‹‹እግዚአብሔር ይቅርታን ይረሳልን? በቁጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?›› (መዝ. ፸፮፥፱)
ሰዎች በዚህ ምድር ስንኖር በየትኛውም ሁኔታና ፈተና ችግር ሊገጥመን ይችላል፤ አንድም አምላክችን ለበጎ ሊፈትን በማሰቡ ሲሆን፤ ሌላው ግን ጠላት ዲያብሎስ ውድቀታችንን በመመኘት በኃጢአት እንድንሰጥም ለማድረግ ነው፡፡ ዕለት ከዕለት ከምናደርጋቸው ክንዋኔዎች አንስቶ በማኅበራዊ ሕይወታችንና በሀገራዊ ተልእኮአችን ጣልቃ በመግባት በተለያዩ መንገዶች መከራና ሥቀይ አብዝቶ ሊጥለን ይፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዳንተገብር፣ ትእዛዛቱንም እንዳንፈጽም እና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዳንኖር በኃጢአት ለማሳት ዘወትር በመልፋቱ እርሱን ለማሸነፍ ከእኛ ጽኑ እምነት ይጠበቃል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች ብርታት የሚሆነው እና በእርሱ ኃይል ጠላት ዲያብሎስን ልናሸንፍ የምንችለው መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ሲሆን ነው፤ ያም በንጹሕ ልቡና የሚገኝ በረከት እንደመሆኑ ከኃጢአት የጸዳንና ከሰይጣን ሥራ የራቅን ልንሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ለዘመናት በኃጢአት ቁራኛ ውስጥ እንኖራለን፡፡
ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በመቅሠፍት የመመታቷ እውነታ የዚህ ምሳሌ ነው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረው የኃጢአት ሰንሰለት መረቡን ከጣለ ከርሟል፤ የተቻለውንም ነፍስ ወደ ሲኦል ለማውረድ የሚለፋው ሰይጣን ብዙዎችን ማሳቱ እሙን ነው፡፡ ሰው አእምሮውን መጠቀም እስኪሳነው ድረስ በትዕቢትና ትምክህተኝነት ታውሮ፤ ልቡናውም ደንድኖ የርኩስ መንፈስ ማደሪያ እስኪሆን ድረስ ሰይጣን እያሳተው ይገኛል፡፡ ‹‹ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር›› እንዲል። (ሕዝ. ፳፪፥ ፴፩)
ይህን ተረድተው በጸጸት እና በንስሓ ወደ አምላክ መመለስ የሚፈልጉ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ተግባራችንን እግዚአብሔርን በመፍራት መፈጸም ሲገባ የፈጣሪያችንን ትእዛዝ በመተላለፍ የእርሱን ሥራ በማናናቅና በጎ ምግባርን እንደ ድክመት በመቁጠር ክፋትን አብዝተን በመሥራታችን ለእንደዚህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ጊዜ ተዳርገናል፡፡ በሽታ፣ ሥቃይ እና መከራ የበዛበት፣ ሰው በሰላም ወጥቶ መግባት የማይችልበት፣ ዓለም በጦርነት እና በቸነፈር የተመላችበት፣ ሰው ከሰው እንዲሁም ሀገራት በጥል እና ጦርነት የሚፋለሙበት ክፉ ወቅት ነው፤ ዓለም የሰይጣን ማደሪያ ሆናለች፡፡ ሰላም ፍቅር እና አንድነት ጠፍቷል፤ ሰዎች እርስ በእርስ አይተዛዘኑም፤ አይረዳዱም፤ ከዛም አልፎ በጥላቻ መንፈስ ይጨካከናሉ፤ ይጣላሉ፤ ይገዳደላሉም፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ላይ እያለን ‹‹ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ለዚያውም በትንፋሽ እና በቀላል ንክኪ የሚተላለፍ በሽታ ከዓለም ዳር እስከ ዳርቻ ድረስ ተስፋፋ፡፡ ይህም ኮሮና ቫይረስ አመጣጡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መብላት የተከለከሉትን እንስሶች በመመገባቸው የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩትን ከጨረሰበት ከቻይና ሀገር መሆኑን መረጃዎች ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ›› እንዲል፡፡ (አሞጽ ፫፥ ፪)
እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋሉን ይስጠንና በቴክኖሎጂ አደጉ ከሚባሉ ሀገሮች በሕክምና ፈውስ ያልተገኘለት እና ወደ እኛ ሀገር የተስፋፋው ወረርሽኝ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍና በኃጢአታችንም ብዛት መምጣቱን ማወቅ ይገባል፡፡ በተለያዩ ዘገባዎች የፊት ጭንብል በማድረግ፣ የእጅ ጓንት በማጥለቅና እርስ በእርስ ንክኪ እንዳይኖር ርቀትን በመጠበቅ መፍትሔ እንደሚገኝ ሲነገር ቆይቷል፤ ሆኖም የበሽታውን ስርጭት ማስቆም አልተቻለም፡፡ በዚህም የምንረዳው አንድ ነገር አለ፤ እግዚአብሔር ቁጣውን እንዲመልስልን እና በምሕረቱም ይቅር ይለን ዘንድ ልንማጸን እንደሚገባ ነው፡፡
በኦሪት ዘጸአት እግዚአብሔር ሙሴን፤ ‹‹ለእስራኤል ልጆች እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ሌላ መቅሠፍት እንዳላመጣባችሁና እንዳላጠፋችሁ ተጠንቀቁ፤…..›› በላቸው ብሎ እንዳዘዘው ሁሉ ከዚህ የባሰ ቅጣት እንዳይመጣብን ራስን ከበሽታ ለመከላከል መጠንቀቅ ተገቢ ቢሆንም ኃጢአት እንደሆኑ እያወቅን ከምንሠራቸው ሥራዎችም ልንታቀብ ያገባል፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለማግኘት እርሱን የሚያስከፉና የሚያስቆጡ ምግባሮችን አለመፈጸም ያስፈልጋል፡፡
ብዙዎች በአሁኑ ሰዓት ስጋትና ጭንቀት ላይ ናቸው፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ይቅርታን ይረሳልን? በቁጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?›› ብሎ በጸሎት እንደጠየቀው አዛውንቶችም የዚህ መቅሰፍት ማብቂያ የሚቆምበትን ጊዜ በመመኘት አምላካቸው ስለምን ቸል እንዳለ ሲጠይቁ ይሰማሉ፤ ምሕረትንም እንዲያበዛልን አብዝተው ሲለምኑ ይደመጣሉ፡፡ (መዝ. ፸፮፥፱)
እኛም ጸሎታችንን ሰምቶና ይቅርታችንን ተቀብሎ ከዚህ መዓትና መከራ ይጠብቀን ዘንድ አምላካችንን እንማጸን፤ የምናሰበውን ክፋትና ተንኮል ከውስጣችን በማውጣት ልባችንን ንጹሕ አድርገን ንስሓ እንግባ፤ ዘወትርም በበጎ ሥራና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እንታነጽ፡፡ ያን ጊዜ ‹‹እግዚአብሔር ይቅርታን ይረሳልን? በቁጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ እናገኛለን፡፡