ቅዱስ አማኑኤል
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፳፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንደምን አላችሁልን? ነቢየ እግዚአብሔር ንገሥ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ….›› በማለት እንደገለጸው ከእናታችን ሆድ ጀምሮ የጠበቀን አሁንም በቸርነቱ የሚጠብቀን እግዚአብሔር ይመስገን! አሜን! (መዝ.፳፪፥፲)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ የምንነግራችሁ ስለጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አማኑኤል’ ስለሚለው ስሙ ትርጉም ይሆናል! ከዚያ በፊት ግን ስም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጥቂት እንንገራችሁ፡፡ ስም በቁሙ ከባሕርይ ከግብር የሚወጣ ቦታንና አካላትን፣ ህላዌና ሕይወት ያለው ማንኛውም ሁሉ በየክፍሉና በያካሉ፣ በየራስ ቅሉ፣ በየዓይነቱና በየመልኩ፣ በየነገዱ፣ በየዘሩና በየበዓቱ፣ በየዘመዱ ተለይቶ የሚጠራበት የሚታወቅበት ነው፡፡ አንድም ጥሪ ማለት ነው፤ ስመ ተጸውዖ ስመ ተቀብዖ ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡
ስመ ተጸውዖ(መጠሪያ ስም) ፍጥረት ሁሉ ከፈጣሪውና ከጌታው ከአዳም እንደተሰየመለት ነው፡፡ (ዘፍ.፩፥፩-፳፫) እንዲሁም ከአባት ከእናት፣ ከቤተ ክርስቲያን ከካህን ተሰይሞ የሚጠራበት ነው፡፡ ስመ ተቀብዖ ግን ከተጸውዖ ስም በኋላ በሹመት ጊዜ ከቀቢ፣ ከሿሚ የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው፡፡ ጳጳስ፣ ንጉሥ፣ ቄስ፣ ራስ…..እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላትገጽ ፰፻፷፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ እኛ የምንነጋራችሁ ስም ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ የጌታችን ስም ከሆኑ መካካል አንዱ ስለሆነው “አማኑኤል” ስለሚለው ድንቅ እና ታላቅ ስም ነው፡፡ ይህን ስም ገና ጌታችን ከመወለዱ በፊት የነበረው ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ ‹‹…ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋች፡፡.›› (ትንቢተ ኢሳይያስ ፯፥፲፬)
አያችሁ ልጆች! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምትወልደውን ልጅ አማኑኤል ብላ እንደምትጠራው ነቢዩ ኢሳይያስ ገለጸልን (ነገረን)፡፡ ይህ ስም ጥልቅ የሆነ ምሥጢር አለው፤ ነቢዩ እንደተነበየው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ በጻፈልን ወንጌል ደግሞ እንዲህ ተብሎ ተገለጸ፤ ‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤›› የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው፡፡›› (የማቴዎስ ወንጌል ፩፥፳፫)
አያችሁ ልጆች! አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፤ አማኑኤል ብለን ስሙን ስንጠራ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው እያልን ነው ! ግን ደግሞ እንዲሁ ዝም ብለን ሳይሆን የምንጠራው በጸሎት ጊዜ፣ በዝማሬ (በምስጋና) ጊዜ በአግባቡ ሊሆን ይገባል፤ ጌታችንን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በወለደችው ጊዜ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነልን፤ ጠላታችንን ሰይጣን ከእኛ አርቆልን እርሱ ከእኛ ጋር ሆነ፤ እርሱ ከእኛ ጋር ከሆነ ደግሞ ማን ያሸንፈናል? ማንስ ይጎዳናል!
ቅዱስ ጳውሎስ ሮሜ ለተባለ አገር ላሉ ምእመናን በጻፈላቸው መልእክት ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹…እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል ?…››( ሮሜ ፰፥፴፩) እርሱ ከእኛ ጋረ ከሆነ ክፉ ነግር አያገኘንም፤ ይጠብቀናል፤ ይባርከናል፤ የምንማረውን ጥበብ ማስተዋል ይገልጥልናል፤ ታዲያ ይህ ሁሉ እንዲሆንና እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን እኛ ታዛዦች፣ ሰው አክባሪዎች፣ በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት ታማኞች፣ ለሰው መልካም ነገር የምንሠራ፣ ሰዎችን የምንወድ መሆን አለብን፤ ያን ጊዜ መልካም እና አስተዋይ ቅን ልጆች ስንሆን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እስኪ እያንዳንዳችን የስማችንን ትርጉም እንጠይቅና እንረዳ፤ ወላጆቻችን ስማችንን ሲሰይሙን (ስም ሲያወጡልን) የራሱ የሆነ ምክንያት አለው ፤ ስም መጠሪያ ብቻ ሳይሆን ማስታወሻም ነው፤ ስለዚህ መልካም ምግባር በመሥራት፣ የጥሩ ነገር አርአያ ሆነን ለመገኘት አስተዋይና ብልህ ልጅ መሆን አለብን፤ ስም በመልካም ሲነሳ ሰው ደስ ይለዋል፤ ከደስታም በላይ ከእግዚአብሔር በረከትን ያሰጣል፤ እንደተሰየመልን ስም ዓይነት መልካም፣ ጠባይና ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ልጅ እንሁን፡፡
መልካም የፈተና ጊዜ ይሁንላቸሁ! በርቱ! ቸር ይግጠመን !
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!