አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል
መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል አምላካችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤ እንደ ሕፃናት ቀስ በቀስ አድጎ፤ ወንጌልን ለዓለም ሰብኮ፤ ለሰው ልጆች ቤዛ ይሆን ዘንድ፤ በሞቱ ሞትን ይሽር ዘንድ፤ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በትንሣኤውም ለሰው ልጆች ትንሣኤን አወጀ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የነበረውንም የጥል ግድግዳ አፈረሰ፡፡ የሰው ልጆች ያጣነውን የእግዚአብሔር ልጅነትንም አገኘን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርኁከ ከመ ያመስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኅኑ ፍቁራኒከ” ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው መዝ.49፡4 እንዲል፡፡ “ጠላቶቻችንን በአንተ ድል አናደርጋቸዋለን” በማለት የመስቀልን ክብርና አሸናፊነት አብስሯል፡፡መዝ. 43፡5፡፡
“እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኀኒተ በማዕከለ ምድር” እግዚአብሔር ዓለም ከመፈጠሩም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ፡፡ መዝ. 73፡16 በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደተቀኘው እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ለማዳን የቃልኪዳን ቦታዎችን በዚህች ምድር ላይ አዘጋጅቷል፡፡ በዓለም ላይ ቃል ኪዳን ከተሰጣቸው ቅዱሳት መካናት መካከል አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያ ሀገራችን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በግምባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አንዷ ናት፡፡ አባቶቻችን “ግሸን ደብረ ከርቤ መካነ መስቀሉ ለክርስቶስ እንተ ይእቲ ኢየሩሳሌም” የክርስቶስ መስቀል መንበር የሆነችው ግሸን ደብረ ከርቤ ናት ይህችውም ኢየሩሳሌም ናት በማለት ግሸን ደብረ ከርቤ ከኢየሩሳሌም ጋር እኩል መሆኗን መስክረውላታል፡፡
የጌታን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መስቀል በቅድስት እሌኒ በ325 ዓ.ም. ከተቀበረበት ከወጣና በክብር ለረጅም ዓመታት በኢየሩሳሌም ከተቀመጠ በኋላ ዐረቦች ኢየሩሳሌምን በመውረራቸው ምክንያት በአረማውያን እጅ እየተማረከ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር ሲንከራተት ቆይቷል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖችም በመስቀሉ መማረክ ያዝኑና ይበሳጩ ስለነበር ጦራቸውን አሰልፈው መስቀሉ ወደሔደበት ሀገር በመዝመት ጦርነት ያካሔዱ ነበር፡፡
በ778 ዓ.ም. አራቱ አኅጉራት ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ በአራቱ የመስቀሉ ክንፍ የተያያዙት ምልክቶችን በማንሳት የተከፋፈሉ ሲሆን በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ዐረቦች በእስክንድርያ ለሚኖሩ አባቶች የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሮቹ እና እጆቹ ተቸንክረው የተሰቀለበትን ሙሉ መስቀል ላኩላቸው፡፡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስም በክብርና በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡
የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር መስቀሉ ለብዙ ዘመናት በግብፅ እስክንድርያ ከቆየ በኋላ የግብፅ እስላሞች ቁጥራቸው በመበራከቱ በክርስቲያኖች ላይ የመከራ ቀንበር ስላጸኑባቸው ከዚህ ስቃይ ይታደጓቸው ዘንድ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት “ንጉሥ ሆይ በዚህ በግብፅ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንስተህ አስታግስልን” ብለው ይልካሉ፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ደግሞ የግብፅ ንጉሥ አቡነ ሚካኤልንና አቡነ ገብርኤልን በማሰሩ ምክንያት ከዚህ አስከፊ ችግር እንዲታደጓቸው ክርስቲያኖች መልእክት እንደላኩባቸው ይገለጻል፡፡ መልእክቱ የደረሳቸው ዐፄ ዳዊትም ስለ ሃይማኖታቸው በመቅናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት አሰልፈው ወደ ግብፅ ይዘምታሉ፡፡ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከልም እርቅ እንዲወርድ ተደረገ፡፡
የግብፅ ክርስቲያኖችም ዐፄ ዳዊት ስላደረጉላቸው መልካም ነገር እጅ መንሻ ይሆናቸው ዘንድ ብዛት ያለው ወርቅና ብር ያቀርባሉ፡፡ ዐፄ ዳዊት ግን ፍላጎታቸው ወርቅና ብሩን መውሰድ ሳይሆን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡ በጥያቄያቸውም መሠረት ተሰጣቸው፡፡ “መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ አይተው ስለነበር ጉዟቸውን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ያደርጋሉ፡፡ በመንገድም እያሉ ያርፋሉ፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ተቀጸል ጽጌ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡
ከዐፄ ዳዊት በኋላ በቦታቸው የተተኩት ዐፄ ዘርዐያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ በማየታቸው መስቀሉን በ1443 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በተለያዩ ቦታዎች ለማሳረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በደብረ ብርሃን፤ በሸዋ ደርሄ ማርያም፤ በጨጨሆ፤ በአንኮበር፤ በመናገሻ አምባ፤ በእንጦጦ፤ ወዘተ አሳርፈውት አልተሳካላቸውም፡፡ በመጨረሻም መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም. በራዕይ በተነገራቸው ቅዱስ ስፍራ በግሸን ደብረ ከርቤ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አኑረውታል፡፡
የተራራው ተፈጥሯዊ አቀማጥ ሲመለከቱት አንድ ጥሩ አናፂ ከጥሩ እንጨት ባማረ ጌጥ ጠርቦ የሰራው ግሩም የእጅ መስቀል ይመስላል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም መሠረቱ የተጣለውና ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽ የበቃው በ514 ዓ.ም. በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት አባ ፈቃደ ክርስቶስ በሚባሉ አባት ነው፡፡ አባ ፈቀደ ክርስቶስ የዐፄ ካሌብ የንስሐ አባት ሲሆኑ በየመን ሀገረ ናግራን ላይ የነበሩ የእግዚአብሔር አብና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁለት ጽላቶችን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው በመምጣት በግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ በማኖር ሲቀደስባቸውና ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደረስባቸው ቆይተዋል፡፡ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የአሁኑን ስም ከማግኘቷ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ስሞች ስትጠራ የቆየች ሲሆን ደብረ ነጎድጓድ፤ ደብረ እግዚአብሔር፤ ደብረ ነገሥት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና መጻሕፍት ለአፍሪካ የደረሰው የመስቀሉ ቀኝ ክንፍ ብቻ ነው ሲሉ፤ የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አበው ሊቃውንት ግን አጥብቀው እንደሚቃወሙት መጻሕፍት ያረጋግጣሉ፡፡ መስቀሉ ለአራቱ ክፍለ ዓለማት ሲከፋፈል መስቀሉ ላይ ተለጥፈው የነበሩት ምልክቶች በማንሳት ለሦስቱ ክፍለ ዓለማት እንደተሰጠና ለአፍሪካ ግን ሙሉ መስቀል እንደደረሰ ይመሰክራሉ፡፡ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በግሸን ደብረ ከርቤ በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው መስቀል የቀኝ እጁ በኩል ብቻ ሳይሆን ሙሉው የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያያናችንም ይህንን መሠረት በማድረግ መስከረም 21 ቀን በየዓመቱ በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በድምቀት ታከብራለች፡፡
-
ምንጭ፡- አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል 1990 ዓ.ም.
ግሸን ደብረ ከርቤ የቃል ኪዳን አምባ ቀሲስ በላይ ተገኝ 1996 ዓ.ም.
ቅዱሳት መካናት በኢትዮጵያ ዘመድኩን በቀለ 1992 ዓ.ም.