ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት
በለሜሳ ጉተታ
ክርስትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ መንገዱም ደግሞ ወደ ዘላዓለማዊ ክብር የሚያደርስ የሕይወት የድኅነትና የቅድስና መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያን ለመሆን በ፵ እና በ፹ ቀን በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነትን ማግኘት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ ማለትም ነው፡፡ ይህንንም ጌታችን ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› ብሎ ገልጾታል (ዮሐ.፫፥፫)።
ያመነና የተጠመቀ ሰው የእግዚአብሔርን የጸጋ ልጅነት ያገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያንም አባል ይሆናል፡፡ ከክርስቲያን አንድነትም ይደመራል፤ ከዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት ከሥጋዊነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስነት፤ ከውሸት ወደ እውነት እንዲሁም ወደ ዘለዓለማዊነት ክብርና ጸጋ ይሸጋገራል፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት የማደግና የመሸጋገር ሕይወት ነው፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና›› ያለን (ገላ.፫፥፳፯)።
ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን እውነት እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ›› (፩ኛቆሮ.፫፥፲፮)። በመሆኑም ራስን ከማንኛውም ክፋት ርኩስትና ኃጢአት ጠብቆ መኖር የማንኛውም ክርስቲያን ግዴታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ሕይወት ሸክላ ናት፤ ትሰበራለች፤ አሰባበሯ ደግሞ ለዳግም መጠገን (ለመነሣት) ዋስትና ነውና ማንነታችን እንይዳቆሽሽ እንዳንጠፋ እርሱንም እንዳናሳዝን ጥንቃቄን ልናደርግ ይገባል፡፡
ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ሕይወትን በእውነት በአርአያነትና በምሳሌነት እንዲሁም በምግባር የመግለጽና የመኖር ሕይወት ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ›› በማለት (፩ኛ ዮሐ.፫፥፲፰)። የቃልና የአንደበት ሕይወት ሳይሆን የእውነት ሕይወት ነው ኦርቶዶክሳዊነት፡፡ በሃይማኖትና በፍሬ ራስን የመምራት (የመኖር) ሃይማኖትን በምግባር የመግለጥ እውነትን (ሕይወትን) በተግባር የመግለጥ ዓለምና የዓለም የሆኑ ነገሮችን የመጥላት ዘወትር ስለ ነገረ እግዚአብሔር ስለ ቅድስና ሕይወት፤ ስለ ዘለዓለማዊ ጸጋና ክብር እያሰቡ የመኖር ሕይወት ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ሕይወትና እውነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ‹‹እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው›› ያለን (ዮሐ.፮፥፷፫)፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ከኢ-ክርስቲያናው ሥነ-ምግባር ሐሳብ ተግባርና ምኞት እራስን የመጠበቅ ማለትም ከዝሙት፣ ከውሸት፣ ከዘረኝነት፣ ከመከፋፈል፣ ከንፉግነት፣ ከስግብግብነት፣ ከዓለምና ከገንዘብ ፍቅር ተስፋን ከመቁረጥ እምነት ከማጣት ከአላስፈላጊ ደስታና ሀዘን ከቁጣ ከንዴት፣ ከብስጭት፣ ከምቀኝን፣ ከግብዝነት ከኩራት ከትምክሕት እራስን የመጠበቅ የመለየት ሕይወትንም በመልካም ምግባራት እራስን የማስተዳደርና የመምራት ማለትም በፍቅር በሰላም በቅድስና በንጽሕና እንዲሁም በትሕትና በደግነት ብሎም በየዋሕነትና በቅንነት የመኖር ሕይወት ነው፡፡
ይህንን ቅዱስ ጰውሎስ በዝርዝር እንዲህ ሲል ገልጿል፤ ‹‹ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቂዎች ሆኑ፥ የማይሞተውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚሞት ሰውና በዎፎች፥ አራት እግር ባላቸውም፥ በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ተዋቸው፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት ሐሰት አድርገውታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተውት፤ እርሱም ለዘላለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን።››
ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ፡፡ ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተመላለሱ፥ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍዳቸውን ያገናሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፣ ምኞትንም፣ ቅሚያንም፣ ቅናትንም፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ከዳተኞች፣ ተንኰለኞች፣ ኩሩዎች፣ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው፡፡ ሐሜተኞች፣ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክሕተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ ናቸው፡፡ የማያስተውሉ፣ ዝንጉዎች፣ ፍቅርም፣ ምሕረትም የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህን እንዲህ ላደረገ ሞት እንደሚገባው እነርሱ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ፍርድ እያወቁ፥ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አይደለም፤ ነገር ግን ሌላውን ያነሣሡታል፤ ያሠሩታልም›› (ሮሜ.፩፥፳፪፥፴፪)።
ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሰው በእምነቱ ጸንቶ በምግባሩ የሚያድግ ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ኦርቶዶክሳዊነት የእድገትና የለውጥ ሕይወት ነውና፡፡ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ እያለ የማያድግ የማይሻሻል የመንፈስ ተግባራትን የማይሠራ ከትላንትናው ሕይወትና ኑሮው የማይመለስ እራሱን የማይፈትሽ የማይመረምር ሃይማኖትን በሥራ በእውነትና በተግባር የማይለውጥ ሰው እርሱ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡
ሃይማኖተኛ (የሃይማኖት ተከታይ) ሰው መሆን ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ሃይማኖት በሥራና በተግባር መገለጥ አለበትና፡፡ ‹‹ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፤ ነገር ግን አንድ ሰው፦ አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? ብሎ ነግሮናል›› (ያዕ.፪፥፲፬-፳)።
ኦርቶዶክሳዊነትና ዘረኝነት በፍጹም አይገናኙም፤ ማንኛውም ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊና መንፈሳዊ ሰው (የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ) ዘረኛ፣ ብሔርተኛና ጎጠኛ መሆን አይችልምና፡፡ ይህ የአረማውያን ተግባር ነው፡፡ እኛን የሚገልጸን ፍቅር ሰላም አንድነት አቃፊነት መተባበር መደጋገፍ ፍትሕ እኩልነት መቻቻል መረዳዳት መደማመጥ መግባባትና በውይይት ማመን ልዩነትንም በመገነዛዘብና በመነጋገር የመፍታት እሴት ነው፡፡
ይህንን ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?›› (፩ኛ ዮሐ.፫፥፲፬-፲፯)፡፡
ኦርቶዶክሳዊነት የእምነት የእውነት የምስጋና ሕይወት ነው፡፡ ለእውነት የመኖርና ለእውነት የመገዛት ጭምር ነው፡፡ ውሸት አስመሳይነት ማጭበርበር መከፋፈል ማታለል ቃልን ያለማክበር ያለመተማመን ከእኛ መራቅ ያለባቸው የሥጋውያን ባሕርያት ናቸው የጥፋትና የሞት መገለጫ የአውሬውም መንፈስ ጭምር ናቸው፡፡
ለዚህ ነው መጽሐፍ ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና›› ብሎ የገለጸው (፪ኛጢሞ.፫፥፩-፯)።
ገንዘብ ጣዖት የሚሆንባቸው (የሆነባቸው) ሰዎች አሉ፡፡ ዓለምን የሚገዛው የገንዘብ ኃይል ነው፡፡ ገንዘብ የጥፋትም የልማትም ኃይል ነው፡፡ ፍቅረ ንዋይ መንፈሳዊነትን ያሳጣል፡፡ ሃይማኖትንም ያስክዳል፡፡ ከኦርቶዶክሳዊነት ዕሳቤና ክህሎትም እንዲሁም ጸጋና ክብርም ይለያል፡፡ ዛሬ ለገንዘብ ፍቅር ብለው የሰውን ነፍስን የሚያጠፉ፤ ሰላምን የሚያናጉ፤ ቤተሰብን የሚበትኑ፤ ሀገርን የሚያፈርሱ ስግብግብ ግለሰቦች አሉ፡፡ ይህ እምነት ካለው ፈጣሪውን ከሚፈራ ከሀገርና ለትውልድም ከሚያስብ ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ክርስቲያን ከዚህ አይነት ክፉ ሐሳብና ተግባር በፍጹም ሊርቅ ይገባል፡፡ በገንዘባችን መልካምነትን እንጅ ክፋትን መዝራት የለብንም፤ አንድነትና ፍቅርን እንጅ ልዪነትን ማስፋት የለብንም፡፡ መልካምነትን እንጅ ክፋትን መዝራት የለብንም፡፡ ጭካኔን ከራሳችን ማራቅ አለብን፡፡ መልካምነትና ደግነትንም ርህራሄንም ገንዘብ ልንደርግ ይገባል፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ‹‹ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ›› ያለን (፩ኛጢሞ.፮፥፲፩-፲፪)። በሌላም በኩል ‹‹ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው›› (ያዕ.፪፥፲፭-፲፯)።
ኦርቶዶክሳዊነት በእውነተኛ ሃይማኖት የመኖርና የማመን እውነታ ነው፡፡ (ይሁ.፩፥፫) መንፈሳዊነት ማለት መንፈሳዊ ሰው መሆን ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ደግሞ የራሱ አስተሳሰብና አካሔድ አለው፡፡ መንፈሳዊ ካልሆነ ሰው ግብሩ የተለየ ነው፡፡ መንፈሳዊነት ምናባዊ የሃይማኖት ሕይወት አይደለም፡፡ መንፈሳዊነት እግዚአብሔርን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚያምኑበት አይደለም፡፡ በሕይወት በእውነት በምግባር በሃይማኖት የሚገልጡት ነው እንጂ፡፡ መንፈሳዊ ሰው ከሥጋ ሰው በግልጽ የተለየ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው በውስጡ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አለው፡፡ ሥጋዊ ሰው ግን ነፍስና ሥጋ እንጂ ለነፍሱ ሕይወትን የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ አይደለም፡፡ ይህን መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹ለሥጋዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም››። (፩ኛ ቆሮ.፪፤፲፬-፲፭) (፩ኛቆሮ.፴፩፥፫፤ሮሜ.፰፥፲፪-፲፮)
መንፈሳዊ ማለት በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ምስክር የሆነ ሰው ማለት ነው፡፡ በስሜት በወሬና በአሉባልታ የማይመራ ሰው ነው፡፡ ስሜቱን መግታትም የሚችል አርቆ ማሰብ ማየት የሚችል ሰው ነው፡፡ በእምነትና በእውቀት የሚመራ ሰው ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑንም ያውቃል፤ በዚህም ንጽህናና ቅድስናውንም ጠብቆ የሚኖር፤ የምሥጢር ተሳትፎ ያለው፤ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚቀበልና አክብሮም የሚኖር ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆኑን ያውቃል፤ ከሰው ጋርም በፍቅርና በአንደነት በመቻቻልና በመረዳዳት በመደማመጥ በመግባባት የሚኖር ሰው ነው፡፡ ትዕግስት ያለው በእምነትና በተስፋ የሚመራና ችኩል ያልሆነ ነው፡፡ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በመፈለግ ሕይወት ውስጥ የሚኖር ሰው ነው ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊ ሰው፡፡ ከእርሱም ጋር አንድነት አለው፡፡ በአጭሩ መንፈሳዊ ሰው ማለት መንፈስ ቅዱስ ያደረበትና የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያም የሆነ ሰው ማለት ነው፡፡ ሁል ጊዜ ባልተቋረጠ ተዘክሮተ እግዚአብሔር ውስጥ የሚኖር ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ማለት ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት የተወለደ አዲሱ ሰው ነው፡፡
መንፈሳዊ ሰው ጠንቃቃ፣ ትሁት ይቅር ባይና የዋሕ የሆነ፣ በጸሎትና ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት የበረታ ሰው፣ እንቅስቃሴው ሁሉ በመንፈስ የተቃኘ ሰው ነው፡፡ እርሱ ከሁሉ ከፍ ብሎ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው የጸጋ መንፈስ ቅዱስ ተካፋይ የሆነና በእግዚአብሔርም ሕያው የሆነ ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለን አንድነት ሥጋዊውን ሰው መንፈሳዊ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሰውም ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና›› የሚለን (፩ኛ ተሰ.፬፥፯)።
ቅድስና የኦርቶዶክሳዊያን መንፈሳዊነትን ለዓለማዊያን የማሳወቂያ (ማሳያ) መንገድ ነው፡፡ ቅዱሳን በእግዚአብሔር እየኖሩ ስለ እግዚአብሔር የመሰከሩ ናቸው፡፡ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት በሕይወት የመሰከሩና የኖሩ ሕያዋን ቤተ መቅደሶች ናቸው፡፡ ቅዱሳን ማለት መልካም ሰዎች፤ ምግባራቸው የቀና፤ እራሳቸውን ለመንፈስ ቅዱስ ያስገዙ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከኦርቶክሳዊ ምግባራት የሚገኝ በረከት (ጸጋ) ነው፡፡ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን መገለጥ ተቀብለዋል መስክረዋልም፡፡
ኦርቶዶክሳዊነት ዕውቀት ብቻ አይደለም፡፡ የመረጃ ሰው መሆንና ተከታይ የመሆን ጉዳይም አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት እውነት፤ ሕይወት፤ ቅድስና እና ፍቅር ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው በውስጡ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያለው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ለመሆን አንድነትና ብርታቱን ይስጠን፤ በሃይማኖት መጽናትን፤ የምግባር ሰው መሆንን እርሱ ያድለን፤ አሜን፡፡