ከምርጫው ይልቅ ለቅድመ ምርጫው!!
መስከረም 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ያህል ዘመን ተጉዛ ከዚህ የደረሰችው በተአምር ብቻ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ በጽኑ እምነትና ምግባር እግዚአብሔርን በማመስገንና ሰውን በማገልገል የታወቁ እልፍ አእላፍ ቅዱሳን ካህናትና ምእመናን በውስጧ በመኖራቸው ነው፡፡ በእነዚህ ቅዱሳን አበው በየቦታው ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉና መጻሕፍትም እንዲበዙ የተደረገውም ጥረት ለዚህ ታሪካዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ የታሪክ ትዝታ ብቻ ሳይሆን አሁንም በተግባር የሚታይ ሐቅ ነው፡፡
በዚህ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ሢመተ ጵጵስና በኢትዮጵያ የክርስትና ሕይወት መንፈሳዊና ማኅበራዊ የታሪክ ጉዞ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ በአራተኛው ምዕት ዓመት ሀገራችን የሙሉ ምሥጢረ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት በመሆን ፍጹም በረከተ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለች፡፡ በዚህም ወቅት ዛሬ ያለችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ተቋቋመች፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቀለምና ብራና እንደ ቃልና አንደበትም ተዋሕደው “ከኀይል ወደ ኀይል” ከክብር ወደ ክብር፣ ከበረከትም ወደ በረከት ሲጓዙም ኖረዋል፡፡ እንደገናም “በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀበልን” እንደተባለው ከ1951 ዓ.ም. አንሥቶ ላለፉት 53 ዓመታት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት የምናከብረውን ፓትርያርካዊ ክብር ተጎናጸፈች፡፡ አክሊለ በረከትን ተቀዳጀች፤ ፓትርያርካዊ በትረ ክህነትን ጨበጠች፤ መንበረ ፓትርያርክንም ዘረጋች፡፡ ይህን የረጅም ጊዜ ጉዞ ስንመለከት የቤተ ክርስቲያናችን ዕድገትና ልዕልና በከፍተኛ ጥረትና መሥዋዕትነት የተገኙ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ምን ጊዜም አገልግሎቷን ሳታቋርጥ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን ስታበረክት ኖራለች፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ያለች እንደመሆንዋ በዚህ ጉዞ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከተፅዕኖ ነጻ አልነበረችም፡፡ በእግዚአብሔር ኀይል ያጋጠሟትን ፈተናዎች እየተቋቋመች እዚህ ደርሳለች፡፡
ከዚህ ተጨባጭ ሐቅ ስንነሣ ያካሄድናቸው ሢመተ ፕትርክናዎች ሁሉ በተቀመጠው ቀኖናዊ አግባብና በሚፈለገው አቋምና ብቃት ሥሉጣን /የተፋጠኑ/ ሆነው የተጓዙ ነበሩ ብለን በሙሉ ድፍረት መናገር አንችልም፡፡ በርግጥ በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም የሰው ልጆች ከመካከላቸው ብልጫ ያለውን ሰው ለከፍተኛ ሓላፊነት ይመርጣሉ፡፡ አንዱን ሰው ከሌላው የበለጠ የሚያደርገው ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያለው ቅንና ቆራጥ አስተሳሰብ፣ አቅም ያለው የሥራ አፈጻጸምና የመሳሰለው መልካም ሥራ ሚዛን ሲደፋ እንደሆነም እንገነዘባለን፡፡
በዕለታዊ የሥራ አፈጻጸምና በማኅበራዊ አገልግሎት ከሁሉ የበለጠ አስተዋፅኦ በማድረግ የተመሰከረለትን ሰው ለከፍተኛ ሓላፊነት መምረጥ ተመራጩን ለመጥቀም ሳይሆን ሥራውን በማክበር ተገልጋዩን ወገን በበለጠ ለማገልገል ነው፡፡ ይህም የመራጮችን አስተዋይነትና ለትክክለኛ ዓላማ የቆሙ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ የተጓዝንበትም መንገድ መመዘን ያለበት አንዱ ከዚህ መሆን እንደአለበትም እናምናለን፡፡
ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋት ፓትርያርክ ምን ዓይነት አባት ነው የሚለው ጥያቄ የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ቢሆንም ይህን ጥያቄ ሊመልስ የሚችለው ምርጫው በራሱ ሳይሆን የምርጫው መደላደል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከምርጫው ይልቅ ለቅድመ ምርጫው ቅድሚያ መስጠት የወቅቱ ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡
በቅዱስ ሲሄዶስ መሪነት፣ ሊቃውንት ካህናትና ምእመናን በነጻ አሳብና በመንፈሳዊ ትብብር እየተመካከሩ ያለምንም አድልዎና ተፅዕኖ መንፈሳዊ አባታቸውን መምረጥ እንዲችሉና ተመራጩም የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ሳይነሣበት ቤተ ክርስቲያኒቱን በሰላምና በአንድነት እንዲመራ ከምርጫው ይልቅ አሁንም ለምርጫው የሚያስፈልጉ መደላድሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል እንላለን፡፡
ከእነዚህም መደላድሎች ውስጥ ዋናዎቹ ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው የአራተኛውን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን መሰደድና የአምስተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ሢመተ ፕትርክና ተከትሎ የተከሰተው የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተጀመረው ቤተ ክርስቲያንን አንድ የማድረግ ጥረት በእርቀ ሰላም እንዲቋጭ ተገቢውን ርብርብ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በሁለቱ አባቶች መካከል ተፈጥሯል የተባለው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ችግር በቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት በመዋቅራዊ አካላቷ ተቋማዊ አሠራር እንዲፈታ መደረግ አለበት፡፡
ሁለተኛው የቅድመ ምርጫ መደላድል፤ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማውጣት ወይም ማሻሻል የሚያስፈልግ ከሆነ ተገቢነታቸው በሊቃውንቱ ተሳትፎ እየተጠና ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው በቅዱስ ሲኖዶስ እየተወሰነ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው መደላድል ደግሞ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ድርጅታዊ አወቃቀር ለማሻሻል የቀረቡና የሚቀርቡ ጥናቶችን በማዳበር የለውጥ ሂደቱን ለመምራት የሚችልና መንፈሳዊነት ሞያዊነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሐዊነት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአሠራር መርሕ መሆኑን በተጨባጭ ሊያረጋግጥ የሚችል የቴክኒክ ኮሚቴ በይፋ ማቋቋም ነው፡፡
የእነዚህ ሦስት መደላድሎች መቅደም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ነጻነት ከማጎናጸፍና የተለያዩ ሕገ ወጥ ቡድኖችን በዘለቄታዊነት ከአስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲታቀቡ ከማድረጋቸውም በላይ የተከፈለችውን አሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ወደ አንድነት ይመራል የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡
ስለሆነም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ምሁራን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ደቀ መዛሙርትና ልዩ ልዩ ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያኒቱ እግዚአብሔር ጥሩ መሪ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጀውን የሁለት ሱባኤ ጸሎተ ምኅላ ከመፈጸም ጎን ለጎን ለመደላድሎቹ ስኬት ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻርም የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አንዳንድ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል ያስፈልጋል፡፡
ከዚሁ ጋር ለእነዚህ ሕገ ወጥ አካሄዶች ሽፋን የሚሆኑና በመሠረቱም ተገቢም ትክክለኛም ያልሆኑ መግለጫዎች፣ ቃለ ምልልሶችና ጽሑፎች እንዲታረሙና በቀጣይም እንዲቆጠቡ መደረግ ይኖርበታል እንላለን፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ለምርጫው ሳይቸኩል ለቅድመ ምርጫው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ጽኑ እምነታችን ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስምዐ ጽድቅ 19ኛ ዓመት ቁጥር 24 2005 ዓ.ም.