በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
፩.የ፳፻፲፬ ዓ.ም. የግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ መክፈቻ ንግግር በቤተ ክርስቲያናችንና በሀገራችን የተከሰተውን የሰላም እጦት ተከትሎ የደረሰው የሰው ሕይወት ኅልፈትና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል የካህናትና የምእመናንን ኅልፈተ ሕይወት ላይ ያተኮረ ሲሆን በዚሁ ላይ የተነጋገረው ምልዓተ ጉባኤ በሰፊው ተነጋግሮ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
፪.የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተከናወነው የመንፈቅ ሪፖርት፣ ምልዓተ ጉባኤ ያዳመጠና የገመገመ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ ተወስነው ፍጻሜ ያላገኙ ጉዳዮች አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ፍጻሜ እንዲያገኙ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
፫.ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ፣ በችግሩ ዙሪያ የተነጋገረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአሁኑ ደረጃ በሀገራችን ያለው የሰላም እጦት ላይ በሰፊው ተወያይቶ በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ተነጋግሮ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል፣ ቤተ ክርስቲያናችን የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
፬.ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችንና በካህናት አገልጋዮቻችን እንዲሁም በምእመናኖቻችን ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የበዓል ማክበሪያ ቦታዎች መነጠቅ አስመልክቶ ጉባኤው የተነጋገረ ሲሆን አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በቀጣይም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግልን በመጠየቅ፣ እስከአሁን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ደረሰ የተባለው ችግር በዓይነትና በቁጥር ተለይቶ ለሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
፭.በሀገራችን በተከሰተው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ለተፈናቀሉና ለተሰደዱ ወገኖች፣ ለፈረሱና ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋሚያ፣ ለተዳከሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች መደጐሚያ የሚሆንየገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
፮.በክልል ትግራይ የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያኒቱን አስመልክተው በ ፴/፬/፳፻፲፬ እና በ፫/፮/፳፻፲፬ ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ምልዓተ ጉባኤው ገምግሞ በቀጣይ የክልሉ አባቶች በማዕከል እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው ለሀገር አንድነትና ሰላም በጋራ እንዲሠሩ ምልዓተ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
፯.ቤተ ክርስቲያናችን በዘመናት በርካታ የልማት ተግባራትን ስታከናውን የቆየች ቢሆንም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ማዕከል ሳታቋቁም መቅረቷ ተገቢ አለመሆኑን በመገምገም፣ በቀጣይ የሕክምና ማዕከሉ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲገነባ ጉባኤው ወስኗል፡፡
፰.በየሦስት ዓመቱ የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አስመልክቶ በተደረገው ምርጫ፡-
፩. ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሰሜን አሜሪካ ኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣
፪. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕርዳር ከተማ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጐ በመምረጥ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ ሰይሟል፡፡
፱.በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጉባኤ ላይ በቆየባቸው ቀናት ባደረገው ሰፊ ውይይት፡-
ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት መጠናከር፣ ለሀገራችን፣ ለሕዝባችንና ለመላው ዓለም ሰላም መገኘት፣ ለተሰደዱና ከቄያቸው የተፈናቀሉ መረጋጋትና ወደቄያቸው መመለስ፣ በሀገራችን ጦርነትና የሰላም እጦት በሚወገድበት ሁኔታ በሰፊው በመምከርና ለዘለቄታዊ ሰላም አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በመሆኑም መላው ሕዝባችንና የመንግሥት መሪዎች ሁሉም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ከምንጊዜወም በላይ በአንድነት በመነሳት በትኩረት እንዲሠሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት ፱-፳፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ሲወያይ በመቆየት በዛሬው ዕለት ስብሰባውን በጸሎት ዘግቷል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት