“ከእንግዲህ በኋላ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠልና ክርስቲያኖችን በጭካኔ መግደል በዝምታ አይታይም” ብፁዕ ሥራ አስኪያጅ

 

                                                       ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን

በካሣሁን ለምለሙ

በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያነጣጠረ ቃጠሎ፣ ዝርፊያ፣ እንዲሁም በክርስቲያኖች ላይ የሚካሔደው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ከእንግዲህ በኋላ በዝምታ ሊታይ እንደማይገባ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ገለጡ፡፡
ለሀገር ብዙ ዋጋ በከፈለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በአማኞቿ ላይ ለበርካታ ዓመታት አረመናዊ ድርጊት በተደጋጋሚ ሲፈጸም ቆይቷል፡፡ እምነትን ትኵረት በማድረግ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከፍተኛ በደል መፈጸሙን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው በተለይም በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በኢሊባቡር እንዲሁም በባሌ ጎባ ችግሩ እጅግ በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ምእመናን በጭካኔ በስለት ታርደዋል ካህናትም ተገድለዋል ብለዋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ዘግናኝ በደሎች ለወደፊቱ የሚፈጸሙ ከሆነ ወደ ፈጣሪ መጮኽ እንደተጠበቀ ሆኖ ከእንግዲህ በኋላ ግን በቤተ ክርስቲያኗም ሆነ በአማኞቿ ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ለመመከት የምንገደድ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲኗም የሚሰማት ካገኘች መጮኽ እስካለባት አካል ድረስ ጩኾቷን ታሰማለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናቸው እየተቃጠለ፤ እምነታቸው እየጠፋ መሆኑን ምእመናን በመገንዘብ ከእንግዲህ በኋላ የተከፈለው ሁሉ መሥዋዕት ተከፍሎ እራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ብፁዕነታቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሥጋ ወደሙ የሚፈተትባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል፤ ካህናትና ምእመናን እንደ ከብት ሲታረዱ ከእንግዲህ በኋላ ዝም ብሎ የሚያይ ምእመን ሊኖር እንደማይገባ ሥራ አስኪያጁ ገልጠው የእስከ አሁኑ ትዕግሥትና ዝምታ ቤተ ክርስቲያንን፣ ምእመናንንና ሃይማኖታችንን በእጅጉ እየጎዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለሀገርና ለወገን ባለውለታ የሆነች ቅድስትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ በዐደባባይ ክብሯ ዝቅ ብሎ የጥፋት ዱላ ሲያርፋባት በጣም ልብ ይነካል፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ ለሀገር ምሶሶ መሆኗ ለመንግሥት ያልተሰወረ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኗና በአማኞቿ ላይ የተቃጣውን እኵይና አርመኔዊ ተግባር በአፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበው፤ ካልሆነ ግን እየታረደና እየተቃጠለ ዝም የሚል ስለማይኖር የከፋ እልቂት እንዳይከተል ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት፣ ሕዝብና ሕግ ባለበት ሀገር ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖችና ካህናት እንደ አውሬ ታድነው በጭካኔ መታረድ የለባቸውም፤ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁ መቃጠል የለባቸውም፤ ምእመናንም ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል የለባቸውም በማለት ብፁዕነታቸው አሳስበዋል፡፡
ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተፈጸመው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት አሥር አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው፣ ካህናትና ምእመናን መታረዳቸው እንዲሁም ሀብት ንብረታቸው መውደሙና መዘረፉ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለመገንባትና ሀብት ንብረታቸው የተዘረፈባቸውን ምእመናን እንደ ገና ለማቋቋም የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳለ የገለጡት ብፁዕነታቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ምእመናን እጃቸውን በመዘርጋት የበረከቱ ተካፋይና የቤተ ክርስቲያኗ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ሀገር የሚገኙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያንና በአማኞቿ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ድርጊት እግዚአብሔር እንዲያርቀው በጸሎት ከማሳሰብ በተጨማሪ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


ምንጭ  ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከነሐሴ16-ጳጉሜ5ቀን 2010ዓ.ም