ካህናተ ሰማይ
ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ቅዱሳን መላእክት ምሕረትን ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ልጅ፤ ጸሎትን ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ለዘለዓለም የማይሞቱ ረቂቃን መናፍስት ናቸው፡፡ በመዓርጋቸውና በነገዳቸውም ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ ኃይላት፣ አርባብ፣ መናብርት፣ ሥልጣናት፣ መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ተብለው ይመደባሉ፡፡ ‹‹ወኍልቆሙ ለእሙንቱ መላእክት ወሊቃነ መላእክት መናብርት ወሥልጣናት አጋእዝት ኃይላት ወሊቃናት ኪሩቤል ወሱራፌል›› እንዲል /አንቀጸ ብርሃን፤ ኵሎሙ ዘመላእክት/፡፡
በአቀማመጥም ኪሩቤል፣ ሱራፌልንና ኃይላትን በኢዮር፤ አርባብን፣ መናብርትንና ሥልጣናትን በራማ፤ መኳንንትን፣ ሊቃናትንና መላእክትን በኤረር አስፈሯቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹እኔ ነኝ ፈጣሪያችሁ›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ አረጋግቶ ኅቡዕ ስሙ የተጻፈበትን ሠሌዳ ሰጥቷቸው፤ አንድም እሑድ በነግህ የተፈጠረው ብርሃን ዕውቀት ኾኗቸው ቅዱሳን መላእክት ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ምሥጢረ ሥላሴን አምልተው አስፍተው ተናግረዋል /ኩፋሌ ፪፥፰፤ ኢሳ. ፮፥፫/፡፡ ይህንን ሃይማኖታቸውን ምክንያት አድርጎ በየነገዳቸው አለቃ ሹሞ ቀብቷቸዋል (አክብሯቸዋል)፡፡
በዚህም መሠረት በኢዮር ያሉት መላእክት አራት አለቃ፣ ዐርባ ነገድ ኾነው የተመደቡ ሲኾን ከእነዚህም ዐሥሩ የኪሩቤል፣ ዐሥሩ የሱራፌል ነገድ ነው /መዝ.፳፫፥፯-፲፤ ማቴ.፳፬፥፴፩/፡፡ በቍጥርም ዘጠና ዘጠኝ ነገድ ናቸው፡፡ ‹‹ኀዲጐ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ ቆመ ማእከለ ባሕር›› እንዲል /ሰላም ዘጥምቀት፤ ራእ. ፲፪፥፱/፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሃያ አራት ሊቃነ መላእክትን መርጦ በመንበረ መንግሥት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቁሟቸዋል፡፡ የብርሃን ዘውድ (አክሊል) ደፍቶላቸዋል፡፡ የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ አስይዟቸዋል፡፡ እንደዚህ አድርጎ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህም ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ይባላሉ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እንደምናገኘው በየዓመቱ ኅዳር ፳፬ ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሰማያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የካህናተ ሰማይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ካህናተ ሰማይ አገልግሎት የሚያስገነዝብ አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፤
ሱራፊ ማለት መልአክ፣ ከካህናተ ሰማይ አንዱ ማለት ነው፡፡ ሱራፌን፣ ሱራፌል፣ ሱራፌም (በፅርዕ ሴራፊም፣ በዕብራይስጥ ስራፊም) ማለት የነገድ ስም፣ ልዑላን መላእክት፣ ሊቃናት፣ የሚያጥኑ፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ቀዳሾች ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፰፻፹፮/፡፡ ከዚህ ላይ ሱራፊ ነጠላ ቍጥርን፤ ሱራፌል ደግሞ ብዙ ቍጥርን ያመለክታል፡፡ ሱራፌል ለቅዱሳን በሰው አምሳል በመገለጣቸው ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል /ኢሳ.፳፬፥፳፫፤ መሳ.፲፫፥፪-፳፭፤ ዳን.፲፥፲፰-፳፩/፡፡ በግእዝ ቋንቋ ደግሞ ካህናተ ሰማይ ይባላሉ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው የሚሰጡትን ሰማያዊ አገልግሎት የሚያመለክት ስም ነው፡፡
በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ ሰኑይ (ሰኞ) ከኪሩቤል ሠራዊት ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳን፣ ከሱራፌል ሠራዊት ገጸ ንሥርና ገጸ እንስሳን ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ፣ ከሰማይ ውዱድ በታች ጀርባቸውን ወደ ውስጥ፣ ፊታቸውን ወደ ውጭ አድርጎ አቁሟቸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹የኔን የፈጣሪያችሁን ፊት ማየት አይቻላችሁም›› ሲል ነው፡፡ የኪሩቤል አለቃቸው ማለትም ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳ ኪሩብ፤ የሱራፌል አለቃቸው ማለትም ገጸ ነሥርና ገጸ ላሕም ደግሞ ሱራፊ ይባላል /ሥነ ፍጥረት ዘእሑድ/፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› /ራእ. ፬፥፮፤ ፭፥፰/ በማለት ስለ ሱራፌል ሰማያዊ አገልግሎት የተናገረ ሲኾን፣ ‹‹በፊታቸው የበጉን ሥዕል ያያሉ›› ማለቱ የክርስቶስን ትስብእት በጌትነት ያዩታል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ወደቁ›› ሲልም መስገዳቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹በግ›› የተባለውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ደምን የተረጨች ልብስ›› ማለቱም ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ መቀበሉን፤ የታተመ መጽሐፍ የክርስቶስ ትስብእት የማይመረመር መኾኑን፤ ‹‹ለበጉ ሥዕል፣ ለታለለችው ልብስና ለታለለው መጽሐፍ ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› ሲልም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትም በሦስትነትም ለሚመለከው ለክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ምስጋና ማቅረባቸውንና መገዛታቸውን ያመለክታል /የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ፣ ፫፥፯-፱/፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤልም ካህናተ ሰማይ ያለ ዘር መገኘታቸውን ሲያመለክት ‹‹በመንበሩ ዙሪያ ቁመው ያሉ ካህናት ኅብራቸው መረግድ የሚባል ዕንቍን ይመስላል›› በማለት ተናግሯል፡፡ ጸጋቸውን ሲገልጽ ደግሞ ‹‹ብሩህ ልብስ ለብሰዋል፤›› ክብራቸውን ሲመሰክርም ‹‹በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተዋል›› ብሏል፡፡ ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የንጽሕናቸውና የቅድስናቸው መገለጫ ሲኾን፣ በራሳቸው ላይ የተቀዳጁት ዘውድ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ዘለዓለማዊ ክብር ያሳያል፡፡ ቍጥራቸው በሃያ አራት መገለጹም ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ኾኗቸው ለሃያ አራት ሰዓታት ሳያቋርጡ ጸሎትና ምስጋናን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ አንድም የ፲፪ቱ ነገደ እስራኤል እና የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ሲኾን (፲፪ + ፲፪ = ፳፬) ይኸውም የብሉይና የሐዲስ ኪዳን አባቶች በአንድነት ኾነው እንደ ሱራፌል በምድር በቤተ መቅደስ፤ እንደዚሁም በሰማይ በገነት (በመንግሥተ ሰማያት) ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ የሚያመሰግኑ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ በዘመነ ብሉይ ደብተራ ኦሪትንና መቅደሰ ኦሪትን በሃያ አራት ሰሞን ተመድበው ያገለግሉ የነበሩ ካህናትም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌዎች ናቸው /፩ኛዜና. ፳፬፥፩-፲፱፤ ሕዝ. ፩፥፭-፳፪፤ ራእ. ፭፥፰-፲፬/፡፡
ካህናተ ሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲያቀርቡ አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው ላይ አውርደው ያለማቋረጥ ይሰግዳሉ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ሰማያዊ ሥርዓት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ፤ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) በመንበሩ ዙሪያ ቆመው በፊቱ ሲሰግዱ የመለኮት እሳት ሲበርቅ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ፤›› /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡ ይህም ምስጋና በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ የጸሎት ክፍሎች ይገኛል፡፡ ‹‹…. ወባቲ ለዛቲ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ መላእክት አርአያ ዘበሰማያት ቤተ ክርስቲያሰ ትትሜሰል በጽርሐ አርያም ዘላዕሉ ….፤ .… ለዚህች ቤተ ክርስቲያን በሰማያዊው አገልግሎት አምሳል የመላእክት የአገልግሎት ሥርዓት አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያንስ በላይኛው (በሰማያዊው) ጽርሐ አርያም ትመሰላለች ….›› እንዳሉ አባ ጊዮርጊስ /ሰዓታት፣ ኵሎሙ ዘዘወትር/፡፡
ዛሬም ምድራውያን ካህናት ማዕጠንትና መስቀል ይዘው በመንበሩ ፊት ቆመው ሲያጥኑ የሚሰግዱት፤ እንደዚሁም ኪዳን ሲያደርሱና ወንጌል ሲያነቡ መጠምጠሚያቸውን የሚያወርዱት ከዚህ ሥርዓት በመነሣት ነው፡፡ ሱራፌል በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ማዕጠንት ይዘው፣ እንደሚሰግዱና አክሊላቸውን እንደሚያወርዱ ኾነው በሥዕለ ሥላሴ ግራና ቀኝ የሚሣሉትም ይህንን አገልግሎታቸውን ለማስታዎስ ነው፡፡ እንደ ጸሎተ ዕጣን፣ ቅዳሴ፣ ማኅሌት፣ የመሰሉ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች ዅሉ ከካህናተ ሰማይ የተወረሱ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሠረት የኾነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቱን የተቀበለው ከሱራፌል መኾኑንም ‹‹ሃሌ ሉያ ዋይዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዓ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ፤ ‹ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን፡፡ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ የጌትነትህ ቅድስና በሰማይ በምድር መላ› እያሉ ሲያመሰግኑ በሰማይ ከመላእክት የሰማሁት ዜማ ምንኛ ድንቅ ነው?›› ከሚለው የአርያም ክፍል ከኾነው ጣዕመ ዜማው ለመረዳት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱና በሰዓታቱ የካህናተ ሰማይ አገልግሎታቸውና ስማቸው በሰፊው ሲጠራ ይኖራል፡፡
ሠለስቱ ደቂቅ ‹‹እግዚአብሔርን አራዊትና አንስሳት ዅሉ ያመሰግኑታል›› በማለት እንደ ተናገሩት ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ሌሊትና ቀን ምስጋና ሲያቀርቡ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሲሰማ ዶሮ እንደሚጮኽና እግዚአብሔርንም እንደሚያመሰግን በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፤ ‹‹ቀን በስድስተኛው ሰዓት የኪሩቤል ልመና ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ ሌሊት በአራተኛው ሰዓት ሱራፌል ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ በዐሥረኛው ሰዓትም ሰማያት ይከፈታሉ፤ እግዚአብሔርም የሰውን ልጆች ጸሎት ይሰማል፡፡ የለመኑትንም ዅሉ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህችም ሰዓት ከሱራፌል ከክንፎቻቸው ድምፅ የተነሣ ዶሮ ይጮኻል፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል፤›› /ሥነ ፍጥረት ዘእሑድ/፡፡
እኛ የሰው ልጆችም የተፈጠርንለት ዓላማ የእግዚአብሔርን ስም ለመቀደስ፣ መንግሥቱንም ለመውረስ መኾኑን በማስተዋል ስለ ግሩምና ድንቅ ሥራው ዅሉ ‹‹አቤቱ የኀያላን አምላክ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ሥራህም ድንቅ ነው›› /መዝ. ፵፯፥፪/ እያልን ዘወትር አምላካችንን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ በምድር በቤተ መቅደሱ፣ በሰማይም በመንግሥቱ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያልን እግዚአብሔርን ከቅዱሳን መላእክት ጋር ለማመስገን ያብቃን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ እኛንም በካህናተ ሰማይ ጸሎት ይጠብቀን፤ በረከታቸውም ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡