እግዚአብሔር ዝም ይላልን?
ክፍል ሁለት
ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ሐምሌ ፲፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
በቤተ ክርስቲያን ላይ መከራ እየበዛ እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል?
በየግል ሕይወታችን ችግር ሲገጥመን መፍትሔ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር እንደምንጮኸው ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ መከራ ሲመጣም እንዲሁ ከርሱ መፍትሔ እንጠብቃለን። በእኛ መረዳት የዘገየ ወይም ዝም ያለ ሲመስለን “ለምን?” እንላለን። “ካህናት እየታረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፣ ምእመናን እየተፈናቀሉ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እየተቆነጸሉ፣ ቤተ መቅደሱ እየተደፈረ፣ እንዴት እግዚአብሔር ዝም ይላል?” እንላለን። እንደዚህ የምንለው ምናልባትም አንዳች መቅሠፍት ወርዶ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን ያጠፋቸው ይሆናል ብለን ስለምንጠብቅና እንዳሰብነው ሳይሆን ሲቀር ሊሆን ይችላል። ምንም እናስብ ብቻ እኛ በጠበቅነው መንገድ ነገሮች ስላልሆኑ ግራ እንጋባለን፤ ከዚያም አልፈን ተስፋ እንቆርጣለን።
ከሁሉ አስቀድመን ማስተዋል የሚገባን ነገር ግን መከራ ራሱ እግዚአብሔር “የሚናገርበት መንገድ” መሆኑን ነው። አዎ! እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ይናገራል። በሥነ ፍጥረቱ፣ በቅዱሳን አንደበትነት፣ በመጻሕፍትና በተአምራት እንደሚናገረው ሁሉ በመከራም ይናገራል። “በመከራ የሚናገረን ለምንድን ነው?” የሚል ቢኖር በሥነ ፍጥረት በሌሎቹም አንደበቶቹ ሲናገር ስላልሰማነው ነው።
እናም “እግዚአብሔር ለምን ዝም አለን? ለምንስ አልሰማንም?” ከማለታችን በፊት “እግዚአብሔርን ለምን አልሰማነውም?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ መልካም ነው። በዚህ መከራ ምን ሊያስተምረን ፈልጎ ይሆን? ምን እንድናስተካክል ነው? እያልን በተደጋጋሚ ራሳችን መፈተሽ ስንጀምር ያኔ እግዚአብሔር በመከራው ውስጥ ምን እየተናገረ እንደሆነ ይገባናል። ምን እየተናገረን እንዳለ ራሳችንን ፈትሸን ስንረዳ፣ ከእኛ የሚጠበቀውን ስናደርግ፣ ያጣመምነውን ስናስተካክል ያን ጊዜ ምናልባትም “ለምን ዝም አለ?” ማለት እንችል ይሆናል፤ ያን ጊዜ ብንጠይቅም መልስ እናገኛለን።
የመጀመሪያው ምክንያት በንስሓ ለሚመለሱ ሰዎች ጊዜ እየሰጣቸው ሊሆን ይችላል። በቤተ ክርስቲያን የመከራ ታሪክ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድዱ የነበሩ በኋላ ንስሓ ገብተው ለቅድስና የበቁ ብዙ አባቶች አሉ። ሁለቱን ለማንሣት ያህል የመጀመሪያው በሐዋርያት ሥራ ላይ ታሪኩ የተጻፈው፣ በመጀመሪያ ላይ ቤተ ክርስቲያንን /በክርስቶስ ያመኑ ክርስቲያኖችን/ ሲያሳድድ የነበረ፣ በጌታ ስቅለት ጊዜ፣ በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነትም ጊዜ ከገዳዮች ጋር ተባባሪ የነበረ፣ በኋላም ሐዋርያትን ለመግደል ክርስቲያኖችን ሁሉ ለማሰር ይዝት የነበረ ይህን የጥፋት አላማውን ለመፈጸም ሲሔድ በእግዚአብሔር ቸርነት በተግሣፅ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። (ሐዋ.፰፥፫፣፱፥፩)
እስኪ ልብ እንበል! ቅዱስ ጳውሎስ በፊት በቤተ ክርስቲያን ላይ ባደረሰው መከራ ምክንያት እግዚአብሔር ባይታገሠውና ቢያጠፋው ኖሮ በዓለም ሁሉ በስብከቱ ያበራውን ብርሃንነቱን እንዴት እናገኘው ነበር? በርግጥም በዚያ ዘመን የነበሩና በእርሱ ምክንያት ይደርስ የነበረውን መከራ ያዩ ክርስቲያኖች ወደ ክርስትና ከመጠራቱ በፊት “ይህ ሰው ይህን ሁሉ መከራ እያደረሰ ለምን እግዚአብሔር ዝም ይለዋል?” ብለው የሚጠይቁ ቢኖሩ ከተጠራ በኋላ ደግሞ “እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ ትክክል ነው፤ የእርሱ ምርጥ ዕቃ የሆነ ሳውልን የታገሠው ለካ ለሁላችን መምህር እንዲሆን ነበር” እንደሚሉ አስተዋላችሁ?
ሌላውና ቤተ ክርስቲያንን በማሳደድ፣ ክርስቲያኖችን በማሠቃየት ይታወቅ የነበረው፣ በኋላ በእግዚአብሔር ትዕግሥት ምክንያት ወደ ክርስትና የተጠራውና ሰማዕትነት ተቀብሎ ያረፈው አርያኖስ ነው። በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን የእስክንድርያ ገዥ የነበረ ሲሆን ከጭካኔው ብዛት የተነሣ ብዙ መኮንኖች ሰማዕታትን አሠቃይተው አልሞትላቸው ሲሉና ሲደክማቸው ወደዚህ ሰው ይልኳቸው ነበር። ይህ ጨካኝ ሰውም በልዩ ልዩ መከራ አሠቃይቶ ይገድላቸው ነበር። ብዙ ሰማዕታት በእርሱ እጅ መከራ (የሰማዕትነት አክሊል) ተቀብለዋል።
በመጨረሻ ግን እርሱንም እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ወደ አሚን መለሰው። በክርስቲያኖች ከሚያደርሰው መከራ ትንሿን እንዲቀምሳት አደረገ፤ ክርስቲያኖችን በቀስት እያስነደፈ ሥቃያቸውን እያየ ይደሰት ነበር። ከሚያስወረውራቸው ቀስቶች አንዷ ወደኋላ ተመልሳ የእርሱን ዐይን ወጋች፤ ሥቃዩ እጅግ አስጨነቀው፤ በዚህ ጊዜ ነበር በአካባቢው ካሉ ከሚያምኑ ሰዎች በአንዱ ምክር ከሰማዕታቱ ደም ዓይኑን ቀብቶ ተፈውሶ በክርስቶስ ያመነው። በመጨረሻም በክርስቶስ ስም መስክሮ ሰማዕት ሆኖ ዐርፏል። መጋቢት ስምንት ቀን ታስቦ ይውላል። (ስንክሳር ዘየካቲት ፳፣ ዘመጋቢት ፰)
ከእነዚህ ቅዱሳን የምንረዳው እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ላይ መከራ የሚያደርሱ ሰዎችን ሲታገሳቸው ለንስሓ ዕድሜ እየሰጣቸው መሆኑን ነው። ከሚያሳድዱን ሰዎች በእግዚአብሔር ጥሪ ተመልሰው ራሳቸው ሰማዕት ሆነው ቀድመውን ገነት የሚገቡ ወይም እኛንም ለሰማዕትነት የሚያበረታቱ ሆነው የሚለወጡ ይኖሩ እንደሁ በምን እናውቃለን?!
እግዚአብሔር መከራ ሲገጥመን ከሃሊነቱን እንድንረዳና በእምነታችን እንድናድግ እስከ ጊዜው ድረስ ዝም ሊል ይችላል። በቅዱስ ወንጌል እንደተገለጠው ጌታችን ከሐዋርያቱ ጋር በታንኳ እየሔዱ ሳለ ማዕበል ተነሥቶባቸው እየተጨነቁ ጌታ ግን ተኝቶ ነበር። በፍርሃት ሆነው ልንጠፋ ነውና አድነን ብለው ቀሰቀሱት። ጌታ ተነሥቶ ማዕበሉን በገሠፀው ጊዜ ጸጥ አለ። ሐዋርያቱ ያን ጊዜ ተደንቀው እንዲህ ነበር ያሉት። “ባሕርና ነፋሳት የሚታዘዙለት ይህ ማነው?” (ሉቃ.፰፥፳፪-፳፭) ከዚህ ታሪክ ላይ እግዚአብሔር ማዕበል እንዲነሣ በመፍቀዱና ታንኳዋን እስኪደፍናት ድረስ ዝም በማለቱ ሐዋርያት በእርሱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር አድርጎላቸዋል። ማለት ባሕር ነፋሳትም የሚታዘዙለት መሆኑን እንዲረዱ ሆነዋል።
እግዚአብሔር በመከራ ሰዓት ስንጠራው የዘገየ ወይም ዝም ያለ ቢመስለንም እስክንጠፋ ድረስ ግን ዝም አይለም። በእሳት እስክንጣል ድረስ ዝም ይላል፤ ልክ ወደ እሳቱ ሲወረውሩን ግን ከእሳቱ ቀድሞ ደርሶ እንዲታደገን መልአኩን ይልካል። በመንኮራኩር እንድንፈጭ እስክንጣል ድረስ ዝም ሊል ይችላል፣ ነገር ግን የመንኮራኩሩ አንድ ጥርስ ሳይነካን ቀድሞ ያድነን ዘንድ መልአኩ ከዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ እንዲደርስልን ያደርጋል።
በቅዱሳን ሰማዕታት ታሪክ የምናስተውለው ይህ ነው። ሠለስቱ ደቂቅ ወደ እሳት እስኪጣሉ ድረስ ዝም አለ። በእሳት ይጣላሉ የሚል አዋጅ ሲወጣ ዐዋጁን አላስቀየረም፤ ንጉሡ እንዲጣሉ ሲፈርድ ዝም አለ፤ እጅና እግራቸውን አሥረው ወደ ምድጃው ሲወስዷቸውም ዝምም። እሳቱ ላይ ሲጥሏቸው ግን እሳቱ እነርሱን መብላት ሳይጀምር መልአኩን ልኮ አንዲት የራሳቸው ጠጉር እንዳትለበለብ እንዲጠብቃቸው አደረገ። በዚህ ሥራው እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ መሆኑ ተገለጠ። ንጉሡም በእግዚአብሔር የማዳን ኃይል አምኖ አዋጁን በአዋጅ እስከ መሻር ደረሰ። እንግዲያውስ እግዚአብሔር ዝም ያለን ሲመስለን በመጨረሻዋ ሰዓት ሊያድነን እንደሚቻለው እንመን።
ግን ባያድነንስ? የክርስትና ዓላማው ከመከራ መዳን ነው እንዴ? እንዲያው በመጨረሻዋ ሰዓት ሊያድነን ይችላል የሚለውን እውነታ (ከኃሊነቱን) እንድንረዳ እንጂ የክርስትና ዓላማው ከመከራ መዳን አይደለም። ሰማዕታትም ወደ እሳት ወደ መንኮራኩርም ሲጣሉ መከራውን ፈልገው እንጂ መዳንን ፈልገው አይደለም፤ መዳን ቢፈልጉማ መጀመሪያውኑ ለምን ወደ ሰማዕትነት አደባባይ ይመጣሉ። እግዚአብሔር ያንን ተአምር ዐይተው ለሚመለሱት ሲል ከእሳቱም ከሌላውም ሥቃይ ያድናቸዋል እንጂ የእነርሱ ፈቃድ በክርስቶስ ስም መከራ ተቀብለው ማለፍ ነው።
በሠለስቱ ደቂቅ ሕይወትም ይህን እናስተውላለን። “. . . ከእሳቱ ያድነን ዘንድ ይችላል” የሚለው አባባላቸው የእግዚአብሔርን የማዳን ችሎታ የገለጡበት ቃል ነው። ሰማዕትነቱን እንደሚፈልጉት ግን “ባያድነንም አንተ ላቆምኸው ምስል አንሰግድም” በሚለው ንግግራቸው እንረዳለን። እግዚአብሔር ማዳን የሚቻለው ሆኖ ሳለ ሰማዕትነት እንድንቀበል ከወደደ እንቃጠል እንጂ ለሱ መስገድ ትተን በእጅህ ለተሠራ ምስል አንሰግድም ማለታቸው ነው። (ዳን.፫፥፲፰)
እግዚአብሔር ከኃሊነቱን በተአምራት መግለጥ ሲፈቅድ በሰው ሰውኛው “አበቃ” እስኪባል ድረስ ዝም ይላል። ሁሉም ነገር ካለቀለት በኋላ ተቆረጠ የተባለው ተቀጥሎ ሲገኝ ከአእምሮ በላይ ስለሚሆን ለእምነት ኅሊናን ያስገድዳል። የተአምሩ ተአማኒነት የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የሆነውን ይህን ክስተት ያዩ ያምናሉ። እናም ተአምራት ተአምር ከተደረገለት ሰው ይልቅ ያን ተአምር ዐይተው ወደ አሚን ለሚመጡ ሰወች ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ነው።
ይህ ከሆነ ትኩረታችን ከሥጋ ሞት መዳን ላይ ትኩረት ያደረገ ሊሆን አይገባውም። “ለምን” ብለን ስንጠይቅም በሥጋ እንዳንሞት ሳይሆን በነፍስ ዘለዓለማዊ ሞት እንዳያገኘን ተጨንቀን ሊሆን ይገባል።
ሁልጊዜ መከራ በቤተ ክርስቲያን ሲኖር አብሮ የሚመጣልን መልካም ዕድል አለ። ይኸውም ሰማዕትነት ነው። የመከራው ዓይነት ሲለያይ የሰማዕትነቱም ዓይነት ይለያይ ይሆናል። መከራው አካላዊ ጥቃት ሲሆን የደም ሰማዕታትን ቤተ ክርስቲያን ታገኛለች፤ በትምህርተ ሃይማኖት ላይ የመናፍቃን መነሣት ሲሆን ደግሞ ቅዱሳን ሊቃውንትን ታገኛለች። በአርዮስ ምንፍቅና ጊዜ ቅዱስ አትናቴወስ፣ በንስጥሮስ ክህደት ጊዜ ቅዱስ ቄርሎስ፣ በልዮን ክህደት ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተነሥተዋል። እንደአጠቃላይ በመናፍቃን መነሣት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሳን የበለጠ እንድንመረምር ዕድል አግኝተናል። ዐላዊያን ነገሥታት በተነሡ ጊዜም ቤተ ክርስቲያን አእላፍ ሰማዕታትን አግኝታለች። በመከራ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ በቅዱሳን ታሸበርቃለች።
ሌላው ልብ ማለት የሚኖርብን ነገር በዚህ የመከራ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እየተጸዳች ሊሆን እንደሚችል ነው። ከሰውነታችን አንድ አካላችን ቢታመም፣ የዚያ አካል መኖር ሌሎች አካላት እንዲመረዙ የሚያደርግ ከሆነ ለሌላው ጤና ሲባል የምንወደው አካላችን እንዲቆረጥ ይደረጋል። በመቆረጡ እናዝናለን ግን ደግሞ ካልተቆረጠ ሌላውን ሁሉ ስለሚበክል አደጋው የከፋ ይሆናል። በቤተ ክርስቲያን መከራ ጊዜ ራሳቸው ተመርዘው ሌሎች ምእመናንንም ሊመርዙ የሚችሉ አካላት ይለያሉ፦ ወይ በመካድ ራሳቸው ይወጣሉ ወይም በመቅሠፍት ይጠፋሉ።
በሰማዕትነት የሚያልፉትን ከዚህ ጋር እንዳናምታታው መጠንቀቅ ያሻናል። በሰማዕትነት የሚያልፉ እነርሱ የክርስቶስ አምላክነት እንዲክዱ ተጠይቀው አንክድም ብለው ወይም ቤተ ክርስቲያንን አናስደፍርም ብለው. . . በአጠቃላይ ዓላማው ለሃይማኖት መቆም ላይ መሠረት ባደረገ ምክንያት የተገደሉና የሚገደሉ እነርሱ በእውነት ሰማዕታት ናቸው፤ ለእነርሱ መከራቸው ሽልማት፣ ሞታቸውም ዕረፍት ነው።
“በሰማዕትነት ያላለፈውና በሌላ ምክንያት የሞተው ሁሉ በቃ ተቀስፏል ማለት ነው?” የሚል ሐሳብም እንዳይኖር፣ ማናችንም ስለማናችን አናውቅም ማሰብ የምንችለው እግዚአብሔር በመከራው ጊዜ ከላይ በገለጽነው ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የሚለየው አካል ሊኖር እንደሚችል ብቻ ነው። ከዚያ ባለፈ ስለማንም ምንም ለማለት አንችልም፤ ብንፈልግም እንኳን ዐቅማችን አይፈቅድም።
በመጨረሻ ማሰብ የሚገባን ነገር እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠበቀውን እንድናደርግ ዕድል እየሰጠን /የአገልግሎት መስክ እያመቻቸልን/ መሆኑን ነው። እርሱ ያለማንም ርዳታ የወደደውን ማድረግ ይችላል፤ የቤተ ክርስቲያንን ችግርም መፍታት ይችላል፤ ይሁን እንጂ ስለፍቅሩ ብዛት የተነሣ እኛ በሥራው እንድንሳተፍ፣ በእኛ አድሮ ለመሥራት ይፈቅዳል። ይህን ለማወቅ ደግሞ ራሱ “ከናንተ የምፈልገው ነገር አለ” እንዲለን መጠበቅ የለብንም። ሰዎችን በሥራው ውስጥ ማሳተፍ ፈቃዱ እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተገልጿልና።
በመጽሐፈ አስቴር ላይ የተገለጸው ታሪክ የሚያሳየን ይህንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነው። አስቴር በወገኖቿ ላይ ሞት በታወጀ ጊዜ ጾም አሳውጃ፣ ራሷም ጾማ ወደ እግዚአብሔር አመልክታ ብቻ ዝም አላለችም። “ከኔ የሚጠበቀው መጸለይና ችግሩን ለእግዚአብሔር ማሳሰብ ነው” አላለችም፤ ይልቁንስ እግዚአብሔር በእርሷ እንደሚሠራ አምና ንጉሡን ያለተራዋ/ያለጊዜዋ ገብታ አነጋገረችው። እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ስለነበረ በፊቱ ሞገስ አግኝታ፣ የእስራኤላውያንን የሞት ደብዳቤ እንዲለወጥ አደረገች። (መጽሐፈ አስቴር ሙሉውን ያንብቡ)
መከራው እስካለ ድረስ እያንዳንዳችን ማድረግ የሚጠበቅብን ነገር እንዳለ ሊሰማን ይገባል። ምናልባትም የሚጀምረው ንስሓ ከመግባት፣ ሥጋ ወደሙ በመቀበል ከክርስቶስ ጋር በመሆን ሊሆን ይችላል። ከእኛ የሚጠበቀው ምንድን ነው? ብለን ማሰብና ሥራ መጀመር ግን ግዴታችን ነው።
በመጨረሻ
የመከራውን ጊዜ እንደክፉ ዘመን ከማሰብ ይልቅ እንደመልካም አጋጣሚ ብናስበው እንጠቀማለን። በዋናነት በዚህ ጊዜ ሁለት መልካም ዕድሎች አሉን። የመጀመሪያውና እጅግ የተወደደው ሰማዕት የመሆን ዕድል ነው። መመረጥ የሚያስፈልገው ዕድል እንደሆነ እናስባለን? እንግዲያውስ በዚህ ሰማዕትነት በበዛበት ዘመን መኖራችን በራሱ መመረጥ መሆኑን አስበን ራሳችንን እናዘጋጅ። ከልባችን ከፈለግነውና እግዚአብሔርን ከለመንነው የማይገባን ቢሆን እንኳን ይህን ዕድል ይሰጠናል።
ለኃጥአን የወረደ ጥፋት ለጻድቃን እንደሚተርፈው ሁሉ ለጻድቃን የወረደ በረከትም ለኃጥአን ይተርፋል። ለተገባቸው ሰዎች የወረደ የሰማዕትነት ዕድል ከልባችን ከሻትነው ለእኛ ላልተገባንም ይሰጠናል። የሰማዕታት ደም እንዲሁ የሚፈስ አይደለም፤ የእነርሱ ትዕግሥት ሌሎች ደካማ የነበሩ ሰዎችን እንዲጨክኑ ኃይል ይሰጣቸዋል። በብዙ ቅዱሳን ሰማዕታት ታሪክ የምናነበው ይህንን ነው።
የመጀመሪያውንና እጅግ መልካሙን ዕድል ለመሳተፍ አቅም እንደሌለንና መከራውን ፈርተን እንደምንክደው እግዚአብሔር ካወቀ ደግሞ በልዩ ጥበቃው ተጠብቀን ከመልካሙ ዘመን እንድንደርስ ማድረግ ይቻለዋል። ከእኛ የሚጠበቀውን አድርገን በንስሓ ሕይወት፣ በሥጋ ወደሙ እየኖርን ‹‹የአንተ ፈቃድ ይሁን›› ብለን ለእርሱ መስጠት ነው። የምንችለውንና የሚጠቅመንን እርሱ ያውቃልና። ከእነዚህ ከሁለቱም መሆን ካልቻልን ዕድል ፈንታችን ምን ይሆን?
እግዚአብሔር በቸርነቱ፣ ስለሰማዕታቱ ደም ብሎ ይማረን! ረድኤቱ አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ወለወላዲቱ ድንግል!
ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን!