይኹናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፡፡ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ኾኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ፤›› በማለት በዓል ዘለዓለማዊ መታሰቢያ እንደ ኾነ ተናግሯል /ዘፀ.፲፪፥፲፬-፲፯፤ ዘሌ.፳፫፥፪-፬/፡፡ ስለዚህም በዓላት በዓመታት፣ በወራት እና በሳምንታት ዑደት እየተመላለሱ ይከበራሉ፡፡ በየዓመቱ ከምናከብራቸው መንፈሳውያን በዓላት መካከል በዓለ ልደት፣ በዓለ ጥምቀት፣ በዓለ ትንሣኤ ይጠቀሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የልደት በዓልን የምታከብረው ክርስቶስ በየዓመቱ የሚወለድ ኾኖ አይደለም፤ የልደቱን መታሰቢያ ለማሰብ ነው እንጂ፡፡ ጥምቀትን ስታከብርም የወንጌልን አስተምህሮ ተከትላ፣ ምሥጢር አስተካክላ፣ ወቅቱን ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ብላ ሰይማ የክርስቶስን መገለጥ በማስተማር በዓሉን ታስበዋለች፡፡ የጥምቀት በዓልን እኛ ምእመናን ስናከብርም ዅልጊዜ እንጠመቃለን ማለት አይደለም፤ በዓሉን የምናከብረው ክርስቶስ መጠመቁን ለመዘከር፤ ከበረከቱም ለመሳተፍ ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤን የምናከብረውም የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በማሰብ፣ የእኛንም ትንሣኤ ተስፋ በማድረግ ነው እንጂ ጌታችን በየዓመቱ ከሙታን ይነሣል በማለት አይደለም፡፡ ሌሎችን በዓላትም እንደዚሁ፡፡

በዓላትን በማክበራችን ምን ጥቅም እናገኛለን?

፩. በረከት

‹‹አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ዅሉ በእጅህም ሥራ ዅሉ ይባርክሃልና እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፤ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘዳ.፲፮፥፲፭/ በዓል ማክበር በረከትን ያሰጣል፡፡

፪. ፍጹም ደስታ

በዓል ስናከብር መንፈሳዊ ደስታ ይሰማናል፡፡ በበዓላት ወቅት እርስበርስ በመጠራራት ቤተሰብ ከሩቅም ከቅርብም ይሰባሰባል፤ ዕለቱ የደስታ ቀን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴም ‹‹አንተም፣ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህ እና ሴት ባሪያህ፣ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለ ሌዋዊ እና መጻተኛ፣ ድሃ አደግ እና መበለትም በበዓል ደስ ይበላችሁ፤›› በማለት በበዓል ቀን በዓሉን በማክበር መደሰት እንደሚገባ ይናገራል /ዘዳ.፲፮፥፲፬/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ እና የምስጋና ቃል አሰሙ፤›› ይላል /መዝ.፵፪፥፬/፡፡ ነቢዩ ዕዝራ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ደስ አሰኝቷቸዋልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ፤›› ሲል የእስራኤላውያንን በበዓል ቀን መደሰት አስረድቶናል /ዕዝ.፮፥፳፪፤ ፪ኛ ዜና መዋዕል ፴፥፳፫-፳፭/፡፡ በአገራችን አባባልም ‹‹አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም›› እንደሚባለው በዓመት በዓል ሕዝበ ክርስቲያኑ እርስበርስ እየተጠራራ አብሮ በመብላት በመጠጣት ይጫወታል፤ ይደሰታል፡፡

የበዓላት ክብር እኩል ነውን?

በዓላት በክብር ይለያያሉ፤ ለምሳሌ የእመቤታችን በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየወሩ በ፳፩ ቀን ይከበራል፡፡ መስከረም ፳፩፣ ኅዳር ፳፩፣ እና ጥር ፳፩ ቀን ደግሞ የእመቤታችን ዐበይት በዓላት ናቸው፡፡ እንደዚሁም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ወር በገባ በ፲፪ኛው ቀን ይከበራል፡፡ ኾኖም ግን የቅዱስ ሚካኤል ዐቢይ በዓል የሚከበረው በየዓመቱ በኅዳር ፲፪ እና ሰኔ ፲፪ ቀን ነው፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ደግሞ በየወሩ በ፲፱ ቀን በዓሉ ቢታሰብም ታኅሣሥ እና ሐምሌ ፲፱ ቀን ዐቢይ በዓሉ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በወር ውስጥ የሚገኙትን እያንዳንዱን ቀናት በቅዱሳን ስም ብትሰይምም በዓላትን በዐቢይነትና ታቦታትን በማውጣት የምታከብራቸው በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ሥርዓትም በዓላት በአከባር የተለያዩ መኾቸውንና ልዩ የበዓል ቀኖችም እንዳሉ እንረዳለን፡፡ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ምዕራፍ ፴፥፳፮ ላይ ‹‹በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ኾነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር፤›› ተብሎ የተጻፈው ኃይለ ቃል ለዚህ ማረጋገጫችን ነው፡፡

በዓላትን አለማክበር ምንን ያመጣል?

፩. ረድኤተ እግዚአብሔርን ያርቃል

በሰቆቃወ ኤርምያስ ምዕራፍ ፩፥፬ ላይ ‹‹ዳሌጥ፣ ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፡፡ በሮችዋ ዅሉ ፈርሰዋል፡፡ ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፡፡ እርስዋም በምሬት አለች፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ በዓላትን በማክበራችን ከእግዚአብሔር በረከትን እንደምንቀበል ዅሉ ባለማክበራችን ደግሞ ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ይርቃል፡፡

፪. ቅጣትን ያስከትላል

በመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ እንደ ተገለጸው የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ ነቢዩ ዳዊት በደስታ ምስጋና ያቀርብ ነበር፡፡ ሚስቱ ሜልኮል ግን ሲዘምር ባየችው ጊዜ ንጉሥ ኾኖ ሳለ ራሱን አዋረደ በሚል ሐሳብ ባለቤቷ ንጉሥ ዳዊትን ናቀችው፡፡ ዳዊትም ሜልኮልን ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እኾን ዘንድ ከአባትሽ እና ከቤቱ ዅሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይኹን፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እዘምራለሁ፤›› በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ እንደሚያስከብርና ከፍ ከፍ እንደሚደርግ ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔርም ለአምላኩ የዘመረውን ዳዊትን በመናቋ ልጅ እንዳትወልድ የሜልኮልን ማኅፀን ዘግቶታል /፪ኛ ሳሙ. ፮፥፲፮-፳፫/፡፡ ከዚህ ታሪክ በዓሉን ብቻ ሳይኾን በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎችንም ማክበር እንደሚገባን እንማራለን፡፡ ‹‹ዕልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፹፱፥፲፭/፡፡

በክብረ በዓላት ምን ዓይነት ልብስ መልበስ አለብን?

ሰው ወደ ሰርግ ሲጠራ ከቤቱ ያለውን፣ የተሻለውን ልብስ መርጦ እንዲለብስ መንፈሳውያን በዓላት የቤተ ክርስቲያን የክብሯ መግለጫ ቀናት እንደ መኾናቸው መጠን እኛ ክርስቲያኖችም በእነዚህ ቀናት የምንለብሰው ልብስ የተለየ መኾን ይገባዋል፡፡ የሌሊት ልብስ ለብሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ እንደማይገባ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡ በገዳማውያን አባቶች ዘንድ ለቅዱስ ቍርባን መቀበያ የሚኾን ልብስ ከሌሎች አልባሳት ተለይቶ ውኀ፣ ጭስ፣ አቧራ ከማይደርስበት ቦታ ይቀመጣል፡፡ አባቶች ይህንን ልብስ የሚለብሱት ለቅዱስ ቍርባን ብቻ ነው፡፡ በገጠሩ የአገራችን ክፍልም ልጆች ልብስ የሚገዛላቸው በአብዛኛው በጥምቀት ወቅት ነው፡፡ ይህም ለበዓሉ የሚሰጠውን ልዩ ክብር ያስረዳናል፡፡ እናቶቻችንም ‹‹ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› እያሉ በበዓለ ጥምቀት ያላቸውን አዲስ ቀሚስ አውጥተው ይለብሳሉ፡፡

በዓመት በዓል ቀን እንስሳት የሚታረዱት ለምንድን ነው?

በዓል ሲደርስ ገበያው ይደምቃል፤ ቤታችን ያምርበታል፡፡ እንበላቸው ዘንድ የተፈቀዱ እንስሳት ይታረዳሉ፡፡ በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለፋሲካ፣ ለልደት እየተባለ በግ ተቀጥቅጦ  ይቀመጥና ጊዜው ሲደርስ ይታረዳል፡፡ በበዓላት ቀን የከብት፣ የበግ፣ የፍየል መሥዋዕት ይቀርብ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ መጽሐፈ ዕዝራ ፫፥፬ ‹‹እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ፤›› ይላል፡፡ ዛሬም በበዓላት ቀን በየቤተ ክርስቲያኑ እና በየቤቱ የሚታረደው ይህንኑ አብነት በማድረግ ነው፡፡ (በተጨማሪም ዘሌ.፳፫፥፴፯፤ ሕዝ.፵፮፥፲፩ ይመልከቱ)፡፡

በአጠቃላይ በዓላትን ከሥጋዊ ሥራ ተከልክሎ ማክበር እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ‹‹በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኹንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ዅሉ አትሥሩበት፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘሌ.፳፫፥፯/፡፡ የበዓላት አከባበርም እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በኾነ ባህል ሳይኾን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ፤ የበዓሉን መንፈሳዊ ታሪክ በተመረኮዘ መንገድ የተሰጠን ትእዛዝ ነው፡፡ ዮሴፍ ወልደ ኮሪዮን በዜና አይሁድ መጽሐፉ እንደ ጠቀሰው አይሁድ በዕለተ ሰንበት ወደ መጸዳጃ ቤት እንኳን አይሔዱም ነበር፡፡ እኛ ግን እንደ አይሁዳውያን በተጋነነ መንገድ ሳይኾን ሰውነትን ከሚያደክም ሥጋዊ ሥራ ተከልክለን በዓላትን እንድናከብር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ አስቀድማ በሕገ ልቦና እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረች በኋላም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕፀ መስቀሉ የቀደሳት፣ በኪደተ እግሩ የባረካት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው መንፈሳውያን በዓላትን በሥርዓት ሲያከብሩ ኖረዋል፡፡ አሁን አሁን ግን በብዙዎቻችን ዘንድ እንደሚስተዋለው የበዓላት አከባበር ሥርዓት እየተጣሰ ይገኛል፡፡ በበዓላት ቀን ሥራ መሥራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ልማድ ሊስተካከልና ሊቀረፍ ይገባል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እንደ በዓለ ጥምቀት ባሉ የዐደባባይ በዓላት ወቅት የሚታየው የሥጋዊ ገበያ ግርግር ክርስቲያናዊ የበዓላት አከባበር ሥርዓትን እንዳያጠፋብን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በአገራችን ብሂል ‹‹በዓል ሽሮ የከበረ፣ ጦም ገድፎ የወፈረ የለም›› እንደሚባለው በዓላትን መሻር ከሚሰጠው ትርፍ ይልቅ የሚያመጣው መቅሠፍት ይብሳልና በዓላትን ለሥጋዊ ጉዳይ መጠቀሚያ ከማድረግ ይልቅ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገን በአግባቡ ማክበር ይገባናል፡፡ አንድ ክርስቲያን መንፈሳውያን በዓላትን በሥርዓት ሲያከብር የሚመለከቱ አካላት ‹‹ሃይማኖቱ እንዴት ደስ ይላል? እኛም እንደ እርሱ በኾንን›› በማለት እርሱንም ሃይማኖቱንም ያደንቃሉ፤ መንፈሳዊ ቅናትንም ይቀናሉ፡፡ ስለዚህም የጥንቱን ሥርዓት ጠንቅቀን፣ መልኩን ሳንለውጥ፣ ሥርዓቱንም ሳናፋልስ በዓላትን ማክበር ይገባናል፡፡ በዓላትን በሥርዓቱ አክብረን በረከትን እናገኝባቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡