ለሲኖዶሳዊ ልዕልና መከበር የምእመናን ድርሻ አስፈላጊ ነው!

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ሐምሌ ፲፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ተቋማዊ መዋቅር እና የሰው ሀብት ያላት ዓለማቀፋዊት ተቋም ናት፡፡ ይህች ለሀገር ጌጥ ለዓለም ፈርጥ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በብቃት እና በሚያሰደንቅ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ጥበብ የአስተዳደር ጥበብን ለሀገር ብሎም ለዓለም ያበረከተች መንፈሳዊ ተቋም ናት፡፡

ለዚህም ትልቁ ምክንያት ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ቀናዒ የሆኑና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ በሚያከብሩ፣ በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመሩ፣ የሞራል ልዕልናቸው ከፍ ያሉ አገልጋዮች እና ምእመናን ስለነበሯት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና አለመከበር እንዲሁም በርካታ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች  ባይታዋር የሆኑበት፣ ቤተ  ክርስቲያንን ለካህናቱና ጳጳሳቱ ብቻ እየተው የመጡበት ሁኔታ ይታያል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስትያንን ፖለቲከኞች፣ አማሳኞች፣ ምንደኞች አገልጋዮች እንዲሁም የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቿ  አጀንዳ ሲያደርጓት፣ ባልዋለችበት ሲያውሏት፣ የማይገልጻትን ጥላሸት ሲቀቧት፣ ታሪኳን ሲሰርዙ፣ ሲደልዙ፣ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሲያደርጓት፣ በባሰ ሁኔታ ኵላዊትነቷን፣ ዓለማቀፋዊነቷን  ወደ ጎን በማለት በርካሽ የጎሳ ከረጢት ሊከቷት ሲሞክሩ እያዩ ዝም ማለታቸው ነው፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኗ ክብሯ ተጠብቆ ሲኖዶሳዊ ልዕልና እንዲከበርና በአገልግሎቷና በአስተዳደርዋ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ  የምእመናን ተሳትፎ  ያስፈልጋል፡፡

ይህ ጽሑፍ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና የምእመናንን ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ የቀረበ ነው፡፡

.. ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ምን ማለት ነው?

ሲኖዶስ ቃሉ የጽርዕ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ስብሰባ (ጉባኤ) ማለት ነው፡፡ አንድ/ቃለ ዓዋዲ፣ ሀብታችንና ሥርዓቱ/ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/

ቤተ ክርስቲያናችን በሕግና በሥርዓት እንድትመራ ልዩ ልዩ መመሪያዎች ተሰጥተዋታል፡፡ የመመሪያው ባለቤትም ራሱ መሥራቿ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው እና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› በማለት አደራ የሰጣቸው የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳትን ነው፡፡ (፪ የሐዋ.ሥራ ፳፥፳፰) የጳጳሳቱ አንድነት ጉባኤ /ስብስብ /ደግሞ ሲኖዶስ ይባላል፡፡

.. የቅዱስ ሲኖዶስ ታሪካዊ አመጣጥ፡

በብዙ ታሪኮች ላይ እንደ መጀመሪያ ሲኖዶስ ጉባኤ ተመዝግቦ የሚገኘው በ፶ ዓ.ም በኢየሩሳሌም የተደረገውን ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤውም በሐዋርያት የተደረገ ስብሰባ ሲሆን መሪውም የኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ያዕቆብ እንደነበረና የስብሰባው ምክንያትም ከአይሁድ ወደ ክርስትና የመጡት እና ከአሕዛብ በመጡት መካከል በነበረው አለመግባባት ላይ ለመምከር ነበር፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፩፥፲፭)  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስብሰባዎች ተደርገዋል፤ በርካታ ሥርዓቶች እና ሕግጋት ለቤተ ክርስቲያን ተደንግገውበታል፡፡ በዚህም ሲኖዶስ እየተባሉ የሚጠሩ እና እስካሁን ቤተ ክርስቲያን የምትመራባቸው ሕጎች ወጥተውበታል፡፡ በኋላም በብዙ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት /ኒቅያ፣ ቍስጥንጥንያ፣ ኤፌሶን ወዘተ/ ዳብረውና ጸንተው የተላለፉ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥት ዋናውና ትልቁ ሲሆን በርካታ የሐዋርያት ሲኖዶስ ውሳኔዎችና ሌሎች ሕጎችን ይዟል፡፡

.. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ተግባርና ኃላፊነት

ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ እንደተገለጸው በዓመት ሁለት ጊዜ እየተሰበሰቡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው እንዲወያዩ ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ (ፍ/መ. ፭፥፻፷፭) ይህም ሥርዓት እስካሁን ቀጥሏል፡፡ የስብሰባውም ምክንያት

  • ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ምግባርን ለማቅናት
  • ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋት፣ ምእመናንን ለማብዛት
  • መናፍቃንን /ከሐድያንን ለመለየት፣ ሕግንና ሥርዓትን ለማውጣት ብሎም ለማስፈጸም
  • የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አንድነት ለማጽናትና ሁለንተናዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ መብቷን ለማስከበር አስተምህሮዋን ለማስፋት እና ለማስቀጥል የሚደረጉ ስብሰባዎች ሲኖዶስ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡

ምክንያቱም ተሰብሳቢዎቹ ‹‹አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ›› እንዲሉ አበው አደራቸውን ለመወጣት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ፣ ለመንጋው መራራትና ለራሳቸው መጠንቀቅ የተሰጣቸው አደራ ነውና፡፡ (የሐዋ. ሥራ ፳፥፳፰) ዋጋቸውንም በሰማይ ይቀበሉ ዘንድ፡፡ አንድም መክሊታቸውን ቀብረው ክፉ አገልጋይ (ማቴ.፳፭፥፳፬) ተብለው እንዳይፈረድባቸው ተግተው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ይሠራሉ፡፡

.. የቅዱስ ሲኖዶስ የክብሩ/የልዕልናውና መገለጫ፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ክብሩ ከፍ ያለ ነው፤ ልዕልናውም እጅግ ታላቅ ነው፤ ቅዱስም ነው፤ ቅድስናው፣ ልዕልናው ክብሩ እንዲሁ አይደለም፤ ምክንያቱም

ሀ. መሪው ሰብሳቢው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ነው፡፡

ሲሰበሰቡና ሲወስኑ መንፈስ ቅዱስን መሪ ሰብሳቢ አጋዥ አድርገው ስለሆነ ነው፡፡ አርዮስን ለማውገዝ ሃይማኖት ለማጽናት በኒቅያ /የቤተ ክርስቲያን ታሪከ፣ ሃይማኖተ አበው/ የተሰበሰቡ ፫፻፲፰ ሊቃውንትም ጌታ አብሯቸው እንደሚሰበሰብ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡

. የሐዋርያት ወራሴ መንበር ስለሆነ

‹‹እናንተን የተቀበለ እኔን መቀበሉ ነው ያላቸው የሐዋርያት ተከታዮች ናቸው፤ ሊቃነ ጳጳሳት በክርስቲያኖች ላይ ያላቸው ሹመት ሙሴ በእስራኤል ላይ እንደነበረው ምስፍና ያለ ነው›› ተብሎ ተደንግጓል፡፡ (ፍ/መ/፬፣፶፬ እና ፶፭/

 . ለቅድስና የሚያበቃ ሕግና ሥርዓት ስለሚወጣበት ነው፡፡

ሥጋዊ ያይደለ መንፈሳዊ፣ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሥርዓት የሚሠራበትና ሕግ የሚደነገግበት ስለሆነ ነው፡፡

. በቅድስናቸውበንጽሕናቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠባቂነት የተመረጡ ስለሚሰበሰቡበት

ለቅድስና በምታበቃ ክህነት የተሾሙ፣ ሹመታቸው/መመረጣቸው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሆነ፣ እኛና መንፈስ ቅዱስ ብለው የሚወስኑ፣ ጥብቅናቸው ለቤተ ክርስቲያን የሆኑ ብፁዓን አበው የሚሰበሰቡበት ስለሆነ ቅዱስ ነው፡፡

. ሃይማኖት እምነት የሚጸናበት ጉባኤ ስለሆነ

የሃይማኖት አንድነት የሚጸናበት፣ ክሕደት፣ ጥርጥር፣ የሚወገዱበት፣ አጋንንትና ውሉደ አጋንንት የሚገሠፁበት እና የቅዱሳን ቅድስና የሚነገርበት/የሚወሰንበት/ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ስንል ቅድስናው የሚመነጨው ከሰው ሳይሆን ከራሱ ሁሉን ከሚቀድስ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ክቡር፣ ቅዱስና ልዑል ነው፡፡

.. የልዕልናው መገለጫ የውሳኔዎቹ መፈጸም ነው፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ሲኖዶስ ክቡር ነው፤ ቅዱስ ነው፤ መሪውም መንፈስ ቅዱስ ነው፤ የክብሩ መገለጫ የልዕልናው መታያ መሆን ያለበት በመንፈስ ቅዱስ በብፁዓን አባቶች የተወሰነ ውሳኔ ሁሉ ሲከበር እና ሲተገበር ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለብዙ ሺህ ዓመታት ጸንታ የቆየችው ወርቃማውን ሥርዓቷን ጠብቃ ለትውልዱ ሁሉ ኩራት የጥበብ፣ የዕውቀት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ቤት፣ የመልካም ሰብእና ማእከል ሆና የዘለቀችው የማይናወጽ ሲኖዶሳዊ ሥርዓት በመጠበቁ በመከበሩ ውሳኔዋ በመፈጸሙ ነው፡፡ በርግጥ አንዳዶች በሊቃውንት ጉባኤ ስትመራ እንደኖረችናየሲኖዶሳዊ ታሪኳ ከ፶ ዓመት ያልዘለዘለ መሆኑን ይሞግታሉ፡፡ (አቡነ ሳሙኤል) ቢሆንም በሐዋርያት ሲኖደስ የምንተዳደር፣ ‹‹ማርቆስ አባታችን እስክንድርያ እናታችን›› ብለን የኖርን ሲኖዶስ አልነበረንም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም፡-

  • የሕግና ሥርዓት ምንጭ፣ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃና ዳኛ
  • የጾታ ምእመናን ባላደራ፣ የሐዋርያት ወራሴ መንበር የሆነ
  • የምሥጢራት ባለቤት፣ የክህነት መገኛ ወዘተ የሆነው

ቅዱስ ሲኖዶስ ክብሩ ልዕልናው ካልተከበረ ውሳኔው ካልተፈጸመ ህልውናው ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀርቶ ሀገርና ትውልድ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ምክንያቱም ሕግ ሁሉ ከሰው ከሆነ ሕገ ሰብእ መሆኑ ይቀርና ሕገ አራዊት ይሆናልና፡፡  ቤተ ክርስቲያን ደግሞ መገለጫዋ መሪዋ የሕግ ሁሉ ምንጭ ሲኖዶሷ ነውና፡፡

ቸር ይግጠመን!

ይቆየን!