ክርስቲያናዊ ሕይወት

መጋቢት 19/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

  • “ለማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ መካነ ድር ዝግጅት ክፍል፡፡ መንፈሳዊ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ እባካችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝን ምክር ለግሱኝ?”

ውብ አንተ


የተከበርክ ወንድማችን ውብ አንተ ክርስቲያናዊ ሕይወትህ እንዲበረታ መንፈሳዊ ምክር ፈልገህ ስለጻፍክልን እናመሰግናለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ይህ ነው ወይም ያ ነው ብሎ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጊዜና ቦታ ይገድበናል፡፡

 

ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝ ምክር እፈልጋለሁ የሚለውን ዐሳብህን ብቻ ነጥሎ ማየት አሁን ያለህበትን የሕይወት ደረጃ ብናውቀው ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም ጥምቀተ ክርስትናን ተቀብለህ በክርስቶስ ክርስቲያን እንደተባልክ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም እንደ ክርስቲያን መኖር ያለብህን ሕይወት ስላልኖርክ በውስጥህ የሚወቅስህ ነገር አለ፡፡ ይህ ወቃሽ ኅሊና በልቡናህ ስለተሳለ እግዚአብሔርን አመስግነው፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የሚጸጸት፣ የሚጨነቅ የሚተክዝ ልቡና ያለው ሰው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ያልተለየው ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን ሲመሰክር እንዲህ አለ “…መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይናገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና” ሮሜ.8፥26-27

መንፈስ ቅዱስ አካሉ አንድ ሲሆን ጸጋው ብዙ ነው፡፡ ጸጋው የማይመረመር ረቂቅና ምሉዕ  ስለሆነ በጎ ችሎታዎች ሁሉ ከእሱ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሰማዕታትን ለእውነትና ምሥክርነት የሚያዘጋጅ፣ ሐዋርያትን ለስብከት የሚያሰማራ መነኮሳትን በገዳም የሚያጸና ተነሳሕያንን ለንስሐ የሚያነሣሣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ከእኛ ጋር ሲሆን ለጸሎት እንነሣለን ለምጽዋት እጆቻችንን እንዘረጋለን ለምሥጋና አፋችንን እንከፍታለን፡፡ ለአምልኮ ወደ ቅድስናው ቦታ እንገሰግሳለን፡፡

 

ይህ በመሆኑ ኀጢአት ስንሠራ ከቤተ መቅደስ ስንለይ ከቃለ እግዚአብሔር ስንርቅ የምንጨነቀው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሲሆን ብቻ ነው፡፡

 

ክርሰቲያናዊ ሕይወት በጣም ጥልቅና ሰፊ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ክርስቲያናዊ ሕይወት ተመክረን ከምንሰማው ተጽፎልን ከምናነበው ይልቅ በሕይወታችን የምንቀምሰው በሒደት የምንማረው ሕይወት ነው፡፡ ሒደት ደግሞ መውደቅና መነሣት፣ ማዘንና መደሰትን ማልቀስና መሳቅ፣ ማጣትና ማግኘትን ይመለከታል፡፡ ክርስትና ስናገኝ የምንደሰትበት ስናጣ የምናዝንበት ስንወድቅ ተስፋ የምንቆርጥበት ሕይወት አይደለም፡፡ ክርስትና በትናንቱ ጥንካሬያችን የምንኩራራበት የትዝታ ሕይወት ሳይሆን አሁን የምንኖርበት ቤት የምንጓዝበት ጎዳና ነው፡፡

ክርስትና ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 38 የተጻፈውን እንመልከት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ሲያስተምር በርካታ ሰዎች ልባቸው ተነክቷል፡፡ በትምህርቱም ተመስጠው ወደ 3ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች አምነዋል፡፡ እነዚህ ያመኑትን ሰዎች በሕይወታቸው የፈጸሙት በርካታ ቁም ነገር ነበር፡፡

1. የሚያስተምረውን ትምህርት በሚገባ አደመጡት ስለሆነም ልባቸው ተነካ፡፡

አሁንም ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሔድ ቅዱሳት መጻሕፍት ስናነብ መዝሙር ስናዳምጥ በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ሳናቋርጥ ሁል ጊዜ ቃለ እግዚአብሔርን በማስተዋል የምናዳምጥ ከሆነ አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ይከፍታል፡፡ በመቀጠልም ወደ እውነተኛው የሕይወት አቅጣጫ ይመራናል፡፡ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ይመራችኋል” /ዮሐ.16፥13/ ብሎ ሐዋርያው እንደጻፈልን እውነት ወደ ሆነው ክርስቶስ ያደርሰናል፡፡

 

2. ምን እናድርግ? አሉ፡፡

ሰው የሚማረውን ከተረዳው በኋላ ቀጣዩ ጥያቄ ምን ላድርግ? ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሊያሳድድ ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት የሚያደርገው ሥራ እግዚአብሔርን ስላሳዘነው የመውጊያውን ጦር ብትቃወመው ለአንተ ይብስብሃል አለው፡፡ የምቃወምህ አንተ ማን ነህ? ብሎ ጥያቄውን አቀረበ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለው ታዲያ ምን እንዳደርግ ትወዳለህ” ብሎ ተናገረ፡፡ የምታደርገውን በከተማ የምታገኘው ሰው ይነግርሃል ብሎ አምላካችን ፈቃዱን ገለጠለት፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ሕይወቱ ተለውጦ እግዚአብሔርን እያገለገለ ኖረ፡፡ /ሐዋ.9፥1/

 

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ሐዋርያው ፊልጶስን ክርስቲያን እንዳልሆን የሚከለክለኝ ነገር ምንድን ነው?” /ሐዋ.8፥36/ ብሎታል፡፡

 

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባቦች የሚያስረዱት እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ሰዎችን ሲያስተምር ከልባቸው የተነኩ ሰዎች የመጀመሪያው ግብረ መልሳቸው “ምን ላድርግ?” የሚል ነው፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እነዚህን አዲስ አማንያን “ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁም ይሠረያል” አላቸው፡፡ ስለዚህ ስረየተ ኀጢአትን ለማግኘት ንስሐ መግባት ያስፈልጋል፡፡

 

3. በጸሎት በረቱ

በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ያመኑት ምእመናን ንስሐ ገብተው ከተጠመቁ በኋላ በጸሎት ይተጉ ጀመር፡፡ ያላቸውን ሀብት ሸጠው በአንድነትና በኅብረት በጥሩ ልብ ይተጉ ነበር፡፡ ይላል እነዚህ ሁሉ ሒደቶች ለክርስትና ሕይወታችን ጥሩ የሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

ወደ ክርስትና ሕይወት ለመመለስ እና በዚሁም ለመጽናት የአባቶቻችንን ሕይወት የሚያብራሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይጠቅማል የእግዚአብሔርን ቃል የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው፡፡” /ዕብ.13፥7/ እንዳለው ሐዋርያው የቅዱሳን ሐዋርያትን፣ ሰማእታትን ጻድቃንን ሕይወት ስንመለከት በሃይማኖት እንበረታለን፡፡

 

ጠያቂያችን ውብ አንተ፡፡ ዋናው እና ትልቁ ነገር አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለህ የልብ ፍላጎት ነው፡፡ ፍላጎትህ ስሜታዊ ሳይሆን ልባዊ ከሆነ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ያስተምርሃል፡፡ ስለዚህ ሳታቋርጥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ ቅዳሴውን አስቀድስ ቃለ እግዚአብሔርን ተማር መዝሙርን አዳምጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ ሊቃውንት አባቶችን ቅረባቸው ቅዱሳት መካናትን ተሳለም፡፡ የበለጠ ፍቅሩ እያደረብህ ጣእሙ እየገባህ ሕይወቱ እየናፈቀህ ይሔዳል፡፡ ሁሉም የሚሆነው በፈቃደ እግዚአብሔር ስለሆነ በሃይማኖት እንድትጸና አምላክህን በጸሎት ጠይቀው፡፡

 

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔ ተማሩ በነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” /ማቴ.11፥28-30/

 

ወስብሐት ለእግዚብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር፡፡