አእመረ አሸብር “የቅዳሴ ሥርዓት” ሲያካሔድ በቁጥጥር ሥር ዋለ
በእንዳለ ደምስስ
በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኑፋቄው ምክንያት የተወገዘው አእመረ አሸብር ከግብረ አበሮቹ ጋር በግለሰብ ቤት ውስጥ “የቅዳሴ ሥርዓት” ሲያካሔድ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡
“መዳን በማንም የለም” በሚል ርእስ በ፳፻፲፩ ዓ.ም ባሳተመው የኑፋቄ መጽሐፉ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዞ የተለየው አእመረ አሸብር በአርባ ምንጭ ከተማ በጫሞ ቀበሌ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከግብረ አበሮቹ ጋር ቅዳሴ እንቀድሳለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ንዋያተ ቅድሳት በመጠቀም ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ክክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር የማይገናኝ ተራ ነገር በማቅረብ “ሥጋ ወደሙ” ነው በማለት፣ የመጾር መስቀል በመጠቀም “የቅዳሴ ሥርዓት” ሲያካሄዱ እንደነበር ከሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዓርብ የካቲት ፰ ቀን ጀምሮ እስከ እሑድ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ጉባኤ ማዘጋጀታቸውንና ዓርብና ቅዳሜ የትምህርትና የምክክር ጉባኤ፣ እሑድ “ቅዳሴ” እናካሒዳለን በማለት ቀደም ብለው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ በለቀቁት ማስታወቂያ እንዲሁም ከተማው ላይ ማስታወቂያ በባነር አሠርተው በይፋ መስቀላቸውን የዓይን እማኞች ገልጠዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ኮሚቴ፣ የአርባ ምንጭ ደ/መ/መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ፣ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች እንዲሁም ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በመሆን ወደ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሄድ ጉዳዩን አሳውቀዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም ቅዳሜ የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም “የቤተ ክርስቲያንን ንዋያተ ቅድሳትን ስለማስከበር” በሚል ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው መፍትሔ እንዲፈልጉ ለአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት፣ ለአርባ ምንጭ ከተማ ፍትሕና ፀጥታ ጽ/ቤት፣ ለጋሞ ጎፋ ዞን ፍትሕና ፀጥታ ጽ/ቤት፣ ለጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ለሚመለከታቸው አካላት በላኩት ደብዳቤም ከዚህ ቀደም በኑፋቄያቸው በሀገረ ስብከቱ ተወግዘው የተለዩ ግለሰቦች ቅዳሴ እንቀድሳለን በማለት ቤተ ክርስቲያን ላይ በማላገጥና የራሷን የሆኑትን ቅዳሴዋንና ንዋያተ ቅድሳቷንና ከራሷ ያገኙትን መዓርግ በመያዝና በመጠቀም በ፲/፮/፳፻፲፩ ዓ.ም ፕሮግራም ሊያካሔዱ ማሰባቸውን ያስረዳል፡፡ ፕሮግራም እንደሚያካሄዱም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ በመልቀቅ ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንን ያስቆጣ ድርጊት በአርባ ምንጭ ደ/መ/መድኃኔዓለም ሰበካ ጉባኤ የቀረቡ የሕዝብ አቤቱታዎች እንደደረሳቸው የገለጹት ብፁዕነታቸው የሚመለከተው አካል ለሰላም ሲባል ትልቅ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ ሊሰጥ ይገባዋል በማለት አሳውቀዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በተጨማሪም በዚሁ አቤቱታቸው “የዚህች ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የሀገረ ስብከቱ አቋም ሰላምን መስበክ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው ከዚህች ቤተ ክርስቲያን እስከወጡ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን መገልገያ ንብረቶች (ንዋያተ ቅድሳት) ሥርዓቷንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ያገኙትን መዓርጋት ሊተዉና የራሳቸውን እምነት ሊያካሔዱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የራሳቸውን ፕሮግራም ማካሔዱን እንደማይቃወሙና የቤተ ክርስቲያን የሆኑትንም ንብረቶች እና ሥርዓቶች ሊመልሱ ይገባል ብለዋል፡፡
እሑድ ጠዋት በቦታው መረጃው የደረሳቸው የሕግ አካላት ባለመገኘታቸው ከፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ኮሚቴ፣ ከሰበካ ጉባኤ እንዲሁም ከስብከተ ወንጌል የተውጣጡ አባላትና ወጣቶች እንዲሁም ምእመናን ተሰባስበው ቅዳሴ ወደሚያካሔዱበት ቤት በመሔድ ግለሰቦቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት እንዲመልሱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የለበሱትን ልብሰ ተክህኖ በማስወለቅ፣ ከበሮ፣ መስቀል፣ መጻሕፍትና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት ይዘው ወደ አርባ ምንጭ ደ/መ/መድኃኔዓለም ሲመለሱ፣ የሕግ አካላትም በመድረስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ሥር በማዋል ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡
ሰኞ ጠዋት የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጽ አስፈላጊና ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗ ጥያቄ እንዲመለስ በማለት በብፁዕነታቸው የተጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ በመያዝ ለሚመለከተው አካል ቢያመለክቱም የሚመለከተው አካል ደብዳቤውን ተቀብሎ ጉዳዩ ከባድ በመሆኑ ከዞኑና ከከተማው ኃላፊዎች ጋር መመካከር አለብን በማለቱ ክስ እስካሁን አለመመሥረቱ ተገልጿል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሲኖዶስ እያከናወነ ስላለው ጥረት ሲገልጹ “ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን መገለጫ የሆኑትን ያሬዳዊ ዜማና ንዋያተ ቅድሳት ለማስጠበቅ ውይይቶችን ሲያደርግ እንደቆየና በአሁኑ ወቅትም የአእምሮ ንብረት በሚል ኮሚቴ ተቋቁሞ በጥናት ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከትም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አማካይነት የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አዋቅሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጠዋል፡፡
በሕግ አካላት ቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ አእመረ አሸብር ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበረና በኑፋቄው ምክንያት የተወገዘ ግለሰብ ነው፡፡ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ጠዋት ከፖሊስ ጣቢያ እንደተለቀቁም የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡