አንቲ ውእቱ ጽጌ መዓዛ ሠናይ (ውዳሴ ማርያም ዘእሑድ)
መ/ር ዘለዓለም ሐዲስ
ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያለው ዘመን ወርኀ ጽጌ በመባል ይታወቃል፡፡ወርኀ ጽጌም የተባለበት ምክንያት ዕፀዋቱ አብበው ምድርን በአበባነታቸው አሸብርቀው የሚታዩበት ወር በመሆኑ ነው፡፡ጽጌ ማለት ጸገየ አበበ ካለው የግእዝ ሐረግ የተመዘዘ ሲሆን ጽጌ ትርጉሙ አበባ ማለት ነው ጌታችን በጽጌ መስለው የተናገሩ ነቢያት ናቸው ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ኢሳይያስ ጌታን ከዕሤይ ሥር በትር ትወጣለች ከርሷም አበባ ይገኛል በማለት ጌታን በአበባው እመቤታችን በበትር መስሎ ተናግሯል፡ንጉሥ ሰሎሞንም በመኃልዩ“ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ በምድራችን አበባ ታየ”በማለት ጌታን በአበባ እመቤታችን በምድር ይመስላታል(ኢሳ ፲፩፥፩)
የዘመነ ሐዲስ ሊቃውንትም የነቢያትን ምሳሌያዊ ምስጢር ከማብራራታቸው በተጨማሪ እመቤታችን በጽጌ በአበባ፣ልጇን ከአበባው በሚገኘው ፍሬና መዓዛ መስለው ተናግረዋል ከእነዚህ ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ኤፍሬም “አንቲ ውእቱ ጽጌ መዐዛ ሠናይ እንተ ሠረጸት እምሥርወ ዕሤይ ከዕሤይ ሥር የተገኘች መዓዛዋ ያማረ ጽጌ አንቺ ነሽ በማለት እመቤታችን በአበባ (በጽጌ) ልጇን በመዓዛው መስሎ ተናግሯል ሌሎችም ሊቃውንት ተመሳሳይ ምሳሌ በመመሰል ምስጢረ ሥጋዌውን አብራርተዋል፡፡
ይህ ወራት በቀደሙት አባቶቻችን ዘንድ እስከ ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘመነ ጽጌ እየተባለ እግዚአብሔር ምድርን በአበባ ማስዋቡ በቤተ ክርስቲያን ቢዘከርም እንደ አሁኑ ማኅሌተ ጽጌ ሰቆቃወ ድንግል እየተቆመ የእመቤታችን ስደት አይታሰብበትም ነበር፡፡ወቅቱ እግዚአብሔር ምድርን በአበባዎች የሚያስጌጥበት ስለሆነ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የሚያስውቡትን የሽቱ ዕፀው ናርዶስ ቀንሞስ ሮማን የመሳሰሉትን እያነሣ ምድር በእነዚህ ሁሉ አበባዎች እንዳጌጠችና እንደተዋበች የተናገረውን የየየቀኑን መዝሙር እየዘመረች ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን ታመሰግንበት ነበር፡፡በኋላ ግን ከቅዱስ ያሬድ ቀጥለው የተነሱት ሊቃውንት ስለእመቤታችን መሰደድ ድርሰት የደረሱ ሊቃውንት የነቢያትን ምሳሌ መነሻ በማድረግ እመቤታችን አበባውን በሚያስገኙ ያማሩ ያማሩ የሽቱ ዕፀው፣ልጇን በጽጌ በአበባ እየመሰሉ ማኅሌተ ጽጌና ሰቆቃወ ድንግልን ከደረሱ ማኅሌቷንም መቆም ከጀመሩ በኋላ ወርኃ ጽጌ ተብሎ ከመታሰቡ በተጨማሪ የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ሁኖ መከበር ጀምሯል፡፡
በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ዜና ማርቆስ አስተማሪነት ከአይሁዳዊነት ወደ ክርስቲያንነት የተመለሰው አባ ጽጌ ብርሃንና (ጽጌ ድንግል) አባ ገብረ ማርያም መምህር ዘደብረ ሐንታው ሁለቱ ማኅሌተ ጽጌንና ሰቆቃወ ድንግልን ደርሰው የእመቤታችን ስደት እያሰቡ ማኅሌት መቆም ከጀመሩበት ከ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ማኅሌቱ ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ምእመናንንም የእመቤታችን ስደት ለማስታወስ በእመቤታችን ስም ማኅበር እየጠጡ ምንም ጾሙ የፈቃድ ቢሆንም ጾም እየጾሙ ዝክር እየዘከሩ ያከብሩታል ማኅበሩም የሚጠጣው በቤተ ክርስቲያን ወይም በተራራ ላይ ነው ከቤታቸው የማይጠጡበት ምክንያት እመቤታችን በረሃ ለበረሃ ስለተሰደደች ያንን ለማስታወስና እንደ እመቤታችን በመንገድ የደከመን እንግዳ ለመቀበል ነው፡፡
የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ የሆነው አባ ጽጌ ብርሃን (ድንግል) ከመጠመቁ በፊት ዘካርያስ ተብሎ ይጠራ ነበር ለማመን ያበቃችውም ገባሪተ ኃይል የሆነች የእመቤታችን ሥዕል ናት ብዙ ተአምራትን ስታደርግ ስላየ ወደአባ ዜና ማርቆስ በመሔድ ተምሮ ለማመን በቅቷል ከአባ ዜና ማርቆስ ትምህርተ ሃይማኖትን ተምሮ በምንኵስና ሕይወት መኖር ከጀመረ በኋላም ያችን ለማመን ያበቃችውን ገባሪተ ኃይል ሥዕል ሳይሳለም አይውልም ነበር፡፡
ከሥዕሏ ፊትም ሲቆም የሚያቀርበው እጅ መንሻ (መባዕ) ስለሌው ይጨነቅ ነበር በኋላ ግን ይህ ዘመነ ጽጌ ሲደርስ በየቀኑ ሃምሳ ሃምሳ የጽጌረዳ አበባ እየፈለገ እንደ ዘውድ እየጎነጎነ ለዚያች ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል ያቀዳጃት ነበር በጋው ሲወጣ የጽጌረዳው አበባ ስለደረቀበት ከሥዕሏ ተንበርክኮ እመቤቴ በየቀኑ የማመጣልሽ የጽጌረዳ አበባ ደረቀ ስለአበባው ፈንታ መልአኩ ተፈሥሒ ተፈሥሒ እያለ ያመሰገነሽን ምስጋና በአበባው ቁጥር ልክ ሃምሳ ሃምሳ ጊዜ እንዳመሰግንሽ ፍቀጅልኝ በማለት ተማጸነ ከዚህ በኋላ በየቀኑ ተፈሥሒ ፍሥሕት የሚለውን የመልአኩን ምስጋና በየቀኑ ሲያቀርብላት ምስጋናው እንደጽጌረዳ አበባ እየሆነ ከአንደበቱ ሲወጣ እመቤታችን አበባውን እየተቀበለች ስትታቀፈው ሰዎች እያዩ ያደንቁ እንደነበር ገድለ ዜና ማርቆስ ያስረዳል፡፡
እሱም በድርሰቱ እንዲህ ሲል ገልጾታል“አባዕኩ ለኪ ስብሐተ ተአምር ዘይሤለስ በበሃምሳ ህየንተ ጽጌያት ሃምሳ ለስዕልኪ አክሊለ ርእሳ” ለስዕልሽ ዘውድ ይሆን ዘንድ ሃምሳ የጽጌ ረዳ አበባ አቀርብልሽ ስለነበረው ፈንታ ሦስት ጊዜ ሃምሳ(መቶሃምሳ) የሚሆን ምስጋናን አቀረብኩልሽ በማለት፡፡ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ምድርን በአበባ ማስጌጡን ማሰባችን እንዳለ ሁኖ በተጨማሪ የእመቤታችን የስደቷን በዓል እናስብበታለን፡፡
ስለምን ወደግብፅ ተሰደደ?
ጌታችን ከመወለዱ በፊት ከጽንሰቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ስለሚሠራው ሥራ አስቀድሞ በነቢያቱ እያደረ ትንቢት አናግሯል፡፡ መልአኩም ለዮሴፍ ብላቴናውን ሄሮድስ እንደሚገድለው ሲነግረው የሚሸሽበትን ቦታ ሳይቀር “ተንሥእ ንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወሑር ውስተ ብሔረ ግብፅ” ተነስተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደግብፅ ሽሽ በማለት ለስደቱ ግብፅን እንደመረጣት በትንቢቱ ተናግሯል(ማቴ፪፥፲፫) ከደቂቅ ነቢያት አንዱ ሆሤዕም ጌታችን ወደግብፅ እንደሚሰደድ “እምግብፅ ጸዋእክዎ ለወልድየ ልጄን ወደግብፅ ጠራሁት” ሲል ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ደግሞ “ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደግብፅ ይወርዳል በማለት ተናግሯል (ሆሴ፲፩፥፩ ኢሳ ፲፱፥፩)ከሌሎች ሀገሮች ለስደቱ ግብፅ የተመረጠችበት ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡
፩.ለፍቅሩ ስለሚሳሱለት፤ ጌታችን ወደግብፅ የተሰደደበት ምክንያት ግብፃውያን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ጌታችን ከምንም በላይ ለፍቅሩ ይሳሱለት ስለነበረ ነው፡፡ይህንም ወደ ግብፅና ወደ ኢትዮጵያ በተሰደደ ጊዜ ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያን እንዴት አክብረው እንደተቀበሉትና እንደሳሱለት በነገረ ማርያም የተጻፈው ታረክ ጥሩ ማስረጃ ነው ምንም ሰይጣን ያደረባቸው እነ ኮቴባን የመሰሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎች ቢያጋጥሟቸውም ብዙዎቹ ደግሞ ለፍቅሩ በመሳሳት“ደም ግባቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ያምራል”ተብሎ የተነገረለትን መልኩን በማየት ብቻ ለማመን የበቁ ደጋጎች ነበሩ እንኳን ቤት መስርተው በዓለም የሚኖሩት በበረሃ ውስጥ የሚኖሩ ሽፍታዎችም ለጌታችን ያሳዩት ርኅራኄና ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስና እመቤታችን ዮሴፍና ሰሎሜ ኢየሩሳሌምን ለቀው ወደ ግብፅ ሲሰደዱ ግብፃዊው ጥጦስና አይሁዳዊ ዳክርስ ሁለት ወንበዴዎች በረሃ ውስጥ አግኝተዋቸው ነበር እስራኤላዊዉ ዳክርስ ልብሳቸውን ለመግፈፍ ሲፋጠን ግብፃዊዉ ጥጦስ ግን በልቡናው ርኅራኄ አድሮበት ለፍቅሩ በመሳሳት እነዚህ ሰዎች የቤተ መንግሥት ሰዎች ናቸው አሳዘኑኝ ወደ ዚህ ቦታ የመጡት ያለ ምክንያት አይሆንምና አንቀማቸው እንተውላቸው በማለት ለጌታ ያለውን ፍቅርና ርኅራኄ ገልጧል
ወደ ኢትዮጵያም በመጡበት ወራት ቤታቸውን እየለቀቁ ያስተናግዷቸው እንደ ነበር ድርሳነ ዑራኤል በሰፊው ይናገራል እመቤታችንም የኢትዮጵያ ሰዎች ባሳዩአት ፍቅር ስትደሰት ጌታችን የዐሥራት ሀገር ትሁንሽ ብሎ ሀገሪቱን ለእመቤታችን የሰጣት በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ባሳዩት ደግነትና ርኅራኄ ነው፡፡ደጉ አባት አብርሃም እንግዳ በመቀበሉና ደግ በመሆኑ ሥላሴ ከቤቱ እንደ ገቡለት ሎጥም እንግዳ በመቀበል መላእክት ወደ ቤቱ ገብተው ሰዶምና ገሞራ ሲጠፉ ከጥፋት እንደታደጉት ጌታችን አባቶቻችን ባደረጉት ደግነት ኢትዮጵያ በእመቤታችን ምልጃ ሊጠብቃት ስለፈለገ የዐሥራት ሀገር አድርጎ ሰጣት ምን ጊዜም ሊምረው የወደደውን ሰው የእመቤታችን ፍቅር ያሳድርበታልና እመቤታችን እንድንወድ አድርጎ በአማላጅነቷ እንድንጠበቅ ፈቀደልን ጌታችን ወደ ግብፅና ወደ ኢትዮጵያ የተሰደደበት ምክንያት ለፍቅሩ ይሳሱለት ለነበሩት ኢትዮጵያና ግብፅ በፍቅር ለመገለጽ ሲሆን በተጨማሪም ገዳማተ ግብፅንና ገዳማተ ኢትዮጵያንም ለመባረክ ጭምር ነው፡፡በግብፅና በኢትዮጵያ ያሉ ታላላቅ ገዳማት የተባረኩት በስደቱ ወራት ነውና፡፡
፪ ኪዳነ መልከ ጼዴቅን ለመፈጸም ነው፤መልከ ጼዴቅ ከዘመዶቹ ተለይቶ በምናኔ ሲኖር በሚያቀርበው መሥዋዕት በሚጸልየው ጸሎት በሥጋ ዘመዶቹ የሆኑትንና የማይዘመዱትን እንዲምርለት እግዚአብሔርን ይለምነው ነበር እንዲህ እያለ አቤቱ ለዲያብሎስ ከመገዛት ለአንተ ወደ መገዛት መልሰኸኛልና ከሀገሬም አውጥተህ አንተን ወደማመልክበት ቦታ አምጥተኸኛልና በደሌንም ይቅር ብለህልኛልና አመሰግንሃለሁ ነገር ግን እኔን ይቅር እንዳልከኝ ዘመዶቼንም ማርልኝ፡፡እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀብሎ እንዲህ ሲል ድምፁን አሰምቶታል ልጄን ወደ ግብፅ በጠራሁት ጊዜ ዘመዶችህን እምርልሃለሁ ብሎ ቃለ ኪዳን ገብቶለት ነበር ዘመኑ ሲደርስ የተናገረውን የማያስቀር እግዚአብሔር የገባለትን ቃለ ኪዳን ለመፈጸም ወደግብፅ ተሰደደለት (ተረፈ ቄርሎስ ፳፭፥፩—፱) ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ መልአከ እግዚአብሔርን ከመካከላቸው እንደ ዳኛ አስቀምጦ ለሦስቱ ልጆቹ ለሴም ለካም ለያፌት ይህን ዓለም ቀኝ ቀኙን ለሴም መሀሉን ለያፌት ግራ ግራውን ለካም አውርሷቸዋል መልከ ጼዴቅ ትውልዱ ከካም ወገን ስለሆነ ምንም ዘመዶቼን ማርልኝ ብሎ የጸለየ ለሁሉም ዘመዶቹ ቢሆንም የአባቱ ወገኖች የካም ዘሮች ናቸውና ጌታ ወገኖቹን ሊምርለት ቃል ኪዳኑን ሊፈጽምለት ወደግብፅ ተሰዷል
፫.አጋንንትን ከግብፅና ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለመስደድ ነው
ጌታ ገና ከመወለዱ በፊት ለልደቱ ሃያ አራት ቀን ሲቀረው መካነ ልደቱ ቤተ ልሔምን በመላእክት አስጠብቋት ነበር፡፡በዚህ ጊዜም አጋንንት በመላእክት ረቂቅ ጦር እየተወጉ ኢየሩሳሌምን ለቀው ሲወጡ የተሰደዱት ወደ ግብፅ ነበር አጋንንት በውስጣቸው አድርው ይመለኩባቸው የነበሩ ጣዖታትም ተሰባብረው ጠፍተዋል ይህንንም ጌታ ወደ ግብፅ በተሰደደ ጊዜ ራሳቸው አጋንንት በኢየሩሳሌም ማደሪያ እንዳሳጣኸን በዚህም ልታሳድደን መጣህን ብለው እንደ መሰከሩ በነገረ ማርያም ተጽፏል ጌታ ወደግብፅ የተሰደደበት ሦስተኛው ምክንያት እነዚህ አጋንንት ማደሪያ ካደረጓቸው የሰው ልቡናናና ከጣዖቱ አስወጥቶ በመስደድ አጋንንትን ለማሳደድ ነው፡፡ ይህንም ቴዎዶጦስ የተባለው ሊቅ ጌታ ተሰደደ ሲባል ብትሰማ ፍጡር ነው ብለህ አትጠራጠር ፈርቶ ሸሸም አትበል የጌታ መሰደድ ዲያብሎስን ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለማሳደድ እንደሆነ እመን እንጅ ብሎ የተሰደደ ዲያብሎስን ለማሳደድ መሆኑን ገልጧል (ተረፈ ቄር፲፥፭)ይህ ሊቅ ጌታ የተሰደደው ዲያብሎስን ለማሳደድ ብቻ ሳይሆን ሰው መሆኑን ለሚጠራጠሩ፣ምትሐት ነው ለሚሉትም በትክክል ሰው መሆኑን ለማስረዳት እንደ ተሰደደ በዚሁ ምዕራፍና ቁጥር ይገልጻል ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበር ፡፡
፬.አዳም ከዚህ ዓለም አፍአ በምትሆን ከገነት ተሰዶ ነበርና ለመካስ
ጌታችን በዕለተ ልደቱ የበለስ ቅጠል የለበሰ አህዮችና ላሞች እስኪያሟሙቁት ድረስ የተበረደ አዳም ከገነት ሲወጣ የበለስ ቅጠል ስለለበሰ ከልብሰ ብርሃን በመገፈፉ ስለተበረደ አዳም የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ለመካስ ነው፡፡ገና በሁለት ዓመቱ ከኢየሩሳሌም ወደግብፅ የተሰደደውም ከዚያው ሁኖ መዳን ተስኖት ሳይሆን አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት እንደ ተሰደደ እሱም ከኢየሩሳሌም ወደ ምድረ ግብፅ ተሰዶ አዳም የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ለመካስ ነው፡፡አዳም ከገነት ወደ ማያውቀው ወደዚህ ዓለም ሲሰደድ ብዙ ፍዳና መከራ አግኝቶታል ፡ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ በሚያደርገው እንቅስቃሴ እሾሁ ሲወጋው እንቅፋቱ ሲመታው ይህ ሁሉ የደረሰበት ከፈጣሪዉ ትእዛዝ በመውጣቱ መሆኑን ሲያስብ ዕንባው ከዓይኑ ያለማቋረጥ እንደምንጭ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡
በገነት ሳለ የሚበላውና የሚጠጣው ከሰውነቱ ጋር ተዋሕዶ ይቀር ነበር እንጅ ወደ ኀሠርነት ስለማይለወጥ በልቶ ጠጥቶ መጨነቅ ሆድ ቁርጠት በልቶ መታመም በቁንጣን መሰቃየት አልነበረበትም ከገነት ከወጣ በኋላ ግን ይህ ሁሉ መከራ በርሱ ላይ መጥቶበታል ይህን ሁሉ መከራ ስለተቀበለ አዳም ወደዚህ ዓለም ሲሰደድ የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ሊክሰው ስለወደደ ወደ ግብፅ ተሰደደለት እንደተበረደ ተበረደለት በዕፀ በለስ ምክንያት ከገነት እንደወጣ በዕፅ ተሰቅሎ ያጣው ክብሩንና የክብር ቦታውን ገነትን መለሰለት
፭ ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ ፤ሰማዕትነት እሳትና ስለት ብቻ አይደለም ሀገርን ጥሎ መሰደድም ሰማዕትነት ነው፡፡ በመሆኑም ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ የማትችሉት መከራ ቢመጣባችሁ ተሰደዱ ለማለት ወደ ግብፅ ተሰደደ ስደት ከሰማዕትነት ገብቶ የተቆጠረበት ምክንያት መከራው በሰይፍ ተቆርጦ በስለት ተቀልቶ ከመሞት በላይ ስለሆነ ነው፡፡ከመከራ ሁሉ ከባዱ መከራም ደም ሳይፈስ በየጊዜው የሚፈጸመው የሰማዕትነት ተጋድሎ ነው በሰይፍ ተቀልቶ እሳት ውስጥ ገብቶ መሞት ቀላል ነው ባይባልም አስፈሪ ቢሆንም በስደት ልዩ ልዩ መከራ ከመቀበልና በየጊዜው ከመፈተን ግን የተሻለ ነው ሰይፍ የሚያስፈራው ለተወሰነ ደቂቃ ነው ስደት ግን በየጊዜው ከሰይፍ በላይ በሚያም መከራ መቆረጥና መሰቃየት ነው እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ልጇ እንዳይሞትባት ከሰው ለመሰወር በበረሃው ስትሔድ ግሩማን አራዊት ያስደነግጧት ነበር ሰው ወዳለበት መንደር ስትሔድ ሰዎች ይጣሏታል፡፡
በዚያ ላይ ደግሞ ቀን ሐሩረ ፀሐዩ ሌሊት ቁረ ሌሊቱ እየተፈራረቀባት እሾሁ እየወጋት እንቅፋቱ እየመታት መውጫና መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥ ገብቶ መሰቃየቱ የመንገዱ መጥፋት በዚያ አሰልችና አድካሚ ጉዞ ውስጥ የልጇ በውኃ ጥም መቃጠልና ማልቀስ ለእመቤታችን ሌላው ሰማዕትነት ነበር ይህን ሁሉ መከራ መቀበሏ ግን ሰማዕታትን በስደትና በልዩ ልዩ መከራ ሲሰቃዩ መከራውን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ለምን ይህ ሁሉ መከራ አገኘን ብሎ ተስፋ እንዳይቆርጡ ተስፋ ይሆናቸዋል ስለዚህ ለምን ይህ ሁሉ መከራ ደረሰብን ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ስደትን ባርካ ሰጠቻቸው እሷን መሠረት አብነት በማድረግም ብዙ ቅዱሳን ለሃይማኖታቸው ለቤተ ክርስቲያናቸው በስደትና በስለት መከራ ተቀበሉ ዋሻ ለዋሻ በረሓ ለበረሓ ተንከራተቱ ግን ተስፋ አልቆረጡም እመቤታችን መጽናኛ ሁናቸዋለችና ስለዚህ እመቤታችን በስለት ከሚፈጸመው መከራ ውጭ ያልተቀበለችው መከራ ስለሌለ እሞሙ ለሰማዕት የሰማዕታት እናታቸው እየተባለች ትመሰገናለች(ቅዳሴ ማርያም)
የቅዱሳንን ገድልና መከራ የሚናገረው ስንክሳር የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍም ስደት እሳትና ስለት ብቻ አለመሆኑን እየተሰደዱ እየታሠሩ እየተገረፉ መከራ የሚቀበሉትን ቅዱሳን ሰማዕት ዘእንበለ ደም እያለ ይጠራቸዋል ሰማዕት ዘእንበለ ደም ማለትም ደማቸው ሳይፈስ ሰማዕትነትን የተቀበሉ ማለት ነው፡፡የእነዚህ ሰማዕታት ሰማዕትነት አንድ ጊዜ በማይገድል በየጊዜው በሚደርስ መከራ መሰቃየት ነውና፡፡
በስደቷ ጊዜ ያገኛት መከራ
እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር በተሰደደችበት ጊዜ ልዩ ልዩ መከራ አግኝቷታል፡፡መከራውም ለእመቤታችን ኀዘን ጭንቅ ቢሆንም ለእኛ ግን ደስታና ድኅነት ነበር ምክንያቱም ከእመቤታችን በኋላ የነበሩ አባቶቻችንና የነርእሱ ልጆች የሆንነው እኛ ዛሬ ላይ ስደቷን መከራዋን እያሰብን የቻልን ሰውነታችን በጾም እያደከምን ያልቻልን ማኅሌት እየቆምን ለርሷና ለልጇ የምስጋና እጅ መንሻ እያቀረብን በስደቷ ወራት የደረሰባትን መከራ እያዘከርን እንድታማልደን እንማጸንበታለን በረከትም እናገኝበታለን፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ “አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ እንዘ ትጐይዪ ምስሌሁ እሀገር ለሀገር በመዋዕለ ሄሮድስ ርጉም አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኅዘ እምአዕይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ አዘክሪ ድንግል ረኀበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኵሎ ዐፀባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ፤ርጉም ሄሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንቺ ጋር ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር የተሰደደውን መሰደድ አሳስቢልን በአይኖችሽና በልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር ዕንባ አሳስቢልን ረሀቡን ጥሙን ችግሩንና ኀዘኑን ያገኘሽንም ልዩ ልዩ መከራ አሳስቢልን (ቅዳሴ ማርያም)በማለት እመቤታችን ሔሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር መሰደዷን፣ ከዓይኗ የፈሰሰውንና በልጇ ፊት የወረደውን ዕንባ አማላጅ አድርጋ እንድታሳስብልን ይናገራል ይህንም ቃል ቅዳሴ ማርያም በተቀደሰበት ቀን ቤተ ክርስቲያናችን ሁልጊዜ ካህናቱ ሥጋውን ደሙን አቀብለው ከተመለሱ በኋላ ትጸልየዋለች እኛን ኀጥአንንም ታማልድበታለች፡፡
እመቤታችን በተሰደደችበት ወራት ካጋጠማት ጭንቅ ጭንቅ መከራ ሁሉ የሚበልጠው በልጇ ላይ የሚመጣው መከራ ነበር ምክንያቱም ሀገር ጥላ የተሰደደችው ተወዳጁን ልጇን ከሞት ለማዳን ነውና፡፡ሄሮድስ አራት ወታደሮችን ከነሠራዊታቸው በሽልማት ሸልሞ እመቤታችን ከነልጇ ይዘው ከመጡ የበለጠ ሹመትና ሽልማት እንደሚጠብቃቸው አብስሮ ልኳቸው ነበር፡፡
የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ይህንን ምስጢር ለአባቱ ለዮሴፍና ለእመቤታችን እንዲሁም ለሰሎሜ ለመንገር ከነበረው ኃይል ላይ የአንበሳ ኃይል ተጨምሮለት በፍጥነት ሲጓዝ እያለ የመልካም ነገር ጠላት የሆነው ሰይጣን መንገድ ላይ ጠብቆ ወዴት እንደሚሔድ ጠየቀው ዮሳም በየዋህነት የሚሮጥበትን ጉዳይ ሳይደብቅ ዘርዝሮ ነገረው ሰይጣንም የሄሮድስ ሠራዊት ቀድመው መሔዳቸውን በሔዱበት ፍጥነት ካገኟቸው እንደሚገድሏቸው ዮሳም በከንቱ እንዳይደክም ያዘነ በሚመስል ድምፅ እንዲመለስ ነገረው ዮሳ ግን ሐሳቡን ሳይቀበል ከሞቱም እቀብራቸዋለሁ በሕይወት ካሉም የሆነውንና የታሰበውን ነግሬ እንዲሸሹ አደርጋለሁ ብሎ መገስገስ ጀመረ ኃይል ከእግዚአብሔር ተጨምሮለታልና፡፡
ዮሳ እየሮጠ ሲሔድ መንገድ ላይ አገኛቸውና ገና ከመድረሱ እመቤታችን ያስደነገጠ ሕሊናዋን የረበሸ ምርር ብላም እንድታለቅስ የሚያደርግ አሰቃቂ ዜናን ነገራት እመቤታችንም የዮሳን ቃል ሰምታ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላኛው ሀገር የተሰደድኩት ከሞት ላላድንህ ነውን? ልጄ አንተን ሲገሉህ ከማይ እኔ አስቀድሜ ልሙት በማለት ስታለቅስ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በእጁ ዕንባዎቿን በማበስ እንደማይሞት ከነገራት በኋላ ፊቱን ወደ ዮሳ መልሶ ዮሳ ዕሡይ ምጽአትከ (አመጣጥህ ዋጋ የሚያሰጥ መልካም) ነበር ነገር ግን እናቴን አስደንግጠሃታልና በዕለተ ምጽአት አስነሥቼ ዋጋህን እስከሰጥህ ድረስ ይህችን ደንጋይ ተተንተርሰህ ዕረፍ ብሎት ዐርፋል፡፡
እንግዲህ እመቤታችን በስደቷ ወራት ውኃ በመጠማት በመራብ እሾሁ እየወጋት እንቅፋቱ እየመታት ቀን የበረሓው ሐሩር እያቃጠላት ሌሊት ደግሞ ብርዱ እያሳቃያት ትጓዝ ስለነበር ያገኛትን መከራ በቃላት ገልጾ መጨረስ አይቻልም በተለይ ሰው ስታይ ልጇን የሚገድሉባት ስለሚመስላት በጣም ትጨነቅም ታለቅስም ነበር፡፡
አባ ሕርያቆስም በስደትሽ ወራት ያገኘሽን ልዩ ልዩ መከራ ከልጅሽ ዘንድ አሳስቢልን ያለው ያገኛትን መከራ አስባ እኛንም ከአስፈሪ ፈተና እንድታወጣን ነው አባቶችም እመቤታችን መከራዋን እያነሡ ካለቀሱና ከለመኗት ፈጥና እንደምትሰማ በሕይወታቸው ካገኙት ተሞክሮ ተነሥተው ይናገራሉ፡፡ስለዚህ እኛም በወርኀ ጽጌ ስደቷን ስናስብ የራሳችንንም የሀገራችንንም ችግር አብረን ልናስብ ይገባል፡፡በተለይ በሀገር የሚመጣ ችግር ለሁላችንም የሚተርፍ ስለሆነ እመቤታችን የዐሥራት ሀገሯን በአማላጅነቷ እንድትጠብቃት ሁላችንም የቻልነውን ያህል በወርኀ ጽጌ ተግተን ልንጸልይ ማኅሌት ልንቆም በጸሎት ልንበረታ ይገባል አምላካችን እግዚአብሔር የሀገራችን ጥፋት አያሳየን አሜን፡፡
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት ፳፮ኛዓመት ቊ ፮ ጥቅምት ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም