ክብረ ሰሙነ ሕማማት – ክፍል ሁለት

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና (የሊቃውንት ጉባኤ አባል)

ሚያዝያ ቀን ፳፻፱ .

የክርስቶስ የሕማማቱ መንሥኤ

ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሰሙን መከራ) ባለቤቱ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቅዶ፣ ወስኖ እስከ መስቀል ድረስ በፈቃዱ መከራ የተቀበለበት ጊዜ ነው፡፡ አምላችን ሥራውን ያለ ምክንያት አይሠራውምና ለሕማሙና ለሞቱ መንሥኤ ከኾኑት መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፤

አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ

‹‹የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሏቸው፤ ‹እነሆ ይህን ሰው ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፡፡ ምን እናድርግ? እንዲሁ ብንተወውም ዅሉ ያምንበታል፡፡ የሮም ሰዎችም መጥተው አገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል›፡፡ ሊቀ ካህናት ቀያፋም ‹ሕዝቡ ዅሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል› አላቸው፤›› (ዮሐ. ፲፩፥፵፯-፶) ተብሎ እንደ ተጻፈ ለጌታችን መከራ መቀበል አንዱ ምክንያት አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ ነው፡፡

በዕለተ ሆሣዕና በምስጋና ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱና ተአምራትን ማድረጉ

በዕለተ ሆሣዕና በሕፃናት አንደበት ሳይቀር በሕዝቡ ዅሉ እየተመሰገነ ጌታችን ወደ ቤቱ መቅደስ መግባቱና በዚያ ወቅት ያደረገው ተአምራት ሌላው የመከራው ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት፤ ልጆችንም በቤተ መቅደስ ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ› እያሉ ሲጮኹ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም፤›› እንዲል (ማቴ. ፳፩፥፲፭)፡፡

ስለዚህም በሆሣዕና ማግስት (ሰኞ ዕለት) የአይሁድ ባለ ሥልጣናት ጌታችንን ለመግደል የአድማ ስብሰባ አድርገው ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ በድጋሜ ማክሰኞ ዕለት ተሰብስበው አሁንም ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ረቡዕ ተሰባሰቡ፤ በዚህ ዕለት ዅሉም አንድ ኾነው ይሙት በቃ የሚል ፍርድ በጌታችን ላይ ወስነው ስበሰባቸውን ደመደሙ (የመጋቢት ፳፫ እና ፳፬ ቀን ስንክሳር)፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችንን አሳልፎ የሚሰጣቸው ምሥጢረኛ ቤተሰብ የኾናቸውን ይሁዳን በማግኘታቸው ደስ አላቸው፡፡ ሠላሳ ብር ሊሰጡትም ተስማሙ፡፡ እርሱም ደስ ብሎት ሰው ሳይኖር አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ቦታ ይሻ ነበር (ሉቃ. ፳፪፥፫-፮)፡፡

ጸሎት ሐሙስ

በጸሎተ ሐሙስ ጊዜ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት

በዕለተ ሐሙስ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል ሠራዔ ሕግ፣ ፈጻሜ ሕግ የኾነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግ በታች ኾኖ ሕገ ኦሪትን እየፈጸመ አድጓልና በኦሪት ሥርዓት የሚፈጸመውን የመጨረሻውን በግዐ ፋሲካ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መመገቡ ነው፡፡ ሁለተኛው ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳ እንደሚያስይዘው ለሐዋርያት በምልክት ማስረዳቱ ነው (ዮሐ. ፲፫፥፳፩)፡፡ ሦስተኛው ደግሞ እንደ አገልጋይ ራሱን ዝቅ አድርጎ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ነው፡፡ በዚህም ኅፅበተ እግር ሐዋርያት እንደ ተጠመቁ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ኅፅበት መድኃኒታችን ክርስቶስ ወሰንና አቻ የሌለው ፍጹም ትሕትናውን የገለጠበት ምሥጢር እንጂ ጥምቀት እንዳልኾነ ብዙ መጻሕፍት ይስማማሉ፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛርቱን እግር ካጠበ በኋላ ‹‹እናንተ መምህራችን፣ ጌታችን ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፡፡ እኔ ጌታችሁ መምህራችሁ ስኾን ዝቅ ብዬ እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም ዝቅ ብላችሁ የወንድሞቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል፡፡ ምሳሌ ኾኛችኋለሁና፤›› በማለት የትሕትና ሥርዓት ሠርቶ እነርሱም በሥራ እንዲገልጡት አዝዞአቸዋል (ዮሐ. ፲፫፥፲፭)፡፡ በግእዝ የተጻፈ አንድ ትርጓሜ ወንጌል ‹‹እዘርእ ፍቅረ ወትሕትና ውስተ አልባቢክሙ፤ ፍቅርንና ትሕትናን በልባችሁ እዘራለሁ፤›› እንዳላቸው ይናገራል፡፡

ሠለስቱ ምእትም በአንቀጸ መነኮሳት ‹‹ወኢትትሐከይ ኀፂበ እግረ አኃው ሶበ መጽኡ ኀቤከ እስመ በእንተ ዛቲ ትእዛዝ ይትኀሠሥዎሙ ለእለ ያጸርዕዋ ለዛቲ ግብር ወለእመ ኮኑ ኤጲስ ቆጶሳተ እስመ እግዚአብሔር ኀፀበ እግረ አርዳኢሁ ቅድመ ወአዘዞሙ ከማሁ ይግበሩ፤ ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፡፡ ይህችን ሥራ ቸል የሚሏትን ስለዚህች ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና፡፡ ኤጲስቆጶሳትም ቢኾኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ፳፥፳፱፤ ፩ኛ ጢሞ. ፭፥፱-፲)፡፡

‹‹የማይታዩ ረቂቃን መላእክቱ አደነቁ፤ ከልዑል ዙፋኑ ወርዶ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያገለግል ባዩት ጊዜ አገልጋዮቹ መላእክት ደነገጡ፡፡ ትሕትና ወዳለበት ፍቅር የአሕዛብ እግረ ልቡናን ያቀና ዘንድ ግሩም እሳት በትሕትና መገለጡን ባዩ ጊዜ ብርሃናት ደነገጡ፤›› ይላል ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ (ሃይማኖተ አበው ፹፰፥፰)፡፡ ፊልክስዩስም ‹‹ወኅፅበተ ፋሲካ ትትሜሰል በምሥጢረ ትሕትና ፍጽምት፤ የፋሲካ ኅፅበት ፍጹም በኾነ የትሕትና ሥራ ይመሰላል፤›› ብሏል (መጽሐፈ መነኮሳት)፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ‹‹… ጌታችን ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በደረሰ ጊዜ ጴጥሮስም ‹አቤቱ እግሬን የምታጥበኝ አንተ ነህን? አለው፡፡ እርሱም መልሶ ‹እኔ እግርህን ከላጠብሁህ አንተም ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም› አለው፡፡ ይህም ማለት ‹እኔ በአገልጋይ ምሳሌ እግርህን ካላጠብሁ አንተም ከበታችህ ላሉ ራስህን ዝቅ ማድረግ አትችልም፡፡ ራስህን ዝቅ ካላደረግህም የእነርሱ አለቃ መኾን አትችልም፡፡ በሰማያት ባለው መንግሥቴስ ከእኔ ጋር እንዴት አንድ ለመኾን ትችላለህ?››› በማለት ራሱ ትሑት ኾኖ ጴጥሮስን ትሑት እንዲኾን አጥብቆ እንደ መከረው ይናገራል፡፡

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ መጻሕፍት በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ፍጹም ትሕትናውን ለመግለጥ እንደኾነ በማያሻማ ኹኔታ አረጋግጠዋል፡፡ ሐዋርያት በዚህ ጊዜ (በኅፅበተ እግር) ተጠመቁ የሚል ግን ማኅበረ ሐዋርያት ከባስልዮስ መጽሐፍ አገኘን ብለው ከጠቀሷት አንዲቷ ጥቅስ በስቀተር ሌላ አልተገኘም፡፡ ከዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖት አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት፤›› (ኤፌ. ፬፥፭) ባለው መሠረት ሠለስቱ ምእት በጉባኤ ኒቅያ በተናገሩት የሃይማኖት ጸሎት ‹‹ኀጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› (ሃይማኖተ አበው ፲፯፥፲፪) ከማለታቸውም ባሻገር ጥምቀት እንዳይደገም፣ እንዳይከለስ በፍትሕ መንፈሳዊ ከልክለዋል፡፡

በየዓመቱ የሕማማት ሐሙስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ፣ ዘወትር በየቀኑ በየገዳማቱና ትምህርት ቤቶች ለሚስተናገዱ እንግዶች ዅሉ ኅፅበተ እግር ይከናወናል፡፡ ኅፅበት ጥምቀት ነው ከተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠለስቱ ምእትም ኅፅበተ እግሩ ባለማቋረጥ ዅልጊዜ ሲተገበር (ሲከናወን) ሰዎች ዅሉ በየጊዜው ይጠመቃሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ሐዋርያትና ሠለስቱ ምእት ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲፈጸም ከወሰኑ በአንድ ምላስ ሁለት ምላስ ያሰኛልና፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚጣረሱ ተቃራኒ ሥርዓቶችን ማራመድ አይቻልምና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋር ደግሞ የእግር መታጠብ ጥምቀት ከኾነ ጌታችን እግራቸውን አጥቦ እንዲህ አድርጉ ብሎ አዞናልና አዲስ ተጠማቂዎችን አብሶም ሕፃናትን መላ አካላቸውን እያጠመቅን ለምን በቅዝቃዜ እናሰቃያቸዋለን? እግራቸውን ብቻ አጥበን ‹‹ተጠምቃችኋል›› እያልን አናሰናብታቸውም? እስኪ በማስተዋል እንመርምረው፡፡

መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ያከናወናቸው አምላካውያት ተአምራት እንዳይገለጡ ‹‹ይህን ለማንም እንዳትናገሩ፤›› እያለ አጥብቆ ይከለክል ነበር (ማቴ. ፰፥፬፤ ፱፥፴፤ ፲፮፥፳፤ ፲፯፥፲፱)፡፡ ይኸውም ገደቡ ካሣ እስከሚፈጸም እስከ ትንሣኤ ድረስ ኾኖ ከዚያ በኋላ ግን ተአምራቱ መነገር እንዳለበት ‹‹ወልደ እጓለ እመ ሕያው ክርስቶስ ከሙታን እስኪነሣ›› ብሎ ግልጽ አድርጎታል (ማቴ. ፲፯፥፲፱)፡፡ ይህንም ‹‹መከራን ከፊት አስቀምጦ፣ ደስታን፣ ክብርን መናገር ስለሚገባ ነው›› ብለው ሊቃውንቱ አትተውታል፡፡

ይቆየን