‹‹ከአነጋገርህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከአነጋገረህ የተነሣ በቃልህ ይፈረድብሃልና›› (ማቴ. ፲፪፥፴፯)
የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በአንደበታችን የምንናገረው ነገር መልካም ሲሆን ጽድቅ ሆኖ እንደሚቆጠርልን ሁሉ መጥፎ ከሆነ ደግሞ ኃአጢት ይሆንና በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ ያደርገናል፡፡ ኃጢአት በአብዛኛው ከንግግር የሚመነጭ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ‹‹ከአነጋገርህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከአነጋገረህ የተነሣ በቃልህ ይፈረድብሃልና።›› ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከት ውስጥ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቈጣ ሁሉ እርሱ ይፈረድበታል፤ ወንድሙንም ጨርቅ ለባሽ የሚለው በአደባባይ ይፈረድበታል፡፡›› (ማቴ. ፲፪፥፴፯፣፭፥፳፪)
ከስድብ እና ከሐሰት፣ ከየማይረባ እና አሳች ከሆኑ ንግግሮች ጨምሮ ከአንደበታችን ከሚወጡ ኃጢአቶች ልጠንቀቅ እንደሚገባ ጌታችን ኢየሱስ አስተምሮናል፡፡ አስከፊ በሆነ ድምፅ ሰዎችን መናገር እንዲሁም ቁጣና ጭካኔ የተሞላባቸው ቃላት እና ግብታዊ ንግግሮች፣ የማስፈራራት ቃላት፣ የሐሰት ምስክርነት እና በሐሰት መማል ሁሉም በአንደበት የምንሠራቸው ኃጢአቶች ናቸውና ከአንደበታችን ሊወጡ አይገባም፡፡
በአንደበታችን የምንሠራው ኃጢአት በልብ እና በምላስ የሚተገበር ድርብ ኃጢአት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላልና፤ ‹‹መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል፤ ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገራልና፡፡›› የምንናገረው ቃል በሌሎች ላይ ተጽእኖ አለው፤ ስለዚህም ከአንደበታችን የምናወጣው ቃል በማስተዋል መሆን አለበት፡፡
ፈሪሳውያንም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው ‹‹ደቀ መዝሙርህ የሽማግሌዎች ሥርዓት ለምን ይተላለፋሉ? እንጀራ በሚበሉበት ጊዜ እጃቸውን አይታጠቡምና ብለው›› በጠየቁት ጊዜ ጌታችን እንዲህ ብሎ መልሶላቸዋል፡፡ ‹‹…ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባው አይደለም፤ ከአፍ የሚወጣው ሰውን ያረክሰዋል እንጂ።›› ፈሪሳውያኑ ግን አንጎራጎሩ፤ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ምሳሌውን ተረጒምልን›› አለው፡፡ ጌታችን እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እናንተም ገና ይህን አላስተዋላችሁምን? ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚወርድ፥ ወደ ውጭም እንደሚወድቅ አታውቅምን? ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው፡፡ ከልብ ክፉ ዐሳብ ይወጣልና፤ ይኸውም መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ ስርቆት፣ በሐሰት መመስከር፣ ስድብም ነው፡፡ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ሰውን አያረክሰውም፡፡›› (ሉቃ. ፮፥፵፭፣ ማቴ. ፲፪፥ ፴፭-፴፮፣ ፲፭፥፲፩-፳)
በሐዋርያው የያዕቆብ መልእክት ‹‹እንዲሁ ምላስም ትንሽ አካል ናት፤ ታላላቅ ነገርንም ታመጣለች፤ እነሆ፥ እጅግ ትንሽ የሆነች እሳትም ይህን የሚያህል ጫካ ታቃጥላለች፡፡ ምላስም እሳት ናት፤ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት፤ ሥጋችን ትበላዋች፤ ውስጣዊ ሰውነታችን ትጠብሰዋለች፤ ከገሃነም ይልቅ ታቃጥላለች፡፡ የአራዊትና የወፎች፥ የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ ለሰው ይገዛል፤ ተገዝቶአልም፡፡ የሰውን ምላስ ግን መግዛት የሚቻለው የለም፤ ክፉ ናት፤ ዐቅምም የላትም፤ የሚገድል መርዝንም የተመላች ናት፤ በእርስዋ እግዚአብሔር አብን እናመሰግነዋለን፤ በእርስዋ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰውን እንረግመዋለን፡፡ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቻችሁን ሆይ፥ እንዲህ አይሁን›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡(ያዕ. ፫፥ ፭-፲)
ብዙ ሰዎች የወደቁባቸው ኃጢአቶች ሐሜት እና ሐሰት ናቸው፡፡ ሰዎች ሌሎች በሌሉበት ጊዜ ስለ አንድ ሰው በፊቱ ልንናገረው የማንችለውን ነገር ማውራት ሐሜት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሐሜት ይወዳሉ፤ በትንሽ ትልቁም ሰበብ እያደረጉ ስለ ሰዎች መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር ያወራሉ፤ በእነርሱም ላይ ያሾፋሉ፤ ያንቋሽሻሉ፤ ድክመታቸውን አጋነው ያወራሉ፤ እንዲህ በማድረግም ሙገሳንና ክብርን ከሌሎች ይጠብቃሉ፡፡ በመጀመሪያ ስለ ሰው በአሉታዊ መንገድ ማውራት ሐሜት እንደሆነና እግዚአብሔር አምላክ የሚጠላው ነገር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም ሐሜትን የለመደ ሰው ከማኅበራዊ ሕይወቱ ጋር የተቆራኘ ባህል ወይንም ሥርዓት አድርጎ በማሰብ ኃጢአትን መሥራታቸውን የሚዘነጉ ሰዎች ወይንም ኃጢአት መሆኑን የማይቀበሉ ሰዎች በርካታ ናቸው፤ ሐሜት የተወገዘ ኃጢአት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንደጠቀሰ ተመልክተናል፤ ስለዚህም ያስጠይቀናል፤ ሰውን ማማት ኃጢአት ወንጀል ነውና ከአንደበታችን ስለሚወጡ ቃላት እንጠንቀቅ!
አምላካችን እግዚአብሔር ሐሰተኛ ምላስን አጥብቆ እንደሚጠላ መጽሐፈ ምሳሌ ላይ ተመዝግቦ እናገኘዋለን፤ እግዚአብሔር አምላክ የሚጠላቸው ስድስት ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ …ሐሰተኛ ምላስ፣…ክፉ ዐሳብን የሚያበቅል ልብ፣ ሐሰተኛ ምስክርን የሚያቀጣጥል….›› (ምሳ.፮፥፲፮-፲፱)
የሌላ ሰውን ስም በተሳሳተ መንገድ ማንሣትና በእርሱ ላይ መመስከር ኃጢአት ነው፡፡ የኩራት እና ራስን የማመጻደቅ ቃል ሁሉ ከኃጢአተኞች አንደበት የሚወጡ ናቸው፡፡ ሐሜተኛ ሰዎች ስለሌሎች ሰዎች ዓለማዊ ሕይወት የማወቅ ጉጉታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ስለ እነርሱ አጥብቀው ይጠይቃሉ፤ ‹‹እርሱ/ እርሷ ወዴት ሄዱ? እርሱ/ እርሷ ማንን አገኘች? እርሱ/ እርሷ የተናገረችው ምድንነው? እነዚህ ሰዎች ስለሚያሙት ሰው መረጃን በሁለት መንገዶች ለመምጠጥ የመሞከር ፍላጎት አላቸው፤ ወይ ስለ አንድ ነገር ወይም ስለ አንድ ሰው ለማወቅ ይጠይቃሉ ወይንም ይከታተሏቸዋል፡፡ ወዴት ሄደ? ከማን ጋር ተገናኘ? ከማን ጋርም ተነጋገረ? ስለ እነርሱ ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ሰዎቹ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ ይህንም የሚያደርጉት ምድራዊ ደስታን ለማግኘት ከሰዎች ጥቅምን በመፈለግ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ሁሉ ራሳችሁን ለዩ! ሐሜተኛ ሰው የሚሰጠው መረጃ የሰማውንና ያልተጣራ ወሬ በመሆኑ እንዲሁም ምንጮቹ ሐቀኛ ባለመሆናቸውም እውነት መናገሩን በምንም ማረጋጥ አይቻለንም፡፡
በጎ ሰው ወይንም ክርስቲያን ግን ሰውን አያማም፤ እውነትንም ለመከተል የሚሻ በመሆኑ ሐሰትን አይናገርም፤ ጊዜውንም ስለሚያከብር በከንቱ ስለሌሎች በማውራት አያባክነውም፤ ለንግግሩም ትኩረት በመስጠት እውነትን ይናገራል፤ ጊዜውን የሚያከብር ሰው ስለ እያንዳንዱ ደቂቃ ያስባል፡፡ ከሰዎች ጋርም ለመግባባት ትርጉም ያላቸውን ቃላቶች ይጠቀማል፤ የሰዎችን ድክመት ስሕተት በአዳባባይ አይዘረዘርም፡፡ ሐሜተኞች ግን ራሳቸውን ፈራጅ አድርገው በከንቱ ይናገራሉ፤ ለሰዎች ስሜት መጎዳት አይጨነቁም፤ አግባብ የሌለው ንግግርም ያዘወትራሉ፡፡
ሰዎችን አሻሚ በሆነ ትምህርት ወይም የተሳሳተ ምክር በመስጠት ሌሎችን የሚያሳስቱ ሰዎች ብዙ ናቸው። ራሱ ኃጢአተኛ የሆነ አስተማሪ የእርሱን ትምህርት የተቀበሉትን ሁሉ ያሳስታል፤ ወይም ‹‹የሌሎችን ሐሳብ ወይንም አሳሳች ሐሳቦቹን በሕይወቱ ስለሚተገብራቸው ዕድሜውን በሙሉ ኃጢአት ስሚሠራ ሥርየትን ሳያገኝ ይሞታል፤ ስለዚህ ይፈረድበታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ ብሏል ‹‹ወንድሞቼ ሆይ፣ ከመካከላችሁ መምህራን ብዙዎች አይሁኑ፤ ጽኑ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁና፤ ሁላችንም እጅግ እንስታለንና፤ በቃል የማይስት ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው›› እንዲል፡፡ (ያዕ. ፫፥ ፩-፪)
ከዚህ በተጨማሪም አንዳንዶች ከወደቅንባቸው ኃጢአቶች መካከል ግነት ነው፤ ማጋነን እውነት ከሆነው መረጃ ሐሰትን ጨምሮ የማቅረብ ነገር ስለሆነ ወደ ኃጢአት ያመራል፡፡ ከንግግር መካከል እውነቱን መለየት ያስፈልገናል፡፡ ስለሰዎች ማውራት ዋጋ ወይንም ትርጉም የሌለው ነገር ነው፡፡
በብዛት የሚቆጠሩ ሰዎች በተመሳሳይ በኃጢአት ይወድቃሉ፡፡ እውነትን ከመናገር ይልቅ የሐሰትን ንግግር ይመርጣሉ፤ ከዚህም ባሻገር ጥቅም የሚያስገኝላቸው ነገር ከሆነ ወይንም መስሎ ከተሰማቸው ያላዩትንና ያልሰሙትን ነገር አይቻለሁ እና ሰምቻለሁ ብለው ስለሌሎች ይመሰክራሉ፡፡ በሐሰት መመስከር የሰዎችን ሕይወት እስከ ማቃወስና ለከባድ ወንጀልም እንዲሁም ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁሉ ኃጢአት በመሆኑ በአንደበታችን ኃጢአት ከመሥራት እንቆጠብ፤ ሰዎችን አምተን፣ በሰዎች ላይ በሐሰት መስክረን ወይንም ሐሰት አውርተን ከሆነም ንስሓ መግባት ይጠበቅብናል፤ ካልሆነ ግን ለዘለዓለም ይፈረድብናል፡፡