አውጣኪ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እና የኬልቄዶን ጉባኤ – የመጀመሪያ ክፍል

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል

ጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

መግቢያ

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ በአንጾኪያና በግብጽ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ያወከና ታላቅ ብጥብጥ የፈጠረ በምሥጢረ ሥላሴ እምነት ላይ የተነሣ የተሳሳተ ትምህርት ነበር፡፡ ይኸውም አርዮስ ከእስክንድርያዊው መምህሩ ከአርጌኒስ በቀሰመው ትምህርት በዘዴ ‹‹ክብር ምስጋና ይግባውና እግዚአብሔር ወልድን ፍጡር ነው፤ አምላክም አይደለም፤›› ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሃሎ ወልድ›› (ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር) በግሪክኛ፡- ‹‹ኢን ፖቴ ኦቴ ኡክ ኢን›› ብሎ የክሕደት ትምህርት በማስተማሩ መላው የክርስትናው ዓለም ታውኮ ነበር፡፡ ይህ በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ አርዮስና ኑፋቄው በመወገዙ ችግሩ መፍትሔ አግኝቶ ነበር፡፡ ከ106 ዓመታት በኋላ ደግሞ ንስጥሮስ ከአንጾኪያ በአገኘው ትምህርት በቊስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን በምሥጢረ ሥጋዌ እምነት ላይ ስለ ክርስቶስ የተሳሳተ ትምህርት ያስተምር ጀመር፡፡

ይኸውም ንስጥሮስ 1ኛ ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አለው፤ 2ኛ/ ክርስቶስ ፍጹም ሰው እንጂ ፍጹም አምላክ አይደለም፤ እንዲሁም  3ኛ/ እመቤታችን ሰውን እንጂ አምላክን አልወለደችም፤ ስለዚህ እመቤታችን ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም (ሕስወኬ ትሰመይ ወላዲተ አምላክ፣ በአማን ትሰመይ ወላዲተ ሰብእ) ብሎ በማስተማሩ ይህ ኑፋቄ በ431 ዓ.ም. ላይ በታላቁ መምህር በእስክንድርያው ፓትርያርክ በቅዱስ ቄርሎስ አማካኝነት በኤፌሶን ጉባኤ ተወግዞ ችግሩ ተወግዶ ነበር፡፡ ሆኖም የንስጥሮስ የክህደት እምነት ጨርሶ ሳይጠፋ በዚያው በመካከ ለኛው ምሥራቅ በተለይ በፋርስና በባቢሎን እንዲሁም በኤዴሳ  ሲስፋፋ ቆይቷል፡፡ እንዲሁም ንስጥሮሳውያን በኤፌሶንና በቊስጥንጥንያ በብዛት ይገኙ ነበር፡፡

አውጣኪና ትምህርቱ

የንስጥሮስን ትምህርት በጥብቅ ይቃወሙ የነበሩት የግብጽ መነኰሳትና ካህናት ነበሩ፡፡ በቊስጥንጥንያም ቢሆን አያሌ የንስጥሮስ ተቃዋሚዎች ነበሩ፡፡ የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ ይቃወም የነበረና ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት እጅግ ቀናኢ የነበረ አውጣኪ የተባለ በቊስጥንጥንያ የአንድ ትልቅ ገዳም አበምኔት (መምህር) ነበር፡፡ አውጣኪ ‹‹ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አለው›› የሚለውን የንስጥሮሳውያንን ትምህርት አጥብቆ በመቃወም እሱ ወደ ተቃራኒው የባሰ ክህደት ውስጥ ገባ፡፡ አውጣኪ በቊስጥንጥንያ ‹‹ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብቻ አለው፤›› እያለ ያስተምር ጀመር፡፡ አባባሉ የቅዱስ ቄርሎስን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ይመስላል፡፡ አውጣኪ ግን ‹‹አንድ ባሕርይ›› ሲል የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ብቻ ማለቱ ነበር፡፡

በአውጣኪ አባባል ‹‹ሁለቱ ባሕርያት ማለት የሥጋና የመለኮት ባሕርያት በተዋሐዱ ጊዜ የመለኮት ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ውጦታል፤ አጥፍቶታል፡፡ ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ በኋላ በክርስቶስ ላይ የሚታየው የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው፤›› ይል ነበር፡፡ ይህ አባባል በእኛም ቤተ ክርስቲያን ማለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተወገዘ ነው፡፡ አውጣኪ በተጨማሪ ከሥጋዌ በኋላ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው ለማለት ‹‹ክርስቶስ ዘዕሩይ ምስሌነ በትስብእቱ›› ማለት ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ (በሥጋው) ከእኛ ጋር አንድ ነው›› የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ አነጋገር አይቀበልም ነበር፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት መሠረት ‹‹ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡›› ነገር ግን ፍጹም ሰው ካልሆነና እኛን ወክሎ በመስቀል ላይ በሥጋው መከራን ካልተቀበለ፣ የእኛ የሰዎች ድኅነት አስተማማኝ አይሆንም፡፡ በክርስቶስ የሥጋና የመለኮት ባሕርያት ተዋሕደው በመስቀል ላይ በአንድነት ባሕርዩ በተቀበለው መከራ ድኅነትን አግኝተናል፡፡

‹‹በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ ወይም ጠፍቶ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው›› የሚለውን የአውጣኪን የኑፋቄ (የክህደት) ትምህርት የሰማው የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ወዲያውኑ ደብዳቤ ጽፎ ስሕተቱን በማስረዳት አውጣኪ ከስሕተቱ እንዲታረምና ይህን ትምህርት እንዳያሰራጭ አስጠነ ቀቀው፡፡ አውጣኪ ግን የኑፋቄ ትምህርቱን አላቆመም፡፡ ከዚህ ላይ አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፤ ይኸውም አውጣኪ ክሪሳፍዮስ ለተባለው ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ኃይለኛ ጠቅላይ ሚኒስትር የንስሓ አባት ስለነበር የልብ-ልብ የተሰማው ይመስላል፡፡ ፓትርያርክ ፍላብያኖስም ይህንን ስለሚያውቅ ይመስላል አውጣኪን በጣም ሊጫነው አልፈለገም፡፡

ሆኖም ኃይለኛ የነበረ የዶሪሊያም ሊቀ ጳጳስ የነበረው አውሳብዮስ አውጣኪን አጥብቆ ስለ ተቃወመውና ስለ ከሰሰው፣ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ እንደተለመደው የመላው አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ተጠርተው ጉባኤ በማድረግ ፈንታ፣ በእርሱ ስር የሚተዳደሩትን ሃያ ዘጠኝ ጳጳሳትንና ሠላሳ ሦስት የገዳማት አበምኔቶችን ብቻ ሰብስቦ በእርሱ ሰብሳቢነት በ448 ዓ.ም. በቊስጥንጥንያ አህጉራዊ ሲኖዶስ አድርጎ የአውጣኪን የክሕደት ትምህርት መመርመር ጀመረ፡፡ አውጣኪ በጉባኤው ላይ እንዲቀርብ ሁለት ጊዜ ተጠርቶ ለመቅረብ አልፈለገም፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ሲጠራ ብቻ ቀርቦ ስለ ኑፋቄ ትምህርቱ ሲጠየቅ ግልጽ ያልሆነ የሃይማኖት መግለጫ በጽሑፍ አቀረበ፡፡

መግለጫው ግን ስለተከሰሰበት የክህደት ትምህርት ምንም አይገልጥም፡፡ ሆኖም የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ ግልጥ አድርጎ ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ ከእኛ ጋር አንድ ነው?›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ አውጣኪ አንድ አይደለም በማለት ካደ፡፡ ከክህደቱም እንዲመለስ ቢጠየቅ አሻፈረኝ አለ፡፡ ስለዚህ ጉባኤው አውጣኪን አወገዘው፡፡ ከአበምኔት ሹመቱና ከክህነት ሥልጣኑም ሽሮ ተራ ሰው አደረገው፡፡ የሮሙ ፖፕ ለቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› የሚል የሃይማኖት ፎርሙላ የያዘ ደብዳቤ ልኮለት ስለነበረ፤ አውጣኪ ይህንንም ነበር እንዲቀበል የተጠየቀው፡፡ ይህ ደግሞ ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር የተዛመደ ስለነበረ (ይህ አባባል መንፈቀ ንስጥሮሳዊ ይባላል) አውጣኪ አልቀበልም አለ፡፡

ስለዚህ አውጣኪ ‹‹የቅዱስ ቄርሎስን ሃይማኖት ስለመሰ ከርኩ እንጂ አንዳች የሃይማኖት ስሕተት ሳይኖርብኝ ያለ አግባብ ተወገዝኩ፤›› ብሎ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ አመለከተ፡፡ እንዲሁም ለሮም ፖፕ ለልዮን ቀዳማዊና ለእስክን ድርያው መንበረ ፓትርያርክ ለዲዮስቆሮስ ለሌሎችም ጳጳሳት ደብዳቤ ላከ፡፡ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስም በበኩሉ የአውጣኪን ኑፋቄና ጉባኤው ስለ እርሱ የወሰነውን ውሳኔ ለፖፕ ልዮን ላከለት፡፡ ፖፑም የጉባኤውን ውሳኔ በማጽደቅ ምሥጢረ ሥጋዌን የያዘ ደብዳቤ ለፍላብያኖስ በድጋሚ ላከለት፡፡ በደብዳቤውም ውስጥ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያትና አንድ አካል እንዳለው በግልጽ አስፍሯል፡፡ ይህም አባባል ከላይ እንደተገለጸው መንፈቀ ንስጥሮሳዊ ነው፡፡

ሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ (449)

አውጣኪ በቊስጥንጥንያ እጅግ የተከበረ ሰው ስለነበረና ብዙም ደጋፊዎች ስለነበሩት የእርሱ በ448 ዓ.ም. ጉባኤ መወገዝ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ እንደውም ያወገዘው ፓትርያርክ ፍላብያኖስ ንስጥሮሳዊ ነው እየተባለ ይወራና ይወቀስ ጀመር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የነገሩን ክብደት ተመልክቶ ምናልባትም በአውጣኪ ንስሓ-ልጅ በጠቅላይ ምኒስትሩ ተጽእኖ ይሆናል ዓለም-አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ሲኖዶስ በኤፌሶን እንዲደረግ ለጳጳሳቱ ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ስብሰባውም በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. በኤፌሶን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ባለፉት ሲኖዶሶች እንደተደረገው ሁሉ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ እንዲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ወሰነ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ በመሆኑ ሃያ ሦስት ከሚሆኑ ከግብጽ ጳጳሳት ጋር ቀደም ብሎ ኤፌሶን ደረሰ፡፡

ፖፕ ልዮን ግን ይህ ስብሰባ እንዲደረግ አልፈለገም ነበር፡፡ እንደውም ለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅ እኅት ለብርክልያ ንጉሡ ጉባኤውን እንዳይጠራ እንድታግባባው ጠይቋት ነበር፡፡ ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ በሐሳቡ ጸንቶ ጉባኤውን ስለጠራ ፖፑም ሦስት መልእክተኞች ላከ፡፡ በጉባኤው ላይ አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ተሰብስበው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ጉባኤው ስብሰባውን የጀመረው አንድ ሳምንት ዘግይቶ ቢሆንም የሮሙ ፖፕ እንደራሴዎች በዚህ ጊዜ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ የቊስጥንጥንያው ፓትርያርክ ፍላብያኖስም በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ተጠርቶ አልመጣም፡፡ የቀረበትንም ምክንያት አልገለጠም፡፡ ምናልባትም በእሱ ሰብሳቢነት የተሰበሰበው አህጉራዊ ሲኖዶስ ያወገዘው የአውጣኪ ጉዳይ እንደገና እንዲታይ በመደረጉ ቅር ብሎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊትም ብዙ መናፍቃን አርዮስም ጭምር መጀመሪያ በአህጉራዊ ሲኖዶሶች ከተወገዙ በኋላ ነበር ጉዳያቸው እንደገና በዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች እንዲታዩ የተደረገው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጳጳሳት ተጠብቀው ባይመጡም ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ የተገኙትን አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ጳጳሳት ይዞ በነሐሴ ወር 449 ዓ.ም. ስብሰባውን ጀመረ፡፡ ጉባኤው የተደረገው እንደበፊቱ በኤፌሶን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ጉባኤውም እንደተጀመረ አውጣኪ ተጠርቶ ስለተከሰሰበት ጉዳይ መልስ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡ አውጣኪ በቊስጥንጥንያ ሕዝብ እጅግ የተወደደና የተደነቀ ከመሆኑም በላይ በቃላት የሚጫወት ቅንነት የጐደለው ሰው ነበር፡፡ አውጣኪ በጉባኤው ፊት ቀርቦ በራሱ እጅ የተጻፈና የፈረመበት የእምነት መግለጫ አቀረበ፡፡ መግለጫውም ከመነበቡ በፊት ራሱ እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፡- ‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ በግልጥ በምነና (በብሕትውና) ለመኖር ነበር የምፈልገው፡፡ ዛሬ በሕዝብ መካከል በመገኘቴ ታላቅ ሐዘን ይሰማኛል፡፡ ሆኖም እምነቴን ለመመስከር ስለሆነ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነውንና አባታችን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ቄርሎስ ያስተማረውን እምነት በትክክል እቀበላለሁ፤›› አለ፡፡ ከዚህ በኋላ የጉባኤው ጸሓፊ የሚከተለውን የአውጣኪ የእምነት መግለጫ ማንበብ ጀመረ፤ መግለጫውም እንዲህ ይላል፡-

‹‹ሁሉን በያዘ፣ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ አምናለሁ፡፡ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ በሚሆን በአንድ ልጁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፤ ለእኛ ለሰዎች ሲል ለድኅነታችን ከሰማይ ወረደ፡፡ ሥጋ ለበሰ፤ ሰውም ሆነ፡፡ ታመመ፤ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ይመጣል፡፡ እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ የሚሉ፣ ከመወለዱም በፊት አልነበረም፤ ካለምንም ተፈጠረ የሚሉት፣ ከአብ ጋር በባሕርዩ የተለየ ነው የሚሉት፣ የእርሱ ሁለቱ ባሕርያት ተቀላቅለዋል ወይም ተዋውጠዋል የሚሉት፣ እነዚህ ሁሉ በአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የተወገዙ ናቸው፡፡ እኔም የምከተለው እምነት ይህ ነው፡፡ በዚህ እምነት እስካሁን ኖሬአለሁ፤ ወደፊትም እስክሞት ድረስ በዚሁ እኖራለሁ፡፡›› የሚል ነበር፡፡

አውጣኪ ይህንን ለጉባኤው ሲያስረዳ ተከትለዉት የመጡትም መነኰሳት አውጣኪ ያቀረበውና የተናገረው ትክክል መሆኑን ከዚያው በጉባኤው ፊት አረጋገጡ፡፡ ስለዚህ ይህን የሃይማኖት መግለጫ ከአዩና ከሰሙ በኋላ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ማለት የኢየሩሳሌሙ፣ የአንጾኪያው፣ የኤፌሶኑና የቂሣርው ዘቀጰዶቅያ አውጣኪ በእምነቱ ኦርቶዶክስ ነው በማለት ለጉባኤው አጽንተው ሲናገሩ ሁሉም አውጣኪ ከተከሰሰበት ኑፋቄ ንጹሕ መሆኑን በአንድ ድምፅ ወሰኑ፡፡ ከተላለፈበትም ውግዘት ፈቱት፡፡ ሥልጣነ ክህነቱንም መልሰውለት ወደ ቀድሞው የሓላፊነት ሥራው እንዲመለስ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ የሁለት ባሕርይን ሐሳብ ይቀበል የነበረው የዶሪሊያም ጳጳስ አውሳብዮስ አውጣኪን በመወንጀል መግለጫ ሲያቀርብ በዚያ የተሰበሰቡት መነኰሳትና ምእመናን በታላቅ ድምፅ ‹‹አውሳብዮስ ይቃጠል! አውሳብዮስ በሕይወቱ ይውደም! ክርስቶስን ለሁለት እንደ ከፈለ እሱም ለሁለት ይከፈል!›› እያሉ ይጮኹ ጀመር፡፡

የቊስጥንጥንያን ፓትርያርክ ፍላብያኖስንና አውጣኪን ያወገዙትን ጳጳሳት የሮሙን ፖፕ ልዮን 1ኛን ጭምር አውጣኪን ያለ አግባብ በማውገዛቸውና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀማቸው ጉባኤው ካወገዛቸው በኋላ፣ የሚከተለውን አጭር መግለጫ አወጣ፡- ‹‹ከኒቅያ እስከ ኤፌሶን አባቶቻችን በጉባኤ ተሰብስበው ከወሰኑት ሃይማኖት ሌላ የሚጨምር፣ የሚቀንስ ወይም የሚያሻሽል ቢኖር የተወገዘ ይሁን፡፡›› ዘግይተው የደረሱት የፖፑ መልእከተኞች ዩልዮስና ሬናቱስ የተባሉት ጳጳሳትና ዲያቆን ሂላሩስ ከፖፑ የተላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ እንዲነበብ ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ደብዳቤው ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› ስለሚልና ይህም ከንስጥሮስ ኑፋቄ ጋር ስለሚመሳሰል ጉባኤው እንዲነበብ አልፈቀደም፡፡ በዚህም ምክንያት የፖፑ መልእከተኞች ተቀይመው ወዲያውኑ በድብቅ ከጉባኤው ወጥተው ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ የጉባኤውም ውሳኔ በንጉሠ ነገሥቱ በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ጸደቀ፡፡ የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ በኤፌሶን 2ኛ ጉባኤ እንደተወገዘ ወዲያውኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

የዚህን ጉባኤ ውሳኔ ሲሰማ የሮሙ ፖፕ ልዮን ቀዳማዊ እጅግ ተናዶ ጉባኤውን ‹‹ጉባኤ ፈያት (የወንበዴዎች ጉባኤ)›› ብሎ ጠራው፡፡ የጉባኤውንም ሊቀ መንበር ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አወገዘው፡፡  ከእስክንድርያ ጋር የነበረውንም ግንኙነት ጨርሶ አቋረጠ፡፡ ፖፑ ይህን ሁሉ ያደረገው እሱ የላከው የሃይማኖት ነክ ደብዳቤ በጉባኤው ላይ ስላልተነበበና የእርሱም መልእክተኞች በጉባኤው ላይ በሙሉ ባለመካፈላቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ፖፑ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ የኤፌሶኑን ጉባኤ የዲዮስቆሮስ ጉባኤ ብሎ በመጥራት በጉባኤው ላይ ያለውን ቅሬታ ከገለጸ በኋላ፣ ሌላ ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ (ጉባኤ) እንዲጠራ ጥብቅ ሐሳብ አቀረበ፡፡ እንዲረዳውም የምዕራቡን ክፍል ገዥ (ንጉሥ) የነበረውን ሣልሳዊ ዋሌንቲኒያኖስን (Valentinianus III) እና ሚስቱን ንግሥት አውዶቅሲያን አጥብቆ ለምኖ ነበር፡፡

እነዚህም ባለሥልጣኖች እያንዳንዳቸው ሐሳቡን በመደገፍ ለንጉሠ ነገሥቱ ለዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ግን ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው የቅዱሳን አባቶች ጉባኤ መሆኑን ገልጦ በመጻፍ ስለ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩን ገልጦ አሳስቧቸዋል፡፡ በተጨማሪም የምዕራቡን ንጉሥና ንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ መክሯቸው ነበር፡፡ ፖፕ ልዮን ግን ሌላ ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስን አጥብቆ መጠየቁን ቀጠለ፡፡ ሆኖም የፖፑ ጥረት ሁሉ ውጤት አላስገኘም፡፡ ምክንያቱም ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ለ2ኛው የኤፌሶን ጉባኤ ታላቅ አክብሮት ስለነበረውና ውሳኔውንም በሚገባ ስላጸደቀው ነበር፡፡

የኬልቄዶን ጉባኤ

ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ከአለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በሐምሌ ወር 450 ዓ.ም. ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ በድንገት ከፈረስ ላይ ወድቆ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ቴዎዶስዮስ ወራሽ ስላልነበረው ለአልጋው ቅርብ የነበረች ታላቅ እኅቱ ብርክልያ (Pulcheria) ነበረች፡፡ ብርክልያ ግን በድንግልና መንኵሳ ነበር የምትኖረው፡፡ ሆኖም ብርክልያ ለሥልጣን ስለጓጓች ምንኵስናዋን አፍርሳ የሮም መንግሥት የጦር አዛዥ ጄኔራል የነበረውን መርቅያን (Marcianus) አግብታ በነሐሴ ወር 450 ዓ.ም. እሱ ንጉሠ ነገሥት እሷ ንግሥት ሆነው የሮምን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ ይህ የብርክልያ ምንኵስናን ማፍረስ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በተለይም በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም ነበር፡፡ የሮሙ ፖፕ ግን ከአዲሶቹ የሮም መንግሥት ንግሥትና ንጉሠ ነገሥት ዘንድ ተወዳጅነትን ለማግኘት ሲል ጋብቻቸውን በማወደስ አጸደቀላቸው፤ ቡራኬውንም ላከላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ፖፕ ልዮን ከቊስጥንጥንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ወዳጅነትን መሠረተ፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ ብሎም በጻፈው ደብዳቤ መጨረሻ ላይ እሱ የፈለገው ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ እንዲሰበሰብ አሳሰበ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ ነገሥቱ በመርቅያንና በፖፕ ልዮን መካከል ብዙ የወዳጅነት ደብዳቤዎች ተጻጽፈዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ መርቅያን በሥልጣኑ በ2ኛው በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው የፍላብያኖስ አስከሬን ፈልሶ በቊስጥንጥንያ በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር እንዲቀበር አደረገ፡፡ የተጋዙት ጳጳሳትም ከግዞት ወጥተው ወደየሥራቸው እንዲመለሱ አደረገ፡፡ በመሠረቱ በሲኖዶስ የተወገዙት ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለስ የሚችሉት በንጉሥ ትእዛዝ ሳይሆን በጳጳሳት ሲኖዶስ መሆን ስለነበረበት ንጉሡ ያደረገው ሕገ-ወጥ ሥራ ነበር:: ፖፑም የሱ ፍላጎት ስለነበረ ይህንን አልተቃወመም፡፡ በተቃራኒው ንጉሡ የተወገዙት ጳጳሳት ወደየሀገረ ስብከታቸው እንዲመለሱ የፍላብያኖስም አስከሬን ወደ ቊስጥንጥንያ ፈልሶ በክብር እንዲቀበር በማድረጉ ፖፕ ልዮን ለንጉሠ ነገሥቱ ልባዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መርቅ ያንና ንግሥቲቱ ብርክልያ 2ኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ ባቀረበው የሃይማኖት መግለጫ መሠረት ነፃ ያደረገውን አውጣኪንም ያለ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሰሜን ሶርያ እንዲጋዝ አደረጉ፡፡

ፖፕ ልዮን በአሳሰበው መሠረት ንጉሥ መርቅያን ጥቅምት 8 ቀን 451 ዓ.ም. ዓለም-አቀፍ ሲኖዶስ እንዲደረግ ለጳጳሳት ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤውም እንዲደረግ የታሰበው ከቊስጥንጥንያ 96 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ በኒቅያ ነበር፡፡ ነገር ግን በጸጥታ ምክንያት ከቊስጥንጥንያ 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቃ በምትገኘው በኬልቄዶን እንዲሆን ንጉሡ ስለ ወሰነ ጉባኤው በኬልቄዶን ሆነ፡፡ ንጉሥ መርቅያንና ንግሥት ብርክልያ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ጉባኤው በሥነ ሥርዓት መካሄዱን የሚቆጣጠሩ 18 ዳኞች በንጉሡ ተሠይመው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ዳኞች መሠየማቸው መንግሥት ሲኖዶሱን ምን ያህል እንደተቈጣጠረው ያመለክታል፡፡ የጉባኤው አባላት አቀማመጥ እንደሚከተለው ነበር፤

ዳኞቹ በመኻል ከዳኞቹ በስተግራ የፖፑ መልእክተኞች፣ ቀጥሎ የቊስጥንጥንያው አናቶልያስ፣ የአንጾኪያው ማክሲሙስ፣ የቂሣርያውና የኤፌሶኑ ጳጳሳትና ሌሎች የምሥራቅና የመካከለኛው ምሥራቅ አህጉር ጳጳሳት ሲሆኑ፣ በቀኝ በኩል ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ የኢየሩሳሌም፣ የተሰሎንቄ፣ የቆሮንቶስ፣ የግብጽ፣ የኢሊሪኩም፣ የፍልስጥኤም ጳጳሳትና ሌሎች ጳጳሳት ተቀምጠዋል፡፡ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገ ዙትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን የቂሮስ ኤጲስቆጶስ ቴዎዶሪጦስንና የኤዴሳን ኤጲስቆጶስ ኢባንን የዚህ ጉባኤ አባላት አድርገው ተቀበሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ብጥብጥ ተነሣ፤ የግብጽ ጳጳሳት በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዙትን ንስጥሮሳውያን ቴዎዶሪጦስንና ኢባንን ጉባኤው በአባልነት በመቀበሉ ‹‹አይሁዶችን፣ የክርስቶስን ጠላቶች ከዚህ አስወጡ!›› እያሉ በመጮኽ ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡ ጉባኤው ግን የእነሱን ጩኸት ከቁም ነገር አልቈጠረውም፡፡

ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት በተራ የመሩት ከመንግሥት የተሠየሙት ዳኞችና የሮሙ ፖፕ መልእከተኞች ነበሩ፡፡ የሮሙ ተወካዮች ጉባኤውን ሲመሩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ከአሁኑ በስተቀር ባለፉት ዓለም-አቀፍ ሲኖዶሶች ሁሉ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ከሊቃነ መናብርቱ ዋናው ነበር፡፡ አሁን ግን የእስክን ድርያውን ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስን ለመኰነን የተሰበሰበ ሲኖዶስ ስለሆነ ዲዮስቆሮስ ከሊቃነ መናብርቱ አንዱ አልሆነም፡፡ የጉባኤው አባላት ቦታቸውን ይዘው እንደተቀመጡ የሮሙ ፖፕ ተወካይ ፓስካሲኑስ (Paschasinus) ተነሥቶ ለዳኞቹ ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ከተቀመጠበት ቦታ ማለት ከጉባኤው እንዲነሣና ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ አመለከተ፡፡ የመንግሥቱ ዳኞች ለምን ይነሣል ብለው በጠየቁ ጊዜ፣ ሌላው የፖፑ መልእክተኛ ሊሴንቲያስ (Licentius) የተባለው ዲዮስቆሮስ ከዚህ በፊት የሮሙ ፖፕ ሳይፈቅድ በሥልጣኑ ሲኖዶስ (የ449 ሲኖዶስን ማለቱ ነው) እንዲካሄድ አድርጓል በማለት ክስ አቀረበ፡፡

ይህ ግን መሠረት የሌለው ክስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የተደረጉት ሲኖዶሶች ሁሉ የተጠሩትና የተካሄዱት በሮም ንጉሠ ነገሥት ፈቃድና ትእዛዝ እንጂ በሮሙ ፖፕ ፈቃድ አልነበረም፡፡ ያለፈውም የሁለተኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ የተጠራው በዳግማዊ ቴዎዶስዮስ ትእዛዝ እንጂ በፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሥልጣን አልነበረም፡፡ ስለዚህ የቀረበው ክስ ዳኞቹን አላረካ ቸውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በፈቃዱ ቦታውን ለቆ ተከሳሾች በሚቀመጡበት ቦታ ሄዶ ተቀመጠ፡፡ የሮሙ ፖፕ ተወካዮች በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ፓትር ያርክ ዲዮስቆሮስ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና አፍርሷል ሲሉ ከሰሱ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሲመልስ እሱ በንጉሠ ነገሥቱ በቴዎ ዶስዮስ ትእዛዝና ጥያቄ መሠረት ነው ጉባኤውን የመራው፡፡ እሱ ቀኖናን አፈረሰ? ወይስ በኤፌሶን ጉባኤ የተወገዙትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን የቂሮስ ኤጲስ ቆጶስ ቴዎዶሪጦስንና የኤዴሳን ኤጲስቆጶስ ኢባንን የዚህ ጉባኤ አባላት አድርገው የተቀበሉት እነሱ ናቸው ቀኖና አፍራሾች? ብሎ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሆኖም ይህ የፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ጥያቄ ምንም መልስ ሳይሰጠው በዝምታ ታለፈ፡፡

ይቆየን