እኔም ልመለስ!
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ኅዳር ፭፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ተስፋው ተፈጽሞ ደርሶ ቃል ኪዳኑ
አዳም ነጻ ሊሆን ሊፈጸም ማዳኑ
ከክብር ሊመለስ ቀርቶለት ባርነት
በደሉ ተፍቆ ዳግም ከልጅነት
ቤተልሔም ዋሻ ከኤፍራታ ምድር
ራሱን ዝቅ አርጎ በበረት ቢወለድ ስለ ሰዎች ፍቅር
ሊገድለው ቢነሣ ሄሮድስ በቅናት
ያኔ ድንግል ፈርታ እጅጉን ጨነቃት፡፡
ስደትን ጀመረች ታቅፋው አምላክን
የሚሣነው የሌለን የሚከውን ሁሉን
ክርስቶስን ይዛ የአፍላጋት ፈጣሪን
ርኃብን አስታግሦ የሚያረካ ጥምን
በርኅርኅት እናት ጨካኙ በዝቶባት
የሚሰጣት ስታጣ ውኃ ጥም ደርሶባት
አቤት ያስደንቃል የጌታ ትዕግሥቱ
በጥበቡ ሠሪ ሁሉን በጊዜያቱ
ሊመልሰው ቢሻ ስለ አዳም ተሰዶ
ስደትን መረጠ በሕፃንነቱ ወዶ ራሱ ፈቅዶ
ባርኮ ሊሰጣቸው ስደተ ጻድቃንን
ፈለጉን ለሚይዙ ሊተው አብትን
ሌት በጽልመት ግርማ ቀን በፀሐይ ሐሩር
ድንግል ተንገላታ ስለ ሔዋን ፍቅር
ስለ አባቷ አዳም ብድር
ከምድር የወደቀችን ቅንጣት ዘር በቸርነቱ አብዝቶ
ፍጥረቱን የሚመግብን ከእርሷ ጋር እርሱ ተገኝቶ
ከሰው ፊት ቆመች እናቱ
ርኅርኅት ቸር አዛኝቱ!
በብዙ ጭንቅ መከራ ከስደት እኛን መለሰን
ከጽልመት ወደ ብርሃን ከሞትም ሕይወት አገኘን፡፡
ከሲኦል አስፈሪው ወጥተን ገነትን ዳግም ወረስናት
ኀዘንን ራቅነውና ደስታን በእርሱ ለበስናት፡፡
ግና ግን! ዳግም በድዬ!
በጠላት ህሱም ራእይ አሁንም እኔ ታልዬ
ወደ ትዕቢት ከትሕትና
ወደ ርኩሰት ከንጽሕና
ከትጋት ሕይወት ወደ ስንፍና
መርጬ ብጓዝ ባርነት ገባሁ
ጭንቀቴ በዛ ነጻነት አጣሁ፡፡
እኔም ልመለስ ድንግል እናቴ
ከስደት ሕይወት ከባርነቴ
በልጅሽ ጉንጮች በወረደ ዕንባ
ባዘነው ልብሽ በተላበሰው የኀዘን ካባ
በእናት አንጀትሽ እንስፍስፍ ብሎ ያኔ በባባ
ተማጽኛለው መልሽኝ ድንግል ከጽድቅ መንደር
በሕጉ ልጓዝ ፍርሃት ርቆኝ በሰላም ልደር፡፡
ማስመሰል ይብቃኝ የታይታ ኑሮ
ውስጤ ተጎድቶ የላዬ አምሮ
ልመለስ ድንግል ሆይ እኔም ከስደት
እውነትን ልያዝ ልራቅ ከሐሰት፡፡
ጥላቻ ገዝቶኝ ወንድሜን ከጠላው
እምነት ምግባሬን ሰይጣን ዘረፈው
መልሽኝ ድንግል ይብቃኝ ግዞቱ
በምግባር እጦት በቁም መሞቱ!