ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም
በአያሌው ዘኢየሱስ
መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፤›› (ዮሐ.፫፥፫)፡፡
ይህ ቃል ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ካስተማረው ትምህርት የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ብዙ የተማረ፤ ብዙ ያወቀ የሃይማኖት ሊቅ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ሊቅ፣ ምሁር፣ አለቃ ተብሎ ተጠርቶአል፡፡ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች ከፍ ያለና የላቀ ዕውቀት የነበረው ሰው ነበር፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር ነበር፡፡ የማታ ተማሪ ነበር፡፡ ቀን፣ ቀን የምኵራብ አስተማሪ ኾኖ ብዙ ሰዎችን ያስተምር ስለ ነበረና እርሱ የሚያስተምራቸው አይሁድ ጌታችንን ስላልተቀበሉ በቀን ለመማር አመቺ ጊዜ አልነበረውም፡፡
በአይሁድ ሕግ ጌታን የሚከተልና የሚቀበል ሰው ከምኵራብ ይባረር ስለ ነበረ እነርሱን ላላማስቀየም ኒቆዲሞስ ማታ፣ ማታ ነበር የሚማረው፡፡ ኒቆዲሞስ፡- ‹‹ከሰው ችሎታ በላይ የኾኑ ተአምራትን ስለምትሠራ እኛን ለማስተማርና ለመምከር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከህ የመጣህ ነህ›› ብሎ ለጌታችን መስክሮለታል፡፡ ጌታችንም፡- ‹‹እናንተን ለማስተማር እንደ መጣሁ ከተረዳህ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም›› አለው፡፡
ኒቆዲሞስ ስላልገባው ‹‹እኔ አርጅቼአለሁ፤ እንዴት ነው ወደ እናቴ ማኅፀን ተመልሼ የምገባውና ዳግም የምወለደው?›› ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታችንም፡- ‹‹ሰው ከሰው ከተወለደ ሥጋዊ ነው፤ የሰው ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለመኾን በመንፈስ መወለድ አለበት፡፡ ከእግዚአብሔር መወለድ ነፋስ ከየት ተነሥቶ ወዴት እንደሚነፍስ እንደማይታወቅ ያለ ረቂቅ ምሥጢር ነው›› አለው፡፡ አሁንም ያ ሊቅ፤ ያ አዋቂ ‹‹አልገባኝም›› አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- ‹‹አንተ የእስራኤል መምህር እና ሊቅ ኾነህ እንዴት ይህን አታውቅም?›› አለው፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የሚወጣ የለም፤ የምናውቀውንም እንናገራለን ካለው በኋላ ጥያቄውን በዚህ ገታ፡፡
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ መማሩ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው፡፡ አይሁድ ወገኖቹ ጌታን ሳይከተሉት እርሱ ግን ጌታን መውደዱ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያመሸው ከጌታ ጋር ነበር፡፡ ባለችው ትርፍ ጊዜው ዅሉ ወደ ፈጣሪው ይሔድ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ቀን ሲያስተምርና ሲደክም ስለሚውል ማታ፣ ማታ ማረፍ ይገባው ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ቤቴ ገብቼ ልረፍ አላለም፡፡ ባለ ሥልጣንና ባለጠጋ ስለ ነበር ደጅ የሚጠናው ሕዝብና መሰል ባልንጀሮቹ ይፈልጉት ነበር፡፡ ይኹን እንጂ ከእነርሱ ጋር አላመሸም፡፡
ከዚህ አባት ታላቅ ትምህርት ልንማር ያስፈልጋል፡፡ እኛ ዛሬ የምናመሸው የት ነው? የምናመሸውስ ከማን ጋር ነው? ምን ስናደርግ ነው የምናመሸው? ኒቆዲሞስ ቤቱ አልነበረም የሚያመሸው፤ ከእውነተኛው መምህር ጋር እንጂ፡፡ ኒቆዲሞስ ጽድቁንና በረከቱን እየያዘ ነበር ወደ ቤቱ ይገባ የነበረው፡፡ እኛ ወደ ቤታችን የምንገባው እየከበርን ነው ወይ? ጸድቀን ነው የምንገባው ወይስ ጐስቁለን?
የዛሬ ዘመን ሰው እየሰከረ፣ እየጨፈረ፣ እየደማ፣ እየቆሰለ አእምሮውን ስቶ ነው ወደ ቤቱ የሚመለሰው፡፡ የሚሞትም አለ፡፡ በቤት ያሉት ወገኖቹም ‹‹እንቅፋት ያገኘው ይኾን? ይሞት ይኾን?›› እያሉ እየተሳቀቁ ነው የሚያመሹት፡፡ ማምሸት እንደ ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ነው እንጂ! ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በማምሸቱ ፈጣሪውን አወቀ፡፡ ጌታን ማወቅ ብቻ ደግሞ አይበቃም፡፡ ማወቅማ አጋንንትም ያውቁታል፡፡ ከመንፈስ መወለድ ያስፈልጋል፡፡
የሰው ልጅ ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ተነጥቆ ነበር፡፡ ጌታችን መጥቶ ዳግም ሰው እስከሚያደርገን ድረስ የሰይጣን ልጆች ኾነን ነበር፡፡ ከዚያም በዐርባና በሰማንያ ቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደናል፡፡ እግዚአብሔርን አባታችን የምንለውም ስለዚህ ነው፡፡ ከእርሱ ከተወለድንና ልጅነትን ካገኘን፣ እንደ ገና ልጅነታችንን እንዳናጣ አክብረን እንያዘው፡፡ መጀመሪያም አላወቅንበትም ነበር፡፡ አዳም ከገነት የሚወጣ አልመሰለውም ነበር፡፡ ሰይጣን አታሎታል፡፡ እኛም እንደ ገና እንዳንታለል ልጅነታችን እንዳይሰረዝ እንጠንቀቅ፡፡
የብዙዎቻችን ልጅነት ዛሬ እየተወሰደ ነው፡፡ ልጅነታችንን እያስነጠቅነው ነው፡፡ እነኤሳው እየነጠቁን ነው፡፡ ብዙዎች እንደ ያዕቆብ ልጅነታችንን ሊወስዱብን አሰፍስፈዋል፡፡ ሰይጣን እንደ አዳም ሊነጥቀን አሰፍስፏል፡፡ ኒቆዲሞስ አርጅቶ ነበር፡፡ በጥምቀትና በንስሐ ግን አዲስ ሕይወትን አግኝቶአል፤ ታድሷል፡፡ ያረጀው ሕይወቱ ለምልሟል፡፡ እኛም ዛሬ በጣም አርጅተናል፡፡ ያረጀው ሰውነታችንን በሥጋውና በደሙ በንስሐ እናድሰው፡፡ ይህ ከኾነ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርሰው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
- ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ሥልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በአዲስ አበባ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ደብር የበላይ ሓላፊ፤ በዚሁ ደብር በአስተዳዳሪነት ባገለገሉባቸው ዓመታት ካስተማሩት ትምህርተ ወንጌል የተወሰደ (መጋቢት ፳፩ ቀን ፲፱፻፹፭ ዓ.ም)፡፡