ከውድቀት አነሣን!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ጥቅምት ፳፮፳፻፲ .

እውነት ተሸሽጎ ሐሰት ወጥቶ ገሃድ

በፍርድ አደባባይ ውሳኔ ሲንጋደድ

የእውነትን ጌታ ብለውት ሐሰተኛ

በደልን ይቅር የሚል ተብሎ በደለኛ

ድውይ በፈወሰ ባስነሣ ሙታንን

ኅብስት አበርክቶ ባስታገሠ ርኃብን

ከወንጀል ተቆጥሮ ሕግን ሠሪ አምላክ

ሕግ አፍራሽ ተብሎ ለሕዝቡ የሚሰብክ

አይሁድ ሲያሠቃዩት

በመስቀል ሲሰቅሉት

ቀራንዮ አምባ በግፍ ሲቸነከር

የሞት ጽዋን ሲቀምስ ስለ አዳም ፍቅር

ማስተዋል ተስኖአቸው

በቅናት በተንኮል ሲታወር ዓይናቸው

ሕሊና ያላቸው ማሰቢያ አእምሮ

ዓይነ ልቦናቸው በጥቅም ታውሮ

በፍርሃት ታስሮ

እውነትን ሸሽገው ሐሰትን ሲናገሩ

በንጹሕ ክርስቶስ ላይ ክፉ ሲናገሩ

ለአዳም የተገባው የተስፋ ቃል ኪዳን

ፍጻሜ አግኝቶ ያኔ በዕለተ ዓርብ

መድኅን ዓለም ጌታ ራሱ ፈቅዶ

በፍቅር ተገዶ

በሐሰት ሲከሰስ

ባልሠራው ሲወቀስ

በግፍ ሲንገላታ

በጥፊ ሲመታ

ምራቅ ሲተፋበት

በጅራፍ ሲገረፍ

የሞቱ ውሳኔ ብይን ሲተላለፍ

ፍቅር የሆነ ጌታ  በፍቅሩ ማራኪ

እውነትን ይቅርታን  በተግባር ሰባኪ

እውነት ሆኖ ሳለ ተብሎ ሐሰተኛ

ሞታችን ሊሞት ተከሶ ስለ እኛ

ድንግል ስታለቅስ ስለ ልጇ ሥቃይ

በቀራንዮ ምድር ጠፍቶ አቁሙ ባይ

ፀሐይ ብርሃኗን ለምድር ከልክላ

ያን ጊዜ የፈጠራትን ጌታ አክብሩ ብላ

ጨረቃ ደም ለብሳ ረግፈው ክዋክብት

ፍጥረቱ ሲጨነቅ ምድር ለብሳ ጽልመት

ለሰሚው በሚከብድ ቃላት በማይገልጸው

በመከራ ውሎ አዳምን አዳነው!

ዲያብሎስ ታሠረ አዳም ነጻ ወጥቶ

ልጅ ተባለ ዳግም በደሉ ተረስቶ

የማይሞተው አምላክ ስለ እኛ ሲል ሞቶ

ከውድቀት አነሣን ልጅነትን ሰጥቶ!