አርአያነት ያለው ተግባር
ነሐሴ 3 ቀን 2004 ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሁን ያለው የክርስትናው ዓለም ከአለመኖር ወደ መኖር የመጣው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍም፤ ሀገር አቀፍም መንፈሳዊ ተቋም በመሆን ስትፈጽመው በኖረችው ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ መንፈሳዊ አገልግሎት ስትፈጽም የኖረችበት ዘመንም በአኃዝ ሲቀመር ከሁለት ሺሕ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ዘመን የደረሰችው ያለ ርእይና ዕቅድ በዘፈቀደ በመጓዝ አይደለም፡፡ አባቶቻችን ዘመንን እየቀደሙ እያቀዱና እየተገበሩ፤ አተገባበራቸውንም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው እየገመገሙ የተዛነፈውንም እያቀኑ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለትውልድ የሚሆነውን በጎ ነገር ሁሉ ሠርተው ቀምረው አስተላልፈዋል፡፡
ይህን የአባቶቻችን ዓቅዶ መሥራት፣ አፈጻጸሙን ቆም ብሎ ማየትን የሚዘክር ተግባር በጅማ ሀገረ ስብከት እያስተዋልን ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ ራስን የመገምገም ተግባርም ለሎሎችም አህጉረ ስብከት አርአያነት ያለው ነው፡፡
በአንዳንድ አህጉረ ስብከት እየደበዘዘ ወይም እየጠፋ ያለውን በዕቅድ መሥራትና አፈጻጸሙን የመገምገም ባህል ከማጎልበት አኳያ የጅማ ሀገረ ስብከት ተግባር ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሔዱ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ አካሄድ ነው፡፡
በዚህ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ የወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮችና የማኅበራት ተወካዮች እንዲሳተፉ ከመደረጉም በላይ የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ መደረጉ በራሰ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው በጨዋነት፣ በመደማመጥና በመከባበር መንፈስ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በግልጽ ተወያይቶ ለመፍትሔው ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክትና በጠቅላላ ጉባኤው የተላለፉትን ውሳኔዎች አተገባበር መከታተል መቻሉ፣ ያልተተገበሩ ሥራዎች ለምን አልተሠሩም ብሎ መጠየቅ ላይ መደረሱ፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስም ሆኑ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች በሥራቸው ያሉትን ካህናትንም ሆነ ምእመናንን ገንቢ ሂስ በሆደ ሰፊነት መቀበላቸው፤ ሌሎች አህጉረ ስብከት በአርአያነቱ ሊወስዷቸው የሚገቡ በጎ ተግባራት ናቸው እንላለን፡፡
በዕቅድ ተመርቶ መሥራትን፣ የዕቅድን አተገባበር መከታተልና የመቆጣጠርን አሠራርን ምን ታቀደ ምን ተሠራ ለምን አልተሠራም ብሎ የዓመቱን የአገልግሎት ጉዞ መለስ ብሎ መመልከትን እንደ ጅማ ሀገረ ስብከት ሁሉ ሌሎችም አህጉረ ስብከት ሊዘምቱበት ይገባል፡፡
ዐቅዳ የምትሠራ የሠራችውንም ሥራ ቆም ብላ የምትገመግም ቤተ ክርስቲያን፤ ምንም ጊዜ ቢሆን በየትኛውም ሁኔታ ድል አድራጊ ናት፡፡ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትም ተቋማዊ መሠረት እንዲይዙ ያስችላታል፡፡ ለብልሹና አድሏዊ አሠራሮች የተጋለጡ የልማትም ሆነ አስተዳደራዊ ተቋማቶቿን ወደተሻለ ምዕራፍ እንድታሸጋግር ያግዛታል፡፡
ከዚህም በላይ ቤተ ክርስቲያናችን ተከታይይዋን ሕዝብ በሰበካ ጉባኤ በማደራጀትና በዚህም ውጤት በተገኘው የገቢ አቅም ጥንካሬ ስብከቷ፣ ትምህርቷ ሕልውናዋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የቤተ ክርስቲያን ችግር ሆነው የኖሩትንም ሆነ የሚሆኑትን አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ለመመከት የጅማ ሀገረ ስብከት አርአያነት ለትልቋ ቤተ ክርስቲያናችን ወሳኝ ነው፡፡
አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ጉዟቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን በማድረግና በእኛዋ ቤተ ክርስቲያን ላይ ቀስታቸውን በማነጣጠር ወደ መንጋችን በረት ዘልቀው ለመግብት እያደረጉት ያለውን ሙከራ በሙከራ ደረጀ ለማስቀረት ብሎም እንዳይታሰብ ለማድረግ እንደ ጅማ ሀገረ ስብከት አቅዶ ለመሥራትንና አፈጻጸምን ገምግሞ ለቀጣይ ሥራ መዘጋጀት ይገባል እንላለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 19ኛ ዓመት ቁጥር 22 ከነሐሴ 1-15 ቀን 2004 ዓ.ም.