ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ
፩. በክልል ትግራይ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በክልሉ ከሚገኙት አህጉረ ስብከት ጋር ተቋርጦ የነበረውን መዋቅራዊ ግንኙነት ችግር በውይይት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና ልዑካኑን በአካል ልኮ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ተብለው በሚጠሩበት በማዕከላዊ ትግራይ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሐምሌ ፲፭ እና ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በተከናወነ ሕገ ወጥ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት መፈጸሙን በመገናኛ ብዙኃን ለማወቅ ችለናል፡፡ በመሆኑም በዚህ የዶግማና የቀኖና ጥሰት ተግባር የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት በእጅጉ አዝኗል፡፡
፪. በመሆኑም የተከሰተው የዶግማ፣ የቀኖና እና አስተዳደራዊ ጥሰት አስመልክቶ ተወያይቶ ተገቢውን ለመወሰን ለሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪ ተላልፏል፡፡
፫. የስብሰባው ቀን ሊራዘም የቻለው በውጭው ክፍለ ዓለማት ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት መገኘት ስላለባቸው የጉዞ ቀኑ እንዳያጥር እና በሀገር ውስጥ የሚገኙትም ሊቃነ ጳጳሳት ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት ለአገልግሎት ወደ አህጉረ ስብከታቸው የሄዱ በመሆኑ ለመመለሻ የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
፬. በየደረጃ ያሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሥራ ኃላፊዎች እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን ከአሁን ቀደም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በደረሰው ፈተና በኀዘንና በጸሎት ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን በመቆም ላሳያችሁት ጽናት እያመሰገንን አሁንም በደረሰው ፈተና እንዳሁን ቀደሙ ሁሉ በኅዘንና በጸሎት ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ጸንታችሁ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
፭. በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ተገቢውን ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በትግዕሥት እንድትጠብቁ እናሳስባለን፡፡
፮. ምንም እንኳን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ ጥሪው በደብዳቤ የተላለፈ ቢሆንም የመልእክቱ በፍጥነት መድረስ ካለው ስጋት አንጻር የችግሩን ተደጋጋሚነትና አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ እስከ ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ድረስ ተጠቃላችሁ ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ እንድትመጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
፯. ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ሚዲያዎችና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ይህን መልዕክት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን መልእክቱን በማስተላለፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በቤተ ክርስቲያናችን ስም እንጠይቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
ምንጭ: ኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ