ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የተውጣጡ ሰልጣኞች ተመረቁ፡፡
በፈትለወርቅ ደስታ
የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ባዘጋጀው ስልጠና ከተለያዩት ቦታዎች የመጡ 27 ሰልጣኞች ለሁለት ሳምንት የቆየ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ተመረቁ፡፡
የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪ ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን እንደገለፁት ይህ ሥልጠና ለ13ኛ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን ከዚህ በፊት በተካሄዱት 12 ዙር ስልጠናዎች 219 ሰልጣኞች ስልጠናውን ተከታትለዋል፡፡ ስልጠናውን ከወሰዱት በጠረፋማ ቦታዎች ከሚኖሩት ብሔረሰቦች ውስጥ ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከደቡብ ኦሞ፣ ከጂንካ፣ ከሰመራ፣ ከአላባ፣ ከጠምባሮ፣ ከስልጤና ከጉራጌ ዞኖች የተውጣጡ እንደነበሩ አስታውሰው በአሁኑ መርሐ ግብር ስልጠናውን የወሰዱት ከሱማሌ፣ ከቦረና፣ ከጉጂና ሊበን ዞኖች የመጡ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ስልጠና ስለ ስነ ፍጥረት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ክርስትያናዊ ሥነ ምግባር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የስብከት ዘዴ በሚሉ ርእሶች ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪ ሰልጣኞቹ ታሪካዊ ቦታዎችንና ሙዚየሞችን በቆይታቸው ወቅት ጎብኝተዋል፡፡
የሰልጣኞቹ ተወካዮች እንደገለጹት “በሚኖሩበት ጠረፋማ አካባቢ ያሉ ምእመናን በመናፍቃንና በአሕዛብ የተከበቡ ሲሆን መናፍቃን በገንዘብና በስልጣናቸው በመጠቀም የተለያዩ ስልጠናዎችን እያዘጋጁ አብዛኛውን ምእመን በቋንቋቸው እያስተማሩ ወደ መናፍቅነት እየለወጧቸው እንደነበርና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ምንም አይነት ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ ሕብረተሰቡ በባእድ አምልኮ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፤ የአካባቢው ምዕመናን መጠመቅ እንደሚፈልጉና ቤተክርስቲያንም ተሠርቶላቸው ቅዳሴ የሚያስቀድሱበት፣ ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት፣ ጸሎት የሚያደርሱበት፣ ወንጌልን የሚማሩበት በአጠቃላይ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽሙበት ቤተክርስቲያን እንዲሰራላቸው ለቤተክርስቲያን ልጆች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ሰልጣኞቹ በስልጠናው በቆዩበት ወቅት ለምግብ፣ አልባሳትና ለመጓጓዣ 50.000.00 ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ ገንዘብ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ክፍልና አውሮፓ ባሉ በጎ አድራጊ ምእመናን የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቀሲስ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የአሁኑን ጨምሮ በአጠቃላይ 246 ሰልጣኞች እንደተመረቁ ገልጸው ሰልጣኞቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ መጻሕፍት፣ አልባሳት፣ ትራንስፖርት በተደጋጋሚ ስልጠናና ድጋፍ እንደሚያስፈለጋቸው፣ ወደ ተለያዩ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋማት እየመጡ የሚሰለጥኑበትና ሃይማኖታቸውን የሚያጸኑበት መንገድ ለመፈለግ የብዙ ምእመናን ድጋፍና ርብርብ አስፈላጊ በመሆኑ እውቀት ያለው በእውቀቱ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ እንዲሁም በጸሎት ቤተክርስቲያንን መደገፍና የተሰጠውን ኃላፊነት እያንዳንዱ ምዕመን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀትና ለወደፊት እውቀታቸውን ለማዳበርና ለአገልግሎት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱስንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የተዘጋጁ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ትውፊትና የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚያስረዱ መጽሐፍትና ሌሎች አጋዥ ጽሑፎች ተሰጥቷቸዋል፡፡
የማኅበሩ ዋና ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለሰልጣኛቹ ባስተላለፉት መልእክት ማኅበሩ ወደ ፊት በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ቋንቋ ስልጠና እንደሚሰጥና አሁን ግን ሠልጣኞቹ የሰለጠኑትን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ በቋንቋቸው እየተረጎሙ ማስተማር እንዳለባቸውና በጾምና በጸሎት በሕይወት በመተርጎም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባቸውና ማኅበሩም በየጊዜው የማሻሻያ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጸው መርሃ ግብሩን በጸሎት ዘግተው ፍጻሜ ሆኗል፡፡