‹‹እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ›› (ኢያ.፭፥፲፫)
ኅዳር ፲፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
በቅድስና፣ በውዳሴ፣ በኅብረ ቀለም፣ በመላእክት ዝማሬ በደመቀው በዓለመ መላእክት ውስጥ ቅዱሳን መላእክት በነገድ ተከፍለው ይኖራሉ፡፡ እነርሱም የዘወትር ምግባራቸው እንዲያውም ምግባቸው ፈጣሪን ማመስገን ነው፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክቱም በሦስቱ የመላእክት ከተሞች ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር በአላቃቸው ስር ሆነው ዘወትር አምላክን ያገለግላሉ፡፡ ለዚህም ድንቅ ሥራው ክብር ምስጋና ይድረሰውና፣ በኢዮር ከተማ የኃይላት አለቃ አድርጎ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ሾሞታል፤ ይህም የሆነበት ኅዳር ፲፪ ቀን የከበረ በዓል ነው፡፡ ስለዚህ የዚህን የከበረና የገናና መልአክ በዓሉን እንድናደረግ ቅዱሳን አባቶች ሥርዓት ሠሩልን፡፡
የስሙ ትርጓሜ ‹‹ማን እንደ እግዚአብሔር›› የሆነው የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤል፣ እንደ አምላክ ኃያል፣ ቸርና ርኅሩኅ ነው፤ በቅዱሱ መጽሐፍ ላይ ይህንን ነገር ራሱ መልአኩ ለነቢዩ ኢያሱ እንዲህ ሲል ገልጾለታል፤ ‹‹እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ›› (ኢያ.፭፥፲፫)
ሊቀ መለእክት ቅዱስ ሚካኤል፣ ለእኛ ሰዎች አማላጅ ሲሆን ለቅዱሳና ሰማዕታት ደግሞ አጋዣቸው የሆነው ነው፤ በሕይወታቸውና በተጋድሏቸውም እስከ መጨረሻው ይረዳቸዋል፤ እዚህ ላይ አንድ ታሪክ እናንሣ፡፡
እግዚአብሔርን የሚወድ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለ ጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ፣ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ፣ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የከበረ መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሰነጥቅ አዘዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ ፫፻ (ሦስት መቶ) የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጀላችሁ›› አላቸው፡፡
እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፤ የከበረ ገናናው መልአክም ‹‹ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፤ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፤ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡››
የኃይላት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከበዓሉ ረድኤት በረከት ይክፈለን፤ ጥበቃውና አማላጅነቱ ሁላችንም ይጠብቀን፤ አሜን!
ምንጭ፡- ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር