‹‹እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነኝም›› (መዝ. ፻፵፫፥፯)
ዲያቆን ዘላለም ቻላቸው
አዳም የድኅነት ቃል ኪዳንን ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተቀበለ ከአምስት ሺሕ ዓመታት በኋላ የአዳምን በደል ካሣ ከፍሎ ከራሱ ጋር ሊያስታርቀው እግዚአብሔር ወልድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በተዋሕዶ ሰው ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ የነበሩ የቃል ኪዳን ዓመታት አምላካችን የፈጸመዉን የድኅነት ሥራ (ሥጋዌ፣ ሞት፣ ትንሣኤ …) የሰው ልጆች እንዲረዱ ለማስቻል ዝግጅት የተደረገባቸው ዘመናት ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናት እግዚአብሔር የራሱን ሕዝቦችን እና ሰዎችን በመምረጥና ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት፣ ለእነዚህ ሕዝቦች ተአምራትን በማድረግና ከጠላቶቻቸው በማዳን፣ ከዚህም ባሻገር ነቢያቱን ልኮ ሕዝቡን በማስተማር፣ ትንቢት በማስነገር ሱባኤም በማስቈጠር አምላነቱንና ዓለምን ለማዳን ያቀደውን ዕቅድ ቀስ በቀስ፣ በጥቂት በጥቂቱ ገልጧል፡፡ በየዘመኑ የተነሡ ነቢያትም ምንም እንኳን አምላክ ይህን ዓለም እንዴት እንደሚያድነው በግልጽ ባይረዱትም እግዚአብሔር ዓለሙን የሚያድንበትን ቀን እንዲያቀርበው እንዲህ እያሉ ይማፀኑ ነበር፤ ‹‹አቤቱ ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው፤ ውረድም፤ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም፡፡ መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው፤በትናቸውም፤ፍላጾችን ላካቸው፤ አስደንግጣቸውም፡፡ እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነኝም›› (መዝ. ፻፵፫፥፭-፯)፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ እንደ ገለጸልን በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ስለሚመጣው ነገር ሁሉ ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔ ቈጥረዋል፤ ሕዝቡም የጌታን ማዳን በተስፋ እንዲጠብቅ አስተምረዋል፡፡ ጌታ ሰው ሆኖ የተወለደው ከዚህ ሁሉ ዝግጅት በኋላ ነው፡፡ የአዳኙ መሲሕ የክርስቶስ መወለድ በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከእስራኤል መካከል ቅን የነበሩትና በእግዚአብሔር መንገድ የተጓዙት ‹‹መሲሑን አገኘነው ፤ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው፤›› እያሉ ተከትለውታል (ዮሐ. ፩፥፵፩-፵፭)፡፡ እንግዲህ ይህ ታሪክ ከተፈጸመ ጌታችንም ከተወለደ እነሆ ፳፻፲፪ ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ እኛም የተደረገውን ሁሉ በትውፊት ተቀብለን በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተሳትፈን በዚህ በድኅነት ጉዞ የተሰጡንን ጸጋዎች ተካፍለን ክርስቲያኖች ሆነናል፡፡
‹‹በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደ ተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን፤›› (ሮሜ. ፮፥፬) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንዳስተማረው ክርስትና፣ በጥምቀታችን ሞተን እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነሥተን በትንሣኤው ብርሃን በአዲስ ሕይወት የምንመላለስበት፤ የእግዚአብሔርን ፍቅር እያገኘን፣ ያደረገልንን ሁሉ እያደነቅን፣ ጸጋውን ዕለት ዕለት እየተቀበልን የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡ በዚህ ክርስቲያዊ ሕይወት ስንኖር አምላካችን ለእኛ ብሎ የፈጸመውን የማዳን ሥራ (ልደቱን፣ ጥምቀቱን፣ ጾሙን፣ መከራውን፣ ስቅለቱን፣ ትንሣኤዉንና ዕርገቱን እንደዚሁም ዳግም ምጽአቱን) ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ሕይወታችን ጌታችን የፈጸመዉን ተግባር ሁሉ በማስታወስ፣ በማሰብ እና በመካፈል ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን በነገረ ድኅነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን የጌታችን ድርጊቶች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እንድናስባቸው አድርጋለች፡፡ የልደትን፣ የጥምቀትን፣ የስቅለትን፣ የትንሣኤን፣ የዕርገት እና ሌሎች በዓላት የማክበራችን ዋናው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
ዳሩ ግን በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሰውነት በኀጢአት በማቆሸሻችንና ራሳችንን ከጸጋ እግዚአብሔር በማራቃችን፣ እንደዚሁም በልዩ ልዩ ሥጋዊ ጉዳዮች ተጠምደን በወከባ በመኖራችን ይህን ማድረግ ይክብድብናል፡፡ እነዚህን በዓላት ስናከብር ከሚያስጨንቁንና ሕሊናችንን ከሞሉት ሥጋዊ ጉዳዮች ተመልሰን በአንድ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ ሐሳብና ተመስጦ መምጣት ስለምንቸገር ቤተ ክርስቲያን ከበዓላቱ በፊት የዝግጅት፣ የማንቂያ ጊዜያት እና አጽዋማት እንዲኖሩም አድርጋለች፡፡ በእነዚህ ወቅቶች ሕሊናችንን ቀስ በቀስ ወደ መንፈሳዊው ሐሳብና ተመልሶና በዓሉን በናፍቆት ጠብቀን በተገቢው ሥርዓት እንድናከብረውም ታዝዛለች፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በዓላት ከመከበራቸው በፊት አጽዋማት ይኖራሉ፤ ሥጋ ወደሙን ከመቀበላችንም በፊት እንጾማለን፡፡ ሌሎቹም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከመፈጸማቸው በፊት የጾምና የዝግጅት ወቅቶችን ማሳለፍ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንዲከበር ያደረገችው ከእነዚህ ዘወትር ልናስባቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የሆነዉን ብርሃኑንና ዘወትር ልናየው የሚገባውን የጌታችንን ልደትን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እንድናስበው ነው፡፡ ይህን በዓመት አንድ ጊዜ የሚመጣውን በዓልም ቢሆን ከማክበራችን በፊት ዐርባ ሦስት ቀናትን በመጾም እንዘጋጃለን፡፡ በመጾም ብቻ ሳይሆን እነዚህ ዐርባ ሦስት ቀናት ተከፋፍለው የልደት በዓልን በተገቢው መንገድ እንድናከብር የሚያዘጋጁ ትምህርቶችን እንማርባቸዋለን፡፡ በተለይም ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት ይህ ዓላማ አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንዘጋጅ ዘንድ እነዚህን ሦስት ሳምንታት የጌታችንን ልደት በናፍቆት በመጠበቅ እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ሆነን እንድናሳልፍ ታደርጋለች፡፡
በእነዚህ ሳምንታት (በተለይም በእሑዶቹ) የብሉይ ኪዳን ነቢያት የአዳኙን መምጣትና የጌታን ቀን መገለጥ በመናፈቅ ስላሳለፏቸው ጊዜያት ደጋግመን በመማር እነዚያን የጨለማ ዘመናት እንድናስታውስና እኛም በእነርሱ መንፈስ ተቃኝተን ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንናፍቃለን፤ በዓሉን ለማክበርም እንዘጋጃለን፡፡ በዓሉን የምናከብረውም እንዳለፈ ታሪክ ለማሰብ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ፤ ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሆነ›› እያልን የምናመሰግነው፤ ‹‹ዮም፣ ዛሬ›› ማለትም በዓሉ የልደት መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን በዚያ በልደት ቀን እንደነበርን አድርገን የምከብረው በዓል መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከልደተ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ ሳምንታት፣ ነቢያቱ፣ አምላክ ይህን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸውና ነገረ ድኅነትን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሳምንታት ናቸው፡፡
፩. ስብከት– ከታኀሣሥ ፯ እስከ ታኅሳስ ፲፫
ስብከት ማለት ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ከሙሴ ጀምሮ የነበሩ ነቢያት በሙሉ አዳኝ (መሲሕ) እንደሚመጣ ማስተማራቸው፣ ጌታችንም ነቢያት ይመጣል ብለው ያስተማሩለት አምላክ እርሱ መሆኑን መግለጡ የሚታሰብበት ነው፡፡ ሙሴ ለጊዜው የጌታችን ምሳሌ ለሆነው ለኢያሱ ፍጻሜው ግን ለጌታችን በሆነው ትንቢቱ ‹‹አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ስሙት፤›› ብሎ ለሕዝበ እስራኤል ነግሯቸው ነበር (ዘዳ. ፲፰፥፲፭)፡፡ ጌታችንም ይህ ትንቢት በእርሱ መፈጸሙን ሲያመላክት ‹‹ሙሴ እና ነቢያት ሁሉ ስለ እኔ ይናገራሉ›› እያለ አስተምሯል፡፡ ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚጓዙ እስራኤላውያንም በቃሌ አምነው ተከትለውታል፡፡ ሐዋርያትና ሌሎች አባቶችም ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ በተለይ የተነገሩትን ትንቢቶች ሁሉ ያውቁ ለነበሩት እስራኤላውያን ያስተማሩት እነዚህን የነቢያት ትምህርቶች እና ትንቢቶች እያጣቀሱ ነበር፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ ‹‹አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለ ማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ እንደ ተናገረ እንዲሁ ፈጸመ፤›› (ሐዋ. ፫፥፲፯-፲፰)፡፡ በሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ ‹‹ወንድሞች ሆይ፥ የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኀኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ … ዕወቁ፤›› (፪ኛ ጴጥ. ፫፥፩-፫)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ስለ እግዚአብሔር መገለጥ እንዲህ ሲል አስተምሯል፤ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፥ ሁሉን በፈጠረበት በልጁ ነገረን፤›› (ዕብ. ፩፥፩-፪)፡፡
፪. ብርሃን- ከታኀሣሥ ፲፬ እስከ ታኅሳስ ፳
ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት፣ ሁሉ ነገር አስጨናቂ የሆነበት፣ ሰው ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ያሉበትን ዘመን «ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ የሚያስወግድና ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን እንዲመጣ እንዲህ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡ ‹‹ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ እነርሱም ይምሩኝ፡፡ አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደራያህ ይውሰዱኝ፤›› (መዝ. ፵፪፥፫)፡፡ ጌታችንም ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ›› በማለት ለዚህ ጸሎት ምላሽ ሰጥቷል (ዮሐ. ፰፥፲፪)፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ መስክረዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ጌታችን ሰው መሆን (ምሥጢረ ሥጋዌ) በተናገረበት በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ጌታችንን ብርሃን ብሎታል፡፡ ‹‹ሕይወት በእርሱ ነበረ፤ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፡፡ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሰነፈውም፤›› (ዮሐ. ፩፥፬-፭)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችን በሚያንጸባርቅ ብርሃን አምሳል እንደ ተገለጠበት ተናግሯል፡፡ ‹‹እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ በሔደ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሔዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንጸባርቅ አየሁ … አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለኝ፤›› (ሐዋ. ፳፮፥፲፫)፡፡
፫. ኖላዊ-ከታኀሣሥ ፳፩ እስከ ታኅሳስ ፳፯
ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው፡፡ ነቢያቱ ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደ ተዋቸው እና እንደ ተቅበዘበዙ በጎች በመቍጠር እንዲሰበስባቸውና እንዲያሰማራቸው እንዲህ እያሉ ይማጸኑ ነበር፤ ‹‹ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ (እረኛ) ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፤›› (መዝ. ፸፱፥፩)፡፡ ጌታችንም ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጥቷል፤ ‹‹ቸር ጠባቂ (እረኛ) እኔ ነኝ፡፡ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል፤›› (ዮሐ. ፲፥፲፩)፡፡
ዛሬም እኛ በኀጢአት ስንዋከብ ዘወትር ልናየውና ልንመላለስበት የሚገባን ብርሃነ ልደቱ ተሰውሮብናል፣ ከቸር እረኛችን የራቅን የተቅበዘበዝን በጎች ሆነናል፡፡ አንዳንዶቻችን በምናስበው ዐሳብ፣ በምንሠራው ሥራ ውስጥም የአምላክን ሰው የመሆን ምሥጢር ረስተነዋል፡፡ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንዳልተወለደ ነው፡፡ ስለዚህ ያጣነውን ይህን ጸጋ ለማግኘትና ብርሃነ ልደቱን ለማየት፣ በዚያ ውስጥም ለመመላለስ የክርስትናችንን እና የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት ለመጨመር መሻት አለብን፡፡ ስለዚህ እስኪ እኛም የብሉይ ኪዳን ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ እየዘከርን፣ ያለንበትን አኗኗር እየመረመርን፣ ስላጣነው ብርሃን ለማሰብ፣ ያጣነውን መልሰን ለማየትና ለማግኘት እንትጋ፡፡ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ በጉዳዩ ላይ በተመስጦ ለማሰብ እና ለመወያየት ጊዜ እንስጥ፡፡ ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንዲያበቃንም ‹‹አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ ቸሩ እረኛችን ሆይ፥ እባክህ ሰብስበን›› እያልን እግዚአብሔርን እንማጸነው፡፡ ሰው ከእነ ኀጢአቱ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ሊቀርብና ብርሃኑን ሊያይ አይቻለውምና በንስሐ ራሳችንን እናጽዳ፡፡ እነዚህን ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችልንን የዝግጅት ጊዜያት በሚገባ ከተጠቀምን ትርጕም ያለው፣ በሕይወታችንና በመንገዳችን ላይ ለውጥ የሚያመጣ ልዩ የልደት በዓል እናከብራለን፡፡ አምላካችን ብርሃነ ልደቱን እንድንመለከት ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር