አትማረኝ ዋሻ
ሚያዚያ 18 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
/ጸበል ጸዲቅ ክፍል አምስት/
“አትማረኝ” እያሉ ስለ ጸለዩ አባት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት በትምህርታቸው እያነሱ በምሳሌነት ከሚጠቅሷቸው ትምህርቶች አንዱ ነው፡፡ ከጣና ሐይቅ ጉዞ ከቃረምኳቸው መረጃዎቼ መካከል ለዛሬ በጸበል ጸዲቅ ጽሑፌ አትማረኝ ዋሻንና ታሪኩን በጥቂቱ ላስተዋውቃችሁ፡፡
አትማረኝ ዋሻ በጣና ሐይቅ ደሴቶች መካከል ከሚገኙ ገዳማት መካከል ከማን እንደ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም አንድነት ገዳም በስተ ምእራብ አቅጣጫ የጣና ሐይቅን ጉዞ ከገታው አንደ ተራራ ሥር የሚገኝ ዋሻ ነው፡፡
ከብርጊዳ ማርያም ገዳም ወደ ማን እንደ አባ ያሳይ መድኀኔዓለም ገዳም በጀልባ እየተጓዝን አብረውን ከነበሩት ደብረ ሲና ማርያም ገዳም መነኮሳት መካከል አንዱ አባት ጣታቸውን ወደ ምእራብ አቅጣጫ ወደ አንድ ዋሻ እያመለከቱ፡፡ “ያ ተራራ ይታያችኋል? ከተራራው ሥር የሚገኘው ዋሻስ?!” አሉን፡፡
ሁላችንም አባታችን በጣታቸው ወደሚጠቁሙት አቅጣጫ ተመለከትን፡፡ በርቀትም ቢሆን ዋሻውን ተመለከትን፡፡ የጋዜጠኝነት ጆሮዎቻችን ተቀሰሩ፡፡ለመስማት ጓጓን፡፡
“በዚህ በምትመለከቱት ዋሻ ውስጥ ለብዙ ዘመናት አንድ አባት የጸሎት በዐት አድርገውት “አትማረኝ” እያሉ የጸለዩበት ቦታ ነው” አሉን፡፡
ይህንን ታሪክ ማን እንደ አባ ያሳይ መድኀኔዓለም ገዳም እንደደረስን ለማጣራት ጥረት ያደረግን ሲሆን የገዳሙ አባቶች የአቡነ ያሳይ ገድልን መሠረት አድርገው የታሪኩ ትክክለኛነት አረጋግጠውልናል፡፡ ታሪኩንም አሳጥሬ ላቅርብላችሁ፡፡
አቡነ ያሳይ ከሰባቱ የአቡነ መድኀኒነ እግዚእ ደቀመዛሙርት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ወደ ጣና ደሴት ከአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ጋር በመሆን በጸሎት ይተጉ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ በጣና ሐይቅ ላይ እንደ ጀልባ የሚጓዙበት አንድ ጠፍጣፋ ድንጋይ /ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡/ በጣና ደሴት ላይ ለአገልግሎት በመፋጠን ላይ እያሉ ዛሬ አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ አንድ አባት ዋሻው ውስጥ “አትማረኝ – አትማረኝ- አትማረኝ” እያሉ ሲጸልዩ ያገኟቸዋል፡፡
አቡነ ያሳይ በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው “አባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት?” አሏቸው፡፡
“አባቴ እንደ እርስዎ ያሉ አባት መጥተው “አትማረኝ” እያልክ ጸልይ ብሎኝ ነው በማለት መለሱላቸው፡፡
“እንዲህ ዓይነት ምክር የሚመክር ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምረው “ማረኝ” እያሉ ይጸልዩ በማለት አቡነ ዘበሰማያትን አሰተምረዋቸው ይሄዳሉ፡፡
አትማረኝ እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም “ማረኝ” እያሉ መጸለያቸውን ቢቀጥሉም ብዙ መግፋት ሳይችሉ ጸሎቱ ይጠፋባቸዋል፡፡ ጸሎቱን ያስጠኗቸው አባት አቡነ ያሳይ ርቀው ሳይሄዱባቸውም በውኃ ላይ እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡
“አባታችን ያስጠኑኝ ጸሎት ጠፋብኝ፡፡ እባክዎ ያስተምሩኝ” ይሏቸዋል፡፡
አቡነ ያሳይ የእኚህ አባት መብቃት ተመልከተው “አባቴ እግዚአብሔር የልብ ነውና የሚመለከተው እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል” ብለዋቸው ይሔዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ተጠርቷል፡፡
ይቆየን