አባ ገሪማ ዘመደራ
ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በሮም ሀገር መስፍንያኖስ የሚባል ንጉሥ ነበረ፤ ሰፍንግያ የምትባል ሚስትም ነበረችው፡፡ ሆኖም ግን መካን ነበረች፤ እርሷም አምላኳ እግዚአብሔርን ልጅ እንዲሰጣት በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ስትማጸነው ከኖረች በኋላ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ይስሐቅ ብላ ጠራችው፡፡ ልጇም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ካደገ በኋላም ተምሮ በዲቁና ማገልገል ጀመረ፡፡
ንጉሥ መስፍንያኖስ ሲሞት ይስሐቅ በአባቱ ዙፋን ተተክቶ ሮምን ሲያስተዳድር ለሰባት ዓመታት ኖረ፤ አንድ ቀንም በዋሻ ይኖሩ ከነበሩት ከአባ ጰንጠሌዎን ዘጾማዕት እንዲህ የሚል መልእክት ደረሰው፤ ‹‹ይስሐቅ ሆይ፣ ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታኖችን ተዋቸው፤ አንተ ግን ክብር ይግባውና የክርስቶስን የማያልፍ መንግሥት ትሻ ዘንድ ወደ እኔ ና››፡፡ መልእክቱን ከተመለከተ በኋላ ይስሐቅ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት አባ ጰንጠሌዎን ወደ ሚኖሩባት ዋሻ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፤ በዚህን ጊዜም ቅዱስ ገብርኤል ተገለጠለትና በብርሃናውያን ክንፎቹ ተሸክሞ ዐሥር ወር የሚወስደውን መንገድ በሦስት ሰዓታት ጉዞ ከአባ ጰንጠሌዎን በዓት አደረሰው፡፡ አባ ጰንጠሌዎን ይስሐቅን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ካስገባው በኋላ የምንኩስና ልብስ አለበሰው፤ ከዚህም በኋላ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተጠምዶ ቆዳው ከዐፅሙ እስኪጣበቅ ድረስ በተጋድሎ ኖረ፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፲፯ ቀን ገጽ ፬፻፳፪-፬፻፳፫)
ከዚህም በኋላ አባ ይስሐቅ መደራ ወደ ምትባል ሥፍራ ሄደው ድንቆችንና ተአምራትን እያደረጉ፣ በሽተኞችን እየፈወሱ፣ አጋንንትን እያስወጡ ብዙ ዓመታት ኖሩ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው እኚህ ቅዱስ አባት ከዕለታት በአንዱ ቀን በጠዋት ሥንዴ ዘርተው፣ በሠርክ ሰብስበው መሥዋዕት አሳረጉ፤ በማግሥቱም ከግራር ዛፍ ላይ በሬዎችን አውጥተው ሥንዴዉን አበራይተው ሰባ ሰባት የእንቅብ መሥፈሪያ ሰብስበዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓለት ላይ የወይን ሐረግ ተከሉ፤ እርሷም ወዲያው በቅላ፣ አብባ ፍሬ ስታፈራ በወይኗ መሥዋዕት አሳረጉ፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ አባ ገሪማ መጽሐፍ እየጻፉ ከቆዩ በኋላ መምሸት በመጀመሩ ፀሐይ ሊጠልቅ ተቃረበ፤ ያን ጊዜም በጸሎታቸው ጽሕፈታቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ፀሐይን በቦታው እንዲቆም አደረጉ፤ በኋላም ከእጃቸው የወደቀው ብዕር ወዲያው በቅሎ፣ አቈጥቍጦ አደገ፡፡ ምራቃቸውን ትፍ ያሉበት ሥፍራም እስከ ዛሬ ድረስ ሕሙማንን ይፈውሳል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፤ ፲፯ ቀን፤ ገጽ ፬፻፳፫)
በአንዲት ዕለት መቅኑናቸውን ተቀብለው ከመነኮሳት ጋር ሲሄዱ መንገድ ላይ ቤተ ክርስቲያን አግኝተው ሲጸልዩ ካህናቱ ቅዳሴ እንዲያሟሉላቸው ጠየቋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ምግብ በልተው ነበርና ‹‹አንችልም›› ሲሉ አባ ይስሐቅ ምግብ አልተመገቡም ነበርና መቅኑናቸውን አስቀምጠው ቅዳሴውን አሟሉ፡፡ ባልንጀሮቻቸው ግን በልተው የቀደሱ መስሏቸው ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው ‹‹ቀሲስ ይስሐቅ ከበላ በኋላ ቀደሰ›› ብለው ከሰሷቸው፡፡ አባ ጰንጠሌዎንም አባ ይስሐቅ ሲመለሱ ‹‹ልጄ ሆይ፥ ምሥጢር ስላለኝ ሰዎችን ከአጠገብህ ገለል አድርጋቸው›› ሲሏቸው አባ ይስሐቅም ‹‹ሰዎችን ተውና ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ገለል ይበሉ›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ወዲያውኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ከቦታቸው ሸሹ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ጰንጠሌዎን ‹‹ልጄ ይስሐቅ ሆይ! ገረምኸኝ›› እያሉ አደነቋቸው፡፡ አባ ገሪማ ተብለው መጠራት የጀመሩትም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፲፯ ቀን ገጽ ፬፻፳፫-፬፻፳፬)
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያዘክረው በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘውን፣ በኋላም በጉባኤ ኬልቄዶን ጊዜ በመለካውያን አማካኝነት የመጣውን የሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ የኑፋቄ እምነት አንቀበልም ካሉት ከዘጠኙ ቅዱሳን መካከለል ማለትም ከአባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ አፍጼ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ጉባ፣ አባ ይምአታ፣ አባ ጰንጠሌዎንና አባ ጽሕማ አንዱ አባ ገሪማ በመሆናቸው በባዛንታይን ነገሥታት ሥቃይ ከደረሰባቸው በኋላ በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፡፡ በወቅቱ ብሔራዊ ቋንቋ የነበረውን የግእዝን ቋንቋ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስትና ከጽርዕ ቋንቋዎች ወደ ግእዝ ተርጕመዋል፡፡ እንደዚሁም ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናት አሳንጸዋል (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ አባ ጎርጎርዮስ ዘሸዋ፤ ፲፱፻፺፩ ዓ.ም፤ ገጽ ፳፫-፳፬)፡፡
በመጨረሻም አባ ገሪማ መልካም ተጋድሏቸውንና የቀና አካሔዳቸውን በፈጸሙ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኔ ፲፯ ቀን ተገልጦ ስማቸውን የሚጠሩትን፣ መታሰቢያቸውን የሚያደርጉትን፣ ገድላቸውን የሚጽፉ፣ የሚያነቡና የሚተረጕሙትን፣ በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ዳግመኛም የተራበውን ላበላ የተጠማውን ላጠጣ እኔ የሕይወት እንጀራን እመግበዋለሁ፤ የድኅነት ጽዋንም አጠጣዋለሁ፤ ቤተ ክርስቲያንህም በማኅሌት ያመሰገነውንና የጸለየውን እኔ የመላክትን ምስጋና አሰማዋለሁ፤ የተራቈተውንም ለሚያለብስ የብልህ ልጅ ያልሠራው የብርሃን ግምጃን አለብሰዋለሁ፤ ነፍሱም ከሥጋው በምትለይ ጊዜ የጨለማ መላእክት አይቀርቡትም፡፡ የብርሃን መላእክትም በዙሪያው አቆማቸዋለሁ፡፡ በስምህም ቤተ ክርስቲያን ለሠራ በሰማያት ዐርባ ሰባት የብርሃን ቦታዎችን እኔ እሰጠዋለሁ፤ ለቤተ ክርስቲያንህ መባ የሚሰጠውንም እኔ በመንግሥቴ እቀበለዋለሁ፡፡ ቦታህን የሚያከብረውንም እኔ በመንግሥቴ አከብረዋለሁ፤ ጠላቶች አጋንትን ረግጦ የሚገዛበትንም እሰጠዋለሁ›› አለው፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፲፯ ቀን ገጽ ፬፻፳፬)
አባ ገሪማም ‹‹ይህንን ታላቅ ሀብት በቸርነትህ ብዛት የሰጠኸኝ አቤቱ ስምህ ይክበር ይመስገን፤ ግን ጌታዬ ሆይ፥ መታቢዬን ላደረገ፣ ገድሌንም ለጻፈ እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ?›› ብሎ ጠየቀ፤ ጌታችንም እስከ ዐሥራ ሁለት ትውልድ እምራለሁ›› ብሎ መለሰለት፤ አባ ገሪማም መልሶ ‹‹ጌታዬ ልጆች ባይኖሩትስ ምን ታደርጋለህ?›› አለው፤ ጌታችንም ዐሥራ ሁለት ዕጽፍ ክብር እሰጠዋለሁ፤ ዳግመኛም የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለሁ›› ካለው በኋላ ሰላምታ ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባ ገሪማም እግዚአብሔር በሰጣቸው ክብር ተደሰቱ፤ በቅጽበትም በብርሃን ሠረገላ ተነጥቀው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በተለይም በገዳማቸው በመደራ አባ ገሪማ የተሠወሩበት ሰኔ ፲፯ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፤ ፲፯ ቀን፤ ገጽ ፬፻፳፬-፬፻፳፭)
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸዉም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡