ክርስቲያናዊ ሕይወትና ምግባር (አንደኛ መጽሐፍ)

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
 
ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍፁም የሚሆነው የዘልማዱን አኗኗር ትተን ከክርስቶስ ጋር አንድ ሁነን በእርሱ ቅዱስ መንፈስ ሱታፌ ኑሮን በእርሱና ስለ እርሱ ለእርሱ ብለን የምንሆነውና የምናደርገው የዘውትር ጥረትና መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ማለትም ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ምግባርም ወይም በጎ አድራጎት በዚሁ ትርጉም ውስጥ ቢጠቃለልም በተለየ መንገድ በክርስቶስ ሁነን ለሌሎች የምናደርገውን የፍቅር ሥራ ውጤት ይመለከታል፡፡ ክርስቲያን መሆን ማለት ከልዩ ልዩ አለማዊና ሥጋዊ ነገሮች ተለይቶ በአንድ ልብ ተወስኖ ራስን ለክርስቶስ ብቻ አስገዝቶ በእርሱ ቅዱስ መንፈስ ተመርቶ ለቃሉ እየታዘዙ በመኖር በስሙ መከራውን በመታገሥ እስከ መጨረሻው በታማኝነት መጽናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ክርስቲያናዊ ሕይወታቺንና ምግባራችን በሌላ እንግዳ ሕግና መመሪያ ሳይሆን በራሱ በክርስቶስና በክርስቶስ ቅዱስ መንፈስ መሆን እንዳለበት የምንመሰክረው፡፡ እኛ ክርስቲያን መስለን ለመታት ሳይሆን ሆነን በመገነትና መሆናቺንንም በመንፈሳዊ ተጋድሎ በተግባር ስንገለጸው ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያን መሆን ወይም አለመሆን እዚህ ላይ ነው ጥያቄው፡፡