ክርስቶስን መስበክ እንዴት?
ሚያዚያ 25፣ 2003ዓ.ም
ፕሮቴስታንቶችና ፕሮቴስታንታዊ መንገድ የሚከተሉ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን አልሰበከችም የሚል ክርክር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በምላሹ እንዲሳተፉበት ጋብዘናል፡፡ ለዚህ እትም የያዝነውን እነሆ!
“ቤተክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ወንጌል ነው”
ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ሁለት ሺሕ ዓመታት አልፏታል። ይህንንም ሊቃውንቱ ምእመናንም ያስረዱትና የተረዱት ነው። ወንጌል ካልተሰበከ ክርስቲያኖች እንዴት ለአሁን ዘመን ደረሱ? ወንጌል መሠረት፣ በጎ እርሾ ሳይሆነው፣ ወንጌል ብርታት ሳይሆነው ይህን ሁሉ ዘመናት አቆራርጦ፣ ድልድዩን አልፎ እንዴት እዚህ ደረሰ? ወንጌል ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ነው፡፡
በቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ የሚያነቧቸው፣ የሚተረጉሟቸው፣ ምእምናን የሚሰሟቸው፣ የሚታነጹባቸው ድርሳናት፣ ተአምራት ወንጌል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌልን የሚፈቱ፣ የሚተረጉሙ፣ የሚያመሰጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆኑ መጻሕፍት በቤተክርስቲያን አይነበብም፣ አይተረጎምም፣ አይሰማም። ቤተክርስቲያን ወንጌልን የምትሰብከው በቃል፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው። ጥምቀት ወንጌል ነው። ቤተክርስቲያንም ጥምቀት የዘወትር ሥራዋ ነው። ወንጌል ስለ ጥምቀት ነው የሚነግረን። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙም በየዕለቱ ይቀርባል፤ ይህ ወንጌል ነው። ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን የተቀደሰውን ጋብቻቸውን በተቀደሰው ቦታ፣ በተቀደሰው ጸሎት በምስጢረ ተክሊል ይፈጽማሉ። ይህም ወንጌል ነው። እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን ከዚህ ዓለም ሲሸኙ በሥርዐተ ፍትሐት፤ ብሉያትና ሐዲሳት እየተነበቡ፣ ያሬዳዊ ዜማ እየተዜመ ነው። ይህ ወንጌል ነው። አላዛርን ከመቃብር ተነሥ እንዳለው፤ የታሰረበትን ፍቱት እንደተባለ እንደተ ፈታ ሁሉ፤ ካህናትም ከኃጢአት እስራት እየፈቱ ሕዝባቸውን መሸኘት፤ “አቤቱ እግዚኦ ይቅር በለው ሲያውቅ፣ ሳያውቅ በሠራው ኃጢአት ይቅር በለው” እያሉ መሸኘት ወንጌል ነው።
ቤተክርስቲያን ራሷም፣ እግሯም፣ መሠረቷም፣ ጉልላቷም ወንጌል ነው። ይህን በቅንነት፣ በበጎ ነገር፣ በምስጢር፣ በትርጓሜ ለሚያዩት ነው። በጥላቻ ካዩት ነጩም ጥቁር ነው፤ ብርሃኑ ጨለማ ነው፤ በጥላቻ ማየትና በፍቅር ማየት፤ በሐሰት መናገርና በእውነት መናገር መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። የቤተክርስቲያን ጥንተ ጠላቶች ለቤተክርስቲያን በጎ ይመሰክራሉ ብለን ከጠበቅን የተሳሳትን ይመስለኛል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን “እግዚአብሔር ከእናንተ ምስክርነትን አይፈልግም” ነው ያላቸው። ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለ ክርስቶስ በጎ ስለማይመሰክሩ ስለማይናገሩ ነው። ምክንያቱም በጭፍን፣ በቅናት፣ ስለጠሉት ነው። ቤተክርስቲያንም ከጠላቶቿ የእውነት ምስክርነትን አትጠብቅም፤ በበጎ ለሚያዩአት ግን ምስክርነቱ በእጅ የሚጨበጥ (የሚዳሰስ) በዐይነ የሚታይ ነው።ቤተክርስቲያን ወንጌል ያልሰበከችበት ዘመንም፣ ጊዜም የለም። ወንጌል አልተሰበከም ለሚሉ ሰዎች ትናንት አለነበሩም፣ ዛሬም የሉም። ለነገሩስ የት ሆነው ያዩታል? ቢኖሩም አይገባቸውም፤ ውስጣቸውም በብዙ ችግር የተተበተበ፤ በቅራኔ የተሞላ ነው። በቅራኔ የተሞላ ደግሞ ከውጭ የሚነገረውን በጎ ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለም።
“ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው”
ሰው በተሰጠው የፈቃድ ነጻነት መሠረት የፈለገውን የመናገር መብት አለው። ፍሬ ነገሩ እውነቱ የቱ ነው? ሐሰቱስ? የሚ ለው ነው። ዲያብሎስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል የብርሃን መላክነት አይመስክርም፤ ሊመሰክርም አይችልም። «ሚካኤል ደካማ ነው» እያለ የፈለገውን መናገር ይችላል። የዲያብሎስን ምስክርነትም ሚካኤል አይፈልገውም፣ አይቀበለውምም። ዲያበሎስ የፈለገውን ቢናገር ሚካኤልን አይከፋውም፤ ከጠላቱ ቡራኬ ስለማይጠብቅ። እንደዚሁ ሁሉ የእኛም ቤተክርስቲያን የሌሎችን ቤተእምነቶች ምስክርነትም ሆነ ክስ አታደንቀውም፤ አትደነግጥበትምም የእኛ ቤተክርስቲያን ጨርቅ ሰጥታ ጉቦ ሰጥታ እንዳልተስፋፋች ሁሉም ያውቁታል፤ ታዲያ ወንጌልና ክርስቶስን ሳትሰብክ ቤተክርስቲያን ሆና ሁለት ሺሕ ዓመታትን እንዴት ተሻገረች? አሸናፊ ስለሆነች በእውነቷ ብቻ ቆማ የምትኖር ናት። ጉቦ አይከፈልባትም፣ ማባበያም አትጠይቅም።
ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ልብን አሻክሮ ምላስን አለዝቦ በማነብነብ አይደለም፤ በድርጊት በማሳየትም እንጂ። በአንድ ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአንድ ቤተክርስቲያን በአንድ ቀን ብቻ የምናደርገው ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ስብከቱ፣ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ዋዜማው በተግባርም ታቦት ይዘን ቆመን ያስተላለፍነው ትምህርት በጠቅላላው መናፈቃኑ ለአንድ ዓመት ከጮኹበት፣ ብዙ ነገር ካወጡበት «አገልግሎት» እጅግ ብልጫ አለው። የዚህ አጠቃላይ አገልግሎታችን ዋነኛ ማእከልም ወንጌልና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ንዋያተ ቅድሳቶቻችን በሙሉ ስብከቶች ናቸው። በቅዳሴ ላይ ቄሱ፣ ዲያቆኑ መስቀል ይዞ የሚዞረው ምን ለማሳየት ነው? ቀሳውስት ዕጣን እያጠኑ “ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ” እያሉ ሲያመሰግኑ ምስጢረ ሥላሴ እና ምስጢረ ሥጋዌን መስበከ፣ ማስተማራቸው ነው። ልብሰ ተክህኖዎቹ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳቱ ሁሉ መስቀል የሚደረግበት ለጌጥ አይደለም። ይህ ስብከት አይደለም እንዴ? መቅደስ ውስጥ ስንቀድስ በአራቱ ማእዘን የምንቆመው ጽርሃ አርያምን እያሳየን ነው። እነርሱ የማያስተውሉትን ሰባቱ ሰማያትን አምጥተን መቅደሱ ላይ ቁጭ አድርገን የምናሳያቸው ለስብከት ነው። ኪሩቤል እንዴት አድርገው ጌታን እንደተሸከሙት ታቦቱን መንበሩ ላይ አስቀምጠን ስንቀደስ እናሳያለን። በተጨባጭ እያሳየን እያሰተማርን ነው።
ደስ ሊለን ይገባል፤ ለሁለት ሺሕ ዘመን ወንጌል ሳይነበብባት በተለያየም መንገድ ሳይሰበክባት የማትውል የማታድር እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ቤተክርስቲያንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነች። ቢያንስ በቅዳሴ ላይ ሰባኪ ያልቆመባቸው፣ ወንጌል ያልተሰማባቸው፣ ሃይማኖት አበው የማይነበብባቸው ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የሉም። ስለዚህ ስብከት መንዘፍዘፍና ዓላማ የሌለው ጩኸት አይደለም። በእርጋታ፣ በማስተዋል፣ በጥንቃቄ የሚፈጸም በብዙ ዓይነት መንገድ የሚከናወን፤ ያልነበሩትን የምናመጣበት የነበሩትን የምናጸናበት አገልግሎት መሆኑን ሁሉም ይረዳ።