ቅዱስ ኤፍሬም

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሐምሌ ፲፬፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ወርኃ ክረምትን እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? ዘመናዊ ትምህርት ተጠናቆ አሁን ዕረፍት ላይ እንደመሆናችሁ መጠን ጊዜያችሁን በተገቢው መንገድ እየተጠቀማችሁበት እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን! በጥሩ ውጤት ከክፍል ክፍል እንደተዘዋወራችሁም ተስፋ አለን፡፡ አሁን ደግሞ ለቀጣይ የትምህርት ዘመን የማጠናከሪያ ትምህርት እየተማራችሁ ያላችሁ ትኖራላችሁ! መልካም ነው!

ሌላው ደግሞ ልጆች ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በሰንበት ትምህርት ቤት በመመዝገብ መንፈሳዊ ትምህርት ልትማሩ ያስፈልጋል፤ ይህን የዕረፍት ጊዜያችሁን እንዲሁ በጨዋታ ብቻ እንዳታሳልፉት! የአብነት ትምህርት፣ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲሁም የሥነ ምግባር ትምህርት ልትማሩ ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ የምንነግራችሁ የቅዱስ ኤፍሬምን ታሪክ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው በሶርያ አገር ነው፤ ቤተሰቦቹ ስለክርስትና እምነት አያውቁም ነበር፤ አባቱ ክርስቶስን የማያመልክ የጣዖት ካህን ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነትም የንጽቢን ጳጳስ ወደ ሆነው ወደ አባ ያዕቆብ በመሄድ የክርስትናን ትምህርት ተምሮ ተጠመቀ፤ ከዚያም በጾም በጸሎት ለብዙ ዘመናት ይተጋ ነበር፤ ይጾማል፤ ይጸልያል፤ መልካም ነገር ያደርጋል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ኤፍሬም በጣም ትጉህ ነበር፤ ለመማር፣ ለማወቅና ለመረዳትም ይተጋ ነበር፤ አንድ ቀን ምን ተከሠተ መሰላችሁ! ቅዱስ ኤፍሬም ተኝቶ ሳለ በሕልሙ የብርሃን ምሰሶ (ዐምድ) ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ተመለከተ፤ ከዚያም እግዚአብሔር የዚህን ምሥጢር ይገልጥለት ዘንድ በጾምና በጸሎት ጠየቀ፤ ከዚያም አምላካችን ‹‹እንደ ምሰሶ (ዐምድ) ያየኸው በቂሳርያ አገር የሚኖር ባስልዮስ የሚባል ቅዱስ አባት ነው›› አለው፡፡

ቅዱስ ኤፍምም ቅዱስ ባስልዮስን ሊያየው (ሊያገኘው) ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ለቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬም እንደሚመጣ ገለጸለት፤ ከዚያም ተገናኙ፤ ይገርማችኋል ልጆች! የሁለቱም አገር ሁለቱ የሚናገሩትም ቋንቋ የተለያየ ስለነበር በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም ቅዱስ ባስልዮስ የየራሳቸውን ቋንቋ እንዲገልጽላቸው ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ገለጸላቸውና ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ፡፡ ከዚያም ቅደስ ባስልዮስ ዲቁናን ቀጥሎም ከጥቂት ወራት በኋላ ቅስናን ሾመው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን በጣም ይወዳት ስነበር ያመሰግናት ነበር፤ ሁል ጊዜም ይማጸናት ነበር፤ ከዚያም እመቤታችን ተገለጠችለትና የማስተዋል ጥበብን ሰጠችው፤ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ደረሰ (ጻፈ)፤ ታደያ ከነዚህ ብዙ መጻሕፍት መካከል አንዱ እኛ ሁል ጊዜ የምንጸልየው ውዳሴ ማርያም ነው፤ ልጆች ውዳሴ ማርያም ከጸሎት በተጨማረም በውስጡ በርካታ ትርጉሞች (ምሥጢር) ያለበት መጽሐፍ ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን በማመስገኑ ምሥጢሩ ጥበቡ ማስተዋሉ ተገለጠለት፤ እመቤታችንን ለማመስገን መጽሐፉን ስንገልጥ ሁል ጊዜ እርሱም ይታሰባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ኤፍሬም አባታችን የእመቤታችንን ውዳሴ በሰባቱ ዕለታት ከፋፍሎ በእመቤታችን ዕድሜ ልክ ፷፬ (ስድሳ አራት) ጊዜ (በዚህ ምድር በኖረችበት ፷፬ ዓመት) ‹‹ቅድስት ሆይ ለምኝልን›› እያለ ተማጽኗታል፤ እኛም እርሱን አብነት አድርገን በውዳሴ ማርያም እናመሰግናታለን፤ እርሷም ትባርከናለች፤ ማስተዋሉን ጥበቡን ትሰጠናለች፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሳን እመቤታችንን ቢያመሰግኗት የሚመሰገኑ እነርሱ እንደሆኑ ስለተረዱ ሁሌ ጠዋት ማታ ስሟን ይጠራሉ፤ እኛም ውዳሴዋን እየደገምን ‹‹ቅድስት ሆይ ለምኝልን›› ብንል እንባረካለን፤ እንቀደሳለን እንጂ ለእመቤታችን የምንጨምርላት ምንም ነገር የለም፤ ማመስገናችን ቅዱስና ክቡር ስሟን መጥራታችን እኛው እንድንከብር እኛው እንድንቀደስ ነውና ሁሌ እንጸልይ! እናመስግን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በክረምቱ! በእግዚአብሔር ቸርነት የተዘራው እህል በቅሎ (አቆጥቁጦ) ምድር ድርቀቷ ተወግዶ በአረንጓዴ ለምለም የምታጌጥበት ወቅት ነው፤ ለምድር ዝናምን ሰጥቶ በዝናብ አብቅሎ፣ በነፋስ አሳድጎ በፀሐይ አብስሎ ፍጥረታቱን የሚመግብ እግዚአብሔርን ቸርነቱን እያስታወስን ለምስጋና በጸሎት መትጋት አለብን፤ የቅዱስ ኤፍሬምን ታሪክ እንዳነበብነው የሚፈልገው ነገር እንዲደረግለት በጸሎት ይተጋ ነበርና፡፡

ሌላው ደግሞ ለማወቅና ለመረዳት ይተጋ ነበር፤ እኛ አንድን ነገር ለማግኘት ሳንሰለች መትጋት ይኖርብናል፤ ቅዱስ ኤፍሬም ከቅዱስ ያዕቆብ እንዲሁም ከቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ በመሄድ ያላወቀውን በመጠየቅ ተማረ ቡራኬን ከአባቶቹ ተቀበለ፡፡ አያችሁ ልጆች! አባቶችን ማክበር ከአባቶች ዘንድ ሄዶ መጠየቅ መረዳት መማር ብልህነት ነው፤ አስተዋይ ያደርጋል፤ ማስተዋል ጥበብን እንድንይዝ ያደርገናልና፡፡

ቤተ ክርስቲያን በመሄድ አባቶቻችንን እንጠይቅ፤ ከእነርሱም እንባረክ፤ ያኔ መልካምና ቅን፣ ታታሪና ጎበዝ እንሆናለን በጸሎትና በጾም ስንበረታ ደግሞ እግዚአብሔር ድካማችንን አይቶ የምንፈልገውን ይሰጠናል፡፡ ሌላው መዘንጋት የሌለብን ነገር በዚህ የዕረፍት ጊዜያችን ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ ለጸሎት፣ ለቅዳሴ መትጋት አለብን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከቅዱሳን ከአባቶቻችን የምንማራቸውን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም በሕይወታችን መተግበር አለብን፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ያልተረዳንን በመጠየቅ፣ በጾም በጸሎት በመትጋት ከእኛ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖቸ እንዴት ይኖሩ እንደ ነበር ጠይቀን በመረዳት እንደነርሱ ልንሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምና ቅዱስ ባስልዮስ የእግዚአብሔር ሰዎች ስለነበሩ አንዳቸው የሚናሩትን አንዳቸው ይረዱ ነበር፤ ተግባብተውና ተዋደው የቦታ ርቀት ሳይወስናቸው የሚናገሩትም ሆነ የቋንቋ ልዩነት ሳይፈጥርባቸው በፍቅር ተግባቡ አብረውም ኖሩ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ያረፈው በሐምሌ ፲፭ (ዐሥራ አምስት) ቀን ነው፤ በረከቱ ይደርብን!

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እኛም መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር ተግባብተን መኖር ይገባናል፤ ሁሉን ስንወድና ስናከብር እግዚአብሔር እኛን ያከብረናል፤ ሌላው ደግሞ ያወቅነውን ለሌሎች ማሳወቅ፣ ሰዎችን በጸሎት መርዳት፣ ስለ እውነት መመስከር አለብን!

አምላከ ቅዱስ ኤፍሬም በረከቱን ያድለን፤ አሜን!!! ቸር ይግጠመን! ይቆየን !!!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘሐምሌ ፲፭

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!