አቡነ እንድርያስ ገዳም/አቡነ እንድርያስ ዋሻ
ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አባላት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ሰብከቶች በመንቀሳቀስ የአድባራትና ገዳማት እንቅስቃሴዎችን ቃኝተን ከተመለስን ሰነባበትን፡፡ ክፍል ስድስት ድረስ ጸበል ጸዲቅ በሚል ርዕስ ስናቀርብ መቆየታችን ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ቀጣዮቹን ክፍሎች ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡
የቴሌቪዥን ክፍል አዘጋጁ ቶማስ በየነ ከቪዲዮ ካሜራ ባለሙያው ሙሉጌታ ቢሆነኝ እኔን ጨምሮ ሊቀ መንኮራኩር ነብያት መንግሥቴ /ማዕረግ የራሳችን/ ሾፌራችን አብራሪነት ከአዲስ ዘመን ከተማ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ወደ አቡነ እንድርያስ ዋሻ ገሰገስን፡፡
የአስፋልቱን መንገድ አገባደን ኮሮኮንቹን ጥቂት ወደ ቀኝ ታጥፈን እንደተጓዝን ከፊት ለፊታችን እንደ ጦር የሾሉ ንጣፍ ድንጋዮች አጋጠሙን፡፡ ሊቀ መንኮራኩር ነብያት መኪናውን በንዴት አቁሞ “እንዴት በዚህ መንገድ ላይ ሂድ ትሉኛላችሁ?`ለመኪናው አስቡ እንጂ!” በማለት ከመኪናው ወርዶ በኩርፊያ ከፊት ለፊት ከሚታየው ትልቅ ድንጋይ ላይ ቁጭ አለ፡፡
ያለን አማራጭ በእግር መጓዝ ስለነበር ለቪዲዮ ቀረጻ የሚያገለግሉንን መሣሪያዎች ከመኪናው ላይ አውርደን በመከፋፈል ተሸክመን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ ከአርባ ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ አቡነ እንድርያስ ዋሻ ደረስን፡፡ የአቡነ እንድርያስ ገዳም ከአዲስ ዘመን ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ ከተራራ ሥር የሚገኝ የዋሻ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በአካባቢው በተለምዶ አቡነ እንድርያስ ዋሻ በመባል ይታወቃል፡፡
ገዳሙ አራት በሮች ሲኖሩት እያንዳንዳቸው ከአንድ ወጥ እንጨት ተጠርበው የተሠሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ደረጃና የበሩ መቃን በጣና ደሴት ውስጥ ከሚገኙት ከደብረ ሲና ማርያም፤ ከደብረ ገሊላ ኢየሱስ አቡነ ዘካርያስ ገዳም፤ ማን እንደ አባ ያሳይ መድኀኔዓለም ገዳም፤ . . . ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ገዳሙ ምንም ዓይነት እድሳት ያልተደረገለት ሲሆን ጥንታዊነቱን ጠብቆ የሚገኝ የዋሻ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ቀሲስ ቢራራ በላቸው ይባላሉ፡፡ የገዳሙ አገልጋይና ቁልፍ ያዥ ናቸው፡፡ ስለ ገዳሙ ካጫወቱንና በገዳሙ ውስጥ ከሚገኘው ከአቡነ እንድርያስ ገድል ካገኘነው በጥቂቱ ላቅርብላችሁ፡፡
ቦታው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ899 ዓ.ዓ. በዐፄ ባዚን ዘመነ መንግሥት የተመሠረተና የአካባቢው ሰዎች በእንጨት ምስል ቀርጸው ጣዖት እያመለኩ ቆይተውበታል፡፡ ለ440 ዓመታትም የኦሪት መሥዋዕት ሲሠዋበት የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ዋሻው ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ባልና ሚስት ዘንዶዎችን እርጎ እየመገቡ ያመልኳቸው እንደነበር በገዳሙ ውስጥ የሚገኘው ገድለ አቡነ እንድርያስ ይገልጻል፡፡
በሩን አልፈው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሰፊውን ቅኔ ማኅሌት ያገኛሉ፤ ከፊት ለፊት ቅድስትና መቅደሱ፤ እንዲሁም በትልቁ የተሳሉ የአቡነ እንድርያስ ስዕሎች ጎልተው ይታያሉ፡፡ በቤተ መቅደሱ ግራና ቀኝ ሰልፋና ደፈር በተባሉ ሰዎች በጥርብ ድንጋይ የተከለሉ ቦታዎች አሉ፡፡ /ሰልፋና ደፈር የዘንዶዎቹ ቀላቢዎች/ እንደነበሩ ገድለ አቡነ እንድርያስን በመጥቀስ አባቶች ይናገራሉ፡፡
ገዳሙ ከክርስቶስ ልደት በኋላም የአካባቢው ሕዝብ ዘንዶዎቹን በማምለክ የቆየ ሲሆን አቡነ እንድርያስ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት በደቀመዛሙርትነት ተመርጠው ምድረ እንፍራንዝ /የአሁኑ ሊቦ ከምከም ወረዳ አካባቢ/ ሄደው ክርስትና እንዲያስተምሩ፤ ህዝቡንም እንዲያጠምቁ ተልከዋል፡፡
አቡነ እንድርያስ ተልእኳቸውን ለመፈጸም ወደ አካባቢው ሲመጡ ረድአቸውን አቡነ ቶማስን አስከትለው ስለነበር አካባቢውን እንዲቃኙና ለጸሎት የሚመች ቦታ እንዲፈልጉ ላኳቸው፡፡ ይህ ዋሻ በአቡነ እንድርያስ ረድእ በነበሩት በአቡነ ቶማስ አማካይነት የተገኘ ሲሆን ዘንዶዎቹን ሲመለከቱ በመፍራታቸው ቦታው እንደማይሆናቸውና የዘንዶዎቹን አስፈሪነት ለአቡነ እንድርያስ ይገልጹላቸዋል፡፡ አቡነ እንድርያስም “በእግዚአብሔር ኃይል እናሸንፋቸዋለን” በማለት መጥተው በመስቀላቸው በማማተብ በእግዚአብሔር ስም ይገስጿቸዋል፡፡ በዚህ ቅጽበት አቡነ እንድርያስ የያዙት መስቀል ከመሬት ወድቆ የቀኝ በኩል ክንፉ በመሰበሩ ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንደነበረ አድርጎ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዘንዶዎቹ አንዱ ከአካባቢው ማዶ ተምዘግዝጎ ግራርጌ ጉበያ ማርያም ከሚባል ቦታ ላይ ወድቋል፡፡ አንደኛው ግን እስከ ዛሬ ድረስ የደረሰበት ባይታወቅም ወደ ዋሻው ውስጠኛ ክፍል ገብቶ እንደቀረ ይነገራል፡፡
አቡነ እንድርያስ ገዳሙን አቅንተው የአካባቢው ምእመናንን ክርስትና በማስተማር ታላቅ ተድጋሎ የፈጸሙበት ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡ ወደ ገዳሙ በተአምራት አብረዋቸው የመጡ አራት በግምት አንድ ሜትር ቁመት ያላቸውና ከ20 እስከ አሥራ አምስት ሣንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው ድንጋዮች መካከል ሁለቱ በደወልነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ሲደወሉ ወፍራምና ቀጭን ድምጽ ስለሚያወጡ የወንድና የሴት ደወሎች ይባላሉ፡፡ በአገልግሎት ወቅት ዋሻው ድምጽ እያስተጋባ ስለሚያስቸግር አቡነ እንድርያስ ገስጸውት እስከ ዛሬ ድረስ ዋሻው ምንም ዓይነት ድምፅ አያስተጋባም፡፡
በገዳሙ ውስጥ ዜና ማርያም የተባለችው ቅድስት እናት ለ25 ዓመታት በጸሎት ተወስና ቆይታበታለች፡፡ ከእንጨት ተፈልፍሎ በቁመቷ ልክ በተሠራ ገንዳ ውስጥ ገብታ የገንዳውን ግራና ቀኝ በደረቷ አቅጣጫ በመብሳት በጠፍር በማሰር ትጸልይ ነበር፡፡/ ዜና ማርያም ትጸልይበት የነበረው የእንጨት ገንዳ ዛሬም በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡/
በገዳሙ ውሰጥ በጥንቃቄ ጉድለት እየተበላሹ የሚገኙት ቅርሶች እንደ አልባሌ እቃዎች ተጥለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ዘንዶው እርጎ ይጠጣበት የነበረው ገንዳ፤ የዜና ማርያም መጸለያ ገንዳ፤ በእንጨት የተሠራ የኦሪት መሠዊያ፤ የመሥዋዕተ በግዕ ሥጋ ማስቀመጫ፤ የደሙ ማኖሪያ፡ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ለገዳሙ ከሰጧቸው 6 ነጋሪቶች መካከል ሁለቱ፤ ብዛት ያላቸው የሰው አጽሞች ይገኛሉ፡፡ ከአጽሞቹ መካከል አንዱ ሙሉ ለሙሉ ሳይፈርስ ከራስ ቅሉ እስከ እግር ጥፍሩ በዘመናዊ ሳጥን ተደርጎ ከላይ በመስታወት ታሽጎ ይታያል፡፡ የአጽሞቹን እድሜ መገመት እንደማይቻልና ቀድሞም እንደነበሩ ቀሲስ ቢራራ በላቸው ይገልጻሉ፡፡
የአቡነ እንደርያስ የእጅ መስቀል በገዳሙ ውስጥ በቅርስነት ተጠብቆ ይኖር እንደነበር፤ ብዛት ያላቸው ምእመናን በመስቀሉ ታሽተው ከያዛቸው ደዌ ይድኑ እንደነበር ቀሲስ ቢራራ በላቸው የዐይን ምስክር እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በአንድ ግለሰብ የአቡነ እንድርያስ መስቀል መዘረፉንና የግለሰቡ ማንነት ታውቆ ክስ ተመሥርቶበት በቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ገልጸውልናል፡፡ የአቡነ እንድርያስን ዋሻ ቆይታችንን አጠናቀን ስንወጣ የገዳሙ አበምኔት የክሱን ሁኔታ ለመከታተል ከሔዱበት ሲመለሱ አግኝተናቸው ነግረውናል፡፡
ገዳሙ ለስርቆት የተጋለጠ በመሆኑ የገዳሙ ጥንታዊ መጻሕፍት ተሰብስበው በአንድ ታማኝ በሆነ ግለሰብ ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ መደረጉንም ቅርሶቹን ለማየት በጠየቅንበት ወቅት ከተሰጠን ምላሽ ለማወቅ ችለናል፡፡ የብራና መጻሕፍት ገድለ ሠማእታት፤ ስንክሳር የዓመት /2/፤ ጸሎተ እጣን፤ ግንዘትና . . . ሌሎችም ንዋያተ ቅዱሳት በዚሁ ታማኝ ነው በተባለው ሰው እጅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በየዓመቱም ቆጠራ እንደሚካሔድ በስፍራው ከነበሩት አባቶች ተገልጾልናል፡፡
ምእመናን ተጠምቀው ከተያዙበት ደዌ የሚፈወሱበት ጸበል ከገዳሙ በስተ ደቡብ ይገኛል፡፡ ጸበሉ በምንጭነት የሚፈልቅ ሲሆን ምንም ዓይነት ከለላ ስላልተደረገለት ለከብቶችና ለአራዊት የተጋለጠ ነው፡፡
የኢየሱስ፤ የቅዱስ ሚካኤልና የአቡነ እንድርያስ ታቦታት፤ እንዱሁም የአቡነ እንድርያስ መቃብር በዚሁ ዋሻ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አቡነ እንድርያስ ግንቦት 20 ቀን 1246 ዓ.ም. ወደ ገዳሙ እንደገቡ ገድላቸው የሚገልጽ ሲሆን ዓመተ ምሕረቱን ባይገልጽም ጳጉሜ 3 ቀን እንዳረፉ ይጠቅሳል፡፡ገዳሙ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ የሌለው ሲሆን አገልጋዮቹ የራሳቸውን የእርሻ መሬት እያረሱ በሚያገኙት ይተዳደራሉ፡፡