‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ›› (ሉቃ.፩፥፲፱)
ዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ
ታኅሣሥ ፲፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ ‹‹እግዚእ ወገብር፤ አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ›› ማለት ነው፤ ‹‹ሰላም ለዝክረ ስምከ ዘኢይተረጐም ምሥጢር ባሕቱ ይመስል ብሂለ እግዚእ ወገብር፤ ገብርኤል ሆይ ተመራምሮ ለማይደረስበት ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፤ ነገር ግን አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ይመስላል›› እንዲል፡፡ (መልክዐ ቅዱስ ገብርኤል)
ቅዱስ ገብርኤል የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት እና ሰው መሆን ለመናገር ተልኮ የምሥራች ዜናን ያበሠረ፤ በዲያቢሎስ የተንኮል ወጥመድ ገብተው ለተሰናከሉት ፈጥኖ ለርዳታ የሚደርስ፣ በጨለማ እና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉ የብርሃን ፋና ያበራ፣ ሰብአ ሰገልን የመራ መልአክ ነው፡፡ ከቀድሞ ጀምሮ ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ተልከው መንፈስ ቅዱስ እንዳናገራቸው ዓለምን ስለማዳን ከጽዮን የሚወጣ ከያዕቆብ በደልን የሚያርቅ ጌታ ‹‹ይወርዳል ይወለዳል›› በማለት በየወገናቸው እና በየዘመናቸው የተናገሩትን የነቢያትን ትንቢት ያስፈጸመና የምሥራችን ቃል የተናገር፣ የጨለማ አበጋዝ በሆነ በሰይጣን ተንኮል ከእፉኝት መርዝ የከፋ በሰው ልቦና ውስጥ አድሮ የነበረውን የኀዘን ስሜት ያጠፋ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡
ቅዱስ ገብርኤል እና ክብሩ
ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሁል ጊዜም ለደስታና ለምሥራች የሚላክ መልአክ ነው፤ በተለይም ስለ ልደተ ክርስቶስ ለድንግል ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ የምስጋና እና የክብር ሰላምታ ያበሠረ በመሆኑ ‹‹አብሳሬ ትስብእት (መልአከ ብሥራት) መጋቤ ሐዲስ›› ተብሎ ይጠራል፡፡
ቅዱስ ገብርኤል ከሌሎች መላእክት ተለይቶ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ አምላካቸውን ለማወቅ ‹‹መኑ ፈጠረነ›› እያሉ ሲባዝኑ ሳጥናኤል ‹‹እኔ ፈጠርኳችሁ›› ሲል ቅዱስ ገብርኤል ግን የፈጠረንን አምላክ እስክናውቅ ድረስ በያለንበት እንቁም እንጽና፤ ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ አምላክነ›› በማለት መላእክትን ያረጋጋ መልአክ ነው፡፡ (አክሲማሮስ. ገጽ.፴፭) በዚህም አባቶቻችን እንደሚሉት መልአኩን የመጀመሪያው የተዋሕዶ ሰባኪ ነው፡፡ ምክንያቱም ከፍጥረታት አስቀድሞ አምላኩን ዐውቆ ስብከት የጀመረ መልአክ ነውና፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታ ‹‹ወበእንተዝ ይደልዎ ከመ ይጹር ዜናሃ ለማርያም፤ድንግል ማርያምን ያበስር ዘንድ የተገባው ሆነ›› እንዲል፤ ነገረ ሥጋዌውን ለድንግል እንዲያበሥር አድሎታል፤ ከዚህ በኋላም ደጋግ ሰዎችን ለመርዳት የሚወጣ የሚወርድ ሆኗል፡፡
ቅዱስ ገብርኤል ከሌሎች መላእክት ተለይቶ ዘወትር በምንጸልያቸው ጸሎቶች ስሙ የሚጠራ መልአክ ነው፡፡ ይኸውም በዘወትር ጸሎቶች በአቡነ ዘበሰማያት፣ በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል፣ በውዳሴ ማርያም፣ በይዌድስዋ መላእክት እና በመሳሰሉት ጸሎቶች ዘወትር ስሙ የሚጠራ መልአክ ነው፡፡
ቅዱስ ገብርኤል ካህናት አባቶች እንደሚሉት ስእለት ሰሚ እንዲሁም ፈጥኖ ደራሽ መልአክ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በክርስቲያኖችም ዘንድ እጅግ ተወዳጅ መልአክ ነው፡፡ ስለዚህም ፈጥኖ ደራሹ መልአክ፣ ስእለት ሰሚው መልአክ ይባላል፡፡ በሀገራችንም ክብረ በዓሉ በቁልቢ ገብርኤል እና በተለያዩ ቦታዎች እጅግ በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ይከበራል፡፡
የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሌሎች መላእክት ሁሉ በይበልጥ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን እንደ ምትወደው በድርሳነ ገብርኤል ላይ ተጽፏል፤ ‹‹ርእዩኬ አኃዊነ ዘከመ ታፈቅሮ እግዝእትነ ማርያም ለቅዱስ ገብርኤል እምኲሎሙ መላእክት እስመ አብሠራ ልደተ ወልድ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ወውእቱ ከመ ያፈቅራ ወይረድኣ በጊዜ ምንዳቤሃ ለነኒ ይርድአነ በጊዜ ምንዳቤነ፣ ወንድሞቻችን ሆይ፥ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከመላእክት ሁሉ ይልቅ ቅዱስ ገብርኤልን በይበልጥ እንደምትወደው ተመልከቱ፤ የልጅዋን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከእርሷ መወለድ ያበሠራት እርሱ ነውና›› እንዲል፡፡ (ድርሳነ ገብርኤል ዘኅዳር ምዕራፍ ፪፥ ቁጥር ፲፫)
ቅዱስ ገብርኤል ብርሃናዊ መልአክ ነው፤ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ በራእዩ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች፡፡›› (ራእ.፲፰፥፩)
ነቢዩ ዳዊት ‹‹መላእክቱን የእሳት ነበልባል የሚያደርግ›› እንዳለው ቅዱስ ገብርኤል ነበልባላዊ መልአክ ነው፡፡ (መዝ.፻፫፥፬)
ቅዱስ ገብርኤል ኃያል መልአክ ነው፤ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ‹‹ብርቱ መልአክ ደመና ተጎናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዐምዶች ነበሩ፤ የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ፤ ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፤ እንደሚያገሳም አንበሳ በታላቅ ድምጽ ጮኸ›› በማለት መስክሯል፡፡ (ራእ.፲፥፩)
ቅዱስ ገብርኤል የመላእክት አለቃ ነው፤ በራማ በሠፈሩት ዐሥሩ የነገድ ሠራዊት ላይ የአርባብ አለቃ ነው፡፡ ነቢዩ ሄኖክም ‹‹በሠራዊት ሁሉ ላይ የተሾመ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው›› ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት የራማው መልአክ ተብሎ ይጠራል፡፡ (ሄኖክ.፲፥፲፬)
ቅዱስ ገብርኤል ፈጣን መልአክ ነው፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሉት በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ጊዜ በመስቀል ላይ የደረሰበትን መከራ አይቶ አላስችለው ቢል ሰይፍ ወርውሯል፤ ‹‹ዓለምም የሚያልፈው ቅዱስ ገብርኤል የወረወረው ሰይፍ ሲያርፍ ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መልኩም ሰይፍ እንደወረወረ ከዚህ በታች በተጻፈው መልኩ እንገነዘባለን ይኸውም፡-
ሰላም ለሰኰናከ ወለመከየድከ ክልኤ
ታሕተ ዐውደ መስቀል ዘቆማ በዕለተ ድልቅልቅ መውዋዔ
ሰይፈ ቁጥዓ ገብርኤል ዘመላኅከ ቅድመ ጉባኤ
አንስትሰ ሶበ ሰምዓ ቃለ ዚኣከ በቋዔ
ኀበ ሐዋርያት ሖራ ይንግራ ትንሣኤ
ትርጉም፡- ገብርኤል ሆይ፥ በዚያ ድብቅልቅና ሽብር በሆነበት ዕለት ከጌታ እግረ መስቀል ሥር ለቆሙት ተረከዞችህና ጫማዎችህ ሰላም እላለሁ፤ ገብርኤል ሆይ የጌታን ትዕግሥት የአይሁድን ግፍ ተመልክተህ በታላቅ ዐደባባይ ላይ ሰይፈ ቁጣህን አምዘገዘግኸው ቅዱሳት አንስት ግን ክርስቶስ ተነሥቷል ስላልካቸው የትንሣኤውን ምሥራች ይነግሩ ዘንድ ወደ ሐዋርያት ሄዱ›› እንዲል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ገብርኤል ከዓለም በፊት አምላኩን ያወቀ ዓለም ልታልፍ ስትልም የወረወረው ሰይፍ እንደሚያርፍ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡
በሀገራችን በተለምዶም ‹‹ሚካኤል እንደአየህ ገብርኤል እንዳያይህ›› የሚባል አባባል አለ፤ ይኸውም የመልአኩ ተራዳኢነት እንዳለ ሁኖ ተነግሮ ለማይሰማ አካል ግን መልአኩ ፈጣን እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም የቅዱስ ገብርኤልን ቁጣ የምንሰማ እና የምናይ ሲሆን ለምሳሌም ካህኑ ዘካርያስ የመልአኩን ቃል ባለመስማቱ (ባለመቀበሉ) ዲዳ ሁኗል፡፡በተጨማሪም በኢ-አማንያንም ዘንድ ሳይቀር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይፈራል፡፡ (ሉቃ.፩፥፲፩)
ቅዱስ ገብርኤል እና ተራዳኢነቱ
ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ሰማዕታትን ገድላቸውን እንዲፈጽሙ እሳቱንና ስለቱን ተሳቀው ወደኋላ እንዳይመለሱ ተጋድሏቸውን እንዲጨርሱ ይረዳቸዋል፡፡ (ዳን.፫፥፳፭) ክርስቶስ በስደት ሲሰደድም ሲመለስም እንዲናገር የተላከ መልአክ ነው፡፡ (ማቴ.፪፥፲፱፣ሉቃ.፪፥፰)
ቅዱስ ገብርኤል የእግዚአብሔር ባለሟል ነው፤ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነኝ›› እንዲል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ማለቱ ለእግዚአብሔር የተወሰነ ፊት ኖሮት ማለትም እንደ ንጉሥ ወታደር በእግዚአብሔር ፊት ተገትሮ የሚቆም መሆኑን ለመግለጽ አይደለም፡፡ ምንጊዜም ከእግዚአብሔር የማይለይ መሆኑን እና አማላጅነቱን ለመግለጽ ነው እንጅ፡፡ (ሉቃ.፩፥፲፱)
ቅዱስ ገብርኤል ምእመናንን የሚጠብቅ ጠባቂ መልአክ ነው፤ ስለዚህም ምሥክር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንመልከት፤ ‹‹በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለአንተ ያዛቸዋል፤እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል››እንዲል (መዝ.፺፩፥፲፩)፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል››(መዝ.፴፬፥፩)፤ ‹‹በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ፡፡››(ዘጸ.፳፫፥፳)
ቅዱስ ገብርኤል እና ክብረ በዓሉ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን መላእክትን ወርኃዊ እና ዓመታዊ በዓላቸውን በጸሎት እና በምስጋና ታከብራለች፡፡ በተለይም ታኅሣሥ ፲፱ ቀን የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል በዓል የሚከበርበት ምክንያት ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አግብርተ እግዚአብሔር አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን (ሠለስቱ ደቂቅን) ከእቶነ እሳት ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ በግእዝ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስም ‹‹ትማልም አሲረነ ሠለስተ እደወ ወደይነ ውስተ እቶነ እሳት ዮምሰ እሬኢ አርባዕተ እደወ እንዘ ያንሶሰዉ ማዕከለ እሳት ፍቱሐኒሆሙ ወገጹ ለራብዓይ ወልደ እግዚአብሔር ይመስል››፤ ትናንት ሦስት ሰዎች አስረን ከእሳቱ እቶን ጥለን ነበር፤ ዛሬ ግን ዐራት ሆነው ከእሥራታቸው ተፈትተው በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ ዐራተኛውም የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል፤ በማለት ይገልጸዋ፡፡ (ወዲያውም ከእቶኑ ሂዶ‹‹ አንትሙ ሲድራቅ ወሚሳቅ ወአብድናጎ አግብርተ እግዚአብሔር ንዑ ፃዑ ዝየ፤ ኑ ውጡ›› አላቸው ብር ብር እያሉ ከእሳቱ ውስጥ ወጥተዋል፤ በልብሳቸው ላይም ጥላሸት እንኳን አልተገኘም፤ ናቡከደነጾርም ይህን አይቶ አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ፤ ንጉሡም አዋጁን በአዋጅ መልሶ ለሕጻናቱ በሹመት ላይ ሹመት በክብር ላይ ክብር ጨምሮላቸዋል)፡፡
የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል በረከት እና ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይኑር፤ አሜን፡፡