‹‹አቤቱ፥ እንደ አዘዝህ ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ›› (ሉቃ.፪፥፳፱)
አባ ፍቅረማርያም መኩሪያ
የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ቅዱስ ስምዖን ይህን ቃል የተናገረው በ፭፻ ዓመቱ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በክንዱ ታቅፎ ከመሰከረ በኋላ ከፈጣሪው እግዚአብሔር ዘንድ መኖርንም ተመኝቶ በተማጸነበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም የሆነው እንዲህ ነበር፤ የግሪኩ ንጉሥ በጥሊሞስ አዋቂ፣ ፈላስፋ፣ መጻሕፍትንም የሚመረምር፣ በዕውቀቱ ደግሞ ከእኔ በላይ ለሐሳር የሚልና ሁሉንም እንደአላዋቂ በመቍጠርም የሚመጻደቅ ሰው ነበር፡፡ ሆኖም ግን እኛ ሰዎች ሁሉን እንድናውቅ ቢፈቀድለንም የማይቻለን ነገር ይኖራልና ይህ ተገቢ እንዳልሆነ የንጉሡ መሳፍንትና መኳንንት እንዲህ አሉት፤ ‹‹እውነት ነው፤ ከሁላችንም የበለጠ ዐዋቂ ነህ፤ ነገር ግን የሚቀርህ ነገር አለ፤ አምላክ ያጻፋቸው ቃላቱና እስትንፋሱ የሆኑ ፵፮ ቅዱሳት መጻሕፍት አሉ፡፡ እነርሱን ብታውቅ ዕውቀትህ ፍጹም ይሆንልሃል›› አሉት፡፡ ጥሩ መካሪዎች ናቸውና በጎ ምክር መከሩት፡፡ ምክንያቱም ሰው ሥጋዊ ዕውቀት ብቻ ከፍጹምነት አያደርሰውም፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት ሲታከልበት ግን ፍጹም ዕውቀት ያገኛል፤ ያለበለዚያ ግን ትዕቢተኛ ይሆናል፡፡ በመንፈሳዊ ዕውቀት ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› የሚለውን ቃል ስለሚረዳ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያድርበታል፡፡ (ምሳ. ፩፥፯)
ከዚህ በኋላ ፵፮ የኦሪት መጻሕፍት ወደ እርሱ አስመጥቶ፤ ጸሐፍቱን ከመተርጒማኑ ጋር አብሮ ወደ ሚኖርበት ግሪክ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ ቁጥራቸው ፸፪ ቢሆንም ሁለቱ ከመንገድ ቀርተው ሰባው ጽርዕ (ግሪክ) ደረሱ፡፡ እያንዳንዳቸውንም ሁለት ሁለት አደርጎ በመመደብ መጻሕፍቱንም ከልሳነ ዕብራሳይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ እንዲተረጒሙት አደረጋቸው፡፡ ጥበብ የእግዚአብሔር ነውና በኋለኛው ዘመን ‹‹አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዷል፤ ከድንግል ማርያም ተወልዷል›› ብለን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት እና የተቆጠረው ሱባኤ መፈጸሙን ስንናገር አይሁድ ግን ‹‹በፍጹም እውነት አይደለም፤ ከእኛ በላይ ለሐሳር፤ የምናውቀው እኛ ነን፤ እናንት ከየት አምጥታችሁት ነው›› ብለው ያሳቱ መናፍቃን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጒም ባለመቀበል እና ቃሉን በመካድ ነው፡፡
ለእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ግን እግዚአብሔር አምላክ ቃሉን ሊያስቀርላቸው ሽቶ በጥሊሞስን አስነሥቶ በጥበብ እንዲተረጎም አድርጎታል፡፡ ከእነዚህ ከ፸ ሊቃናት መካከል አንዱ ተርጓሚ ስምዖን ይባላል፡፡ ይህ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመተርጎም ወደ ግሪክ ሲወርድ ዕድሜው ፪፻ ዓመት ነበር፤ ይህ የሚያስድንቅ ነው፡፡ በዚህ ዕድሜው መጻሕፍትን ከማንበቡም ባሻገር ይተረጉምም ነበር፡፡ እኛ ግን በ፴ እና በ፵ ዓመታችን መጻሕፍትን ማንበብ ሰልችተናል፡፡ መተርጎሙ ቀርቶ የተጻፈ እንኳን ማንበብ አቅቶናል፡፡ አጫጭር ጽሑፎችን ሳይቀር ከምናነብ ከሌሎች መስማትን እንመርጣለን፤ ከስምዖን ታሪክ ግን መጻሕፍትን ማንበብ እንደሚገባ እንማራለን፡፡
አረጋዊው ስምዖንም እንዲተረጒም ትንቢተ ኢሳይያስ ተሰጠው፤ መጽሕፍቱንም ምዕራፎቹንም እየተረጎመ ከዘለቀ በኋላ ምዕራፍ ፯ ቍጥር ፲፬ ላይ ደረሰ፤ ኃይለ ቃሉም ‹‹ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› ይላል፡፡ ጌታ ለመዳን የሚሰጠው ምልክት እንደሆነ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ቃል ነቢዩ በትንቢት እንደተናገረው ሲተረጒም እንጨት ጠርቦ፣ ድንጋይ አለዝቦ ጣዖት ለሚያመልክ ንጉሥ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለድ እንዴት ይቻላታል ብሎ ተጠራጥሮ የእግዚአብሔርን ቃል ከሚያቃልለው ‹‹ሴት ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› ብለው ይሻላል በማለት በራሱ ሐሳብ መጽሐፉን ተረጎመው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ምንም መጻፍ ስላልተቻለው አንቀላፋ፡፡ በዚያም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ ‹ሴት› የሚለውን ቃል ‹ድንግል› በሚለው ተካው፤ ስምዖንም በድጋሜ የጻፈውን እያጣራ ከቃሉ ሲደርስ ‹‹ምን ነክቶኝ ነው እንዲህ የጻፍኩት›› ብሎ ‹ድንግል› የሚለውን ፍቆ ‹ሴት› በሚለው ተካው፤ ነገር ግን አሁንም ከደረሰበት ምዕራፍ ማለፍ አልቻለም፡፡ እግዚአብሔርን ዓለም ሳይፈጠር በልቡናው አኑሯት ለዓለም መዳን ምክንያት ያደረጋትን የእመቤታችንን ክብር ተላልፎ ሌላ ነገር መጻፍም ሆነ መሥራት አልቻለም፡፡ ስለዚህ ስምዖን ይህን የራቀ እና የረቀቀ የእግዚአብሔር ምሥጢር በራሱ ሐሳብ ለመተርጐም ቢሻም ዳግም አንቀላፋ፤ የእግዚአብሔር መልአክ እንደገና ‹ሴት› የሚለውን ቃል ‹ድንግል› በሚለው ተካው፤ በሦስተኛው ሊፍቅ ሲነሣ መልአኩ እጁን ይዞ ‹‹ይህንን የተጠራጠርከውን ሳታይ አትሞትም›› አለው፡፡ ወዲያውኑ መልአኩ እንዳስቀመጠው ጽፎ ሥራውን ፈጽሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር የካቲት ፰)
ይህ ሲሆን ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊወለድ የቀረው ፫፻ ዓመት ነበር፡፡ ያም በደረሰ ጊዜ አረጋዊው ስምዖን በ፭፻ ዕድሜው ከአልጋ ተጣብቆ ይኖር ነበር፡፡ አምላክም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ በ፵ ቀኑ ድንግል ማርያም ሕግ ሥርዓት ለመፈጸም ወደ ቤተ መቅደስ ይዛው ሄደች፡፡ በዚህ ጊዜ ሰምዖን መንፈስ ቅዱስ አነሣሣው፡፡ ተጣብቆበት ከነበረበት አልጋም አስነሥቶ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲሄድ አበረታው፡፡ በዚህም ሲደርስ ድንግል ማርያም መድኃኒዓለምን ታቅፋ ስትደርስ እኩል ሆነ፤ ስምዖንም ጌታችንን በክንዶቹ ታቀፈው፡፡ ለ፫፻ ዓመት ታግሦ አምላኩን ለመታቀፍ በቃ፡፡ በዚያችም ቅጽበት ከሽምግልና የተነሣ የታወሩ ዓይኖቹ በሩለት፤ ወደ ፴ ዓመት ጎልማሳነትም ተቀየረ፤ ወገቡ ጸናለት፤ ቍርጭምጭሚቱም ረታ፤ ከዚያም መድኃኔዓለምን ፊት ለፊት ተመለከተው፤ የተጠራጠራትን ድንግል ማርያምንም ተመለከታት፡፡
ከዚያ በኋላ ስምዖን አምላኩ እግዚአብሔርን አመሰገነው፤ ከታሰረበት ስለፈታው፣ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቍራኛ ስላዳነው፣ ቃል የገባለትን የፈጸመለትን አምላኩን እንዲህ አለው፤ ‹‹አቤቱ፥ እንደ አዘዝህ ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፡፡ ዐይኖቼ ትድግናህን አይተዋልና፡፡ በወገንህ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ለአሕዛብም ብርሃንንም፥ ለወገንህ ለእስራኤልም ክብርን ትገልጥ ዘንድ፡፡›› (ሉቃ.፪፥፳፱-፴፪)
ቀጥሎም ‹‹የናቁሽ ሁሉ ከእግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእስራኤል ከተማ፥ ጽዮን ተብለሽም ትጠሪያለሽ›› እያለ ድንግል ማርያምን አመሰገናት፡፡ እንደ ነቢይነቱ ትንቢት ተናገረ፤ ለብዙዎቹ ለመነሣታቸውም ሆነ ለመውደቃቸው መንሥኤ ሆናል፡፡ መናፍቃንም እግዚአብሔርንም የባሕርይ አምላክነቱን ዘንግተው ወልደ ዮሴፍ እና አማላጅ ነቢይ የሚሉት መቀጣት ምክንያት ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ አንደሆነ ነገራት፡፡ (ኢሳ. ፷፥፲፬)
ዛሬ በስመ ክርስትና ክርስቶስን የማይሰብኩ እርሱንም የሚያቃልሉ ብዙ ድርጅቶች አሉ፤ የአውሬው መንፈስ ያደረባቸው እና ጌታችንን ለሚያቃልሉ አሕዛብ የመውደቃቸው እና የመቀጥቀታቸው ምክንያት ልጅዋ ምክንያት እንደሆነ የነገራት ምክንያት በዚህ ነበር፡፡ እንዲሁም ለአዳም እና ለልጆቹ፣ ከእርሱም በኋላ የባሕርይ አምላክነቱን፣ ጌትነቱን፣ ሕይወትነቱን፣ መድኃኒትነቱን፣ አምነው ለሚጠጉት ቤዛችን እንዲሁም ተስፋችን እንደሆነ ለሚያምኑና ሁሉ በዚህ ዓለም አረንቋ ተይዘው እንዳይቀሩ የረዳቸው እንዲሁም የምድራዊ ትጋታቸውን በክብር ፈጽመው በክብር ለተለዩት እና ገነት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረሳቸው መጠጊያ የሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ምክንያት መሆኑን አስረዳት፡፡ ‹‹ባንቺ ግን ከልብሽ ፍላጻ ይገባል፤ የብዙዎቹን ዐሳብ ይገልጥ ዘንድ›› አላት፡፡ ለነገረ ድኅነት እና ለቤዛ ዓለም ልጅዋ በመልዕልተ መስቀል እንደሚሰቀል፣ ሥጋው እንደሚይቆረስ፣ ደሙ እንደሚፈስ፣ የእርሱን መከራ ግን ማየት ለእርሷ እንደሚብስም ነገራት፡፡ እመቤታችንም ልጇን ከስምዖን ተቀብላ እና ወደ ደረቷ አስጠግታ ምርር ብላ አለቀሰች፤ በዚም ቃል ኪዳን ተቀብላበታለች፡፡ (ሉቃ.፪፥፴፭፣ ተአምረ ማርያም ፵፱)
ከዚህ ጋር ተያይዞም ጌታችን ስምዖንን ‹‹ወደኸው ከሆነ ከዚህ ላኑርህ›› ብሎ እንደጠየቀው ይገልጻል፡፡ ያን ጊዜም ስምዖን ‹‹ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ›› አለው፡፡ በድንግል ክንድ የታቀፈው ሕፃኑ ኢየሱስም ጸሎቱን ሰማ፡፡ (የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ፪፥፳፱)
ሰዎች ብዙ ዓመት መኖርን ይመኛሉ፤ ፈጣሪንም ረጅም ዕድሜ እንዲሰጣቸው ይማጸናሉ፡፡ ሰው በተሰጠው ዘመን በጎ የማይሠራበት ከሆነ ዕድሜ ብድር ነው፤ ብድር ደግሞ ዕዳ ነው፤ ሊመለስ ይገባልና፤ እግዚአብሔር በሰጠን ዕድሜ ልንሠራበት እንጂ በከንቱ ማባከን አይገባንም፤ ካለበለዚያ ግን ያስጠይቀናል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የአንዲት አረጋዊት ሴት ታሪክ እናንሣ፤ ‹‹ሴትዬዋ ወደ ፈጣሪያቸው ሲጸልዩ እንዲህ አሉ፤ ነፍሴን ከሥጋዬ እንዳትለያት፤ ይህች አሮጊት ሞቷ ላይቀር በዚህ በጠራራ ፀሐይ አስመታችን እያሉ ቀባሪው እንዳያንጎራጉርብኝ፤›› ከዚያ ደግሞ በጋው አልፎ ክረምት ሲመጣ ‹‹ፈጣሪ ሆይ አደራህን! በዚህ በክረምት ነፍሴን ከሥጋዬ እንዳትለያት፤ ይህች አሮጊት ሞቷ ላይቀር በዚህ በጭቃ አንገላታችን ብለው ቀባሪዎቼ እንዳያዝኑ›› ብለውም ተማጸኑ፡፡ ከዚያ ባለቤቱ ተገለጠና ‹‹በበጋም አትውሰደኝ፤ በክረምትም አትውሰደኝ አልሽኝ፡፡ እንደው መቼ ልውሰድሽ?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አሰብ አደረጉና ‹‹ ምን አለበት ብትተውኝ›› አሉት ይባላል፡፡ ስለዚህም ዕድሜያንችን በጎ ነገር የማንሠራበት ከሆነ በምድር ብዙ ዓመት መኖር ዋጋ የለውም፤ እንዲያውም ጊዜያችንን ካልተጠቀምንበት ለክፋት እና ጥፋት ይዳርገናል፤ ወደ ኃጢአት ባርነት ውስጥም ይከተናል፡፡
አእምሮአችንን መንፈሳችንን ውሳጣዊ እና አፋዊው ሕይወታችን ያሰረን ብዙ ነገር አለ፡፡ ዓይናችን ታውሯል፤ የቅድስናን ነገር ማየትም ተስኖታል፡፡ እራሳችንንም የምናወዳድረው በቁስ ነገር ነው፤ በዙሪያችን ካሉ ሀብት ካካበቱ ወይም ይበልጡናል ብለን ከምናስባቸው ሰዎች ጋርም ራሳችንን እናወዳድራለን ወይም እንለካለን፡፡ ይህም የሆነው ዓይነ ልቡናችን ስለታወረ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር እንዳንገዛ ዓይናችንን፣ እጃችንን እና እግራችንን ያሰረን ኃጢአት ከእስር ፈትቶ በሰላም ያሰናብተን ዘንድ ልንጸልይ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም በዚህ ባለን ነገር እንዳንመካ ተስፋም እንዳናደርግ ይረዳናል፡፡
ስምዖን ከታሰረበት በሽታ ጌታችንን ሲያቅፍ ተፈትቷል፤ አርጅቶበት ከነበረው ሕይወቱም ታድሷል፤ ይህም ቤተ መቅደስ በሥጋ ሆነ በነፍስ መታደሻ መሆኑን ያሳያል፡፡ ቤተ መቅደስ ሄዶ ደጅ መጥናት፣ እጣኑን መታጠን እንዲሁም ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሳተፍ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ የምናገለግለው መንፈሳዊ አገልግሎት የሠመረ እንዲሆን እና ለእኛም አልፎ ለሌሎች አገልጋዮች መትረፍ እንዲቻለን ከቤተ መቅደስ የተለየ ሕይወት ሊኖረን አይገባም፡፡
ስምዖንም ዓይኑ በርቶ ጌታችን እና እናቱ ድንግል ማርያምን ካየ በኋላ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር መሔድ ናፍቆ እንዲያሰናብተው ጠየቀ እንጂ ዕድሜ እንዲጨመርለት አልተመኘም፡፡ እኛም እንደእርሱ እንድንመኝ ዓይነ ልቡናችንን እንዲያበራልን፣ ልክ እንደ ስምዖንም በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና በበጎ ሥነ ምግባር ጸንተን እንድንቆም መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ የስምዖንን ጸሎት ሰምቶ ፈጣሪው ከዚህ ምድር ያሳረፈው ቀን የካቲት ፰ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ያችን ዕለት ልደተ ስምዖን ብለዋታል፤ ከእስር ተፈትቶ ወደ ፈጣሪ እግዚአብሔር የሄደባት ቀን ነውና፡፡
እኛንም አምላካችን እግዚአብሔር ከታሰርንበት ነገር ሁሉ ይፍታን፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ አይለየን፤ አሜን፡፡