ንዑስ አገባብ
መምህር በትረማርያም አበባው
ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ላይ ‹‹ደቂቅ አገባብ›› በሚል ርእስ አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስለ ‹‹ንዑስ አገባብ›› እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!
የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ቋንቋ ተርጉሙ!
፩) አባቴም እስከዛሬ ይሠራል
፪) ከረኀብ ጦር ይሻላል
፫) ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ
፬) በአብ እናምናለን
፭) ፊቷ እንደ ኮከብ ያበራል።
የጥያቄዎች መልሶች
፩) አቡየሂ እስከ ይእዜ ይገብር
፪) እምነ ረኀብ ይኄይስ ኲናት
፫) ድኅረ ኀለፈ ዝሰብ ከልሐ ከልብ
፬) ነአምን በአብ
፭) ከመ ኮከብ ያበርህ ገጻ
የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሙ!
፩) ተንሥኡ ለጸሎት
፪) ንሑር ኀበ ደብረ ከርቤ
የጥያቄዎች መልሶች
፩) ለጸሎት ተነሡ
፪) ወደ ደብረ ከርቤ እንሂድ
ንዑስ አገባብ
ንዑስ አገባብ ንዑስ መባሉ ቅጽል አንቀጽ አጎላማሽ ስለሆነ ነው። እንደ ዐበይት አገባባት ከአንቀጽ በኋላ እየወደቀ ማሰሪያ አገዝ ይሆናል።
፩) እንበለ፣ቅድመ፣ኢ….ሳ ይሆናሉ። እንበለን ‹ዘ› ቅድመን ደግሞ ‹እም› ያዳምቋቸዋል። ዘእንበለ ይቁም አድባር። እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም እንላለን። ትርጉሙ ዓለም ሳይፈጠር ማለት ነው። እንበለ እና ቅድመ ለዐበይት አገባባት አውታር በጣሽ ይሆናሉ። እስመ ቅድመ ይስተይ ማየ ሖረ እንላለን፤ ትርጉሙ ውኃ ሳይጠጣ ሄዷልና ማለት ነው። ኢተዘኪሮ አበሳ ዚኣነ ቢባል የእኛን በደል ሳያስብ ማለት ነው። ኢ ‹ሆኖ› ተብሎም ይተረጎማል። ምሳሌ፦ አልቦ ባዕድ አምላክ ኢ በሰማይ ወኢበምድር ዘእንበለ አምላክነ፤ ትርጉሙ በሰማይም ሆኖ በምድርም ሆኖ ከአምላካችን በቀር ሌላ አምላክ የለም ማለት ነው።
፪) ለኢ….ላለ ተብሎ ይተረጎማል። ለምሳሌ፡- ለኢዐሪገ ኢዐሪግ ሰማየ ብንል ትርጉሙ ወደሰማይ አለማረግን ላለማረግ ተብሎ ይተረጎማል። ‹በኢ› ደግሞ ባለ፣ ያለ ተብሎ ይተረጎማል። ምሳሌ፡- በኢሐነጸ ኢሐኒጽ መቅደሰ ብንል ትርጉሙ መቅደስን አለመሥራትን ባለመሥራት ተብሎ ይተረጎማል። ልዮን መሀረ በኢጽድቅ ጴጥሮስ ሰበከ በኢሕሳዌ ብንል ትርጉሙ ልዮን ያለ እውነት አስተማረ፤ ጴጥሮስ ያለሐሰት አስተማረ።
፫) እም…..ከ፣ኪ፣ክ፣ኪያ ይሆናል። ለምሳሌ፡- ይቀልል ኅልፈተ ሰማይ ወምድር እምትደቅ አሐቲ ቃል ዘወንጌል። የወንጌል አንዲት ቃል ከምትወድቅ/ከምትቀር የሰማይና የምድር ማለፍ ይቀላል።
፬) እስመ፣ጓ…..እኮን፣ብያ፣እኮ ይሆናሉ። በቀዳማይ፣ በካልዓይ፣ በሣልሳይ ይነገራል። ምሳሌ፡- ከለባትኒ ጓ ይበልዑ እምፍርፋራት ዘይወድቅ እማዕደ አጋእዝቲሆሙ እንላለን፤ ትርጉሙም ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ። እስመ እሳት ትነድድ እመዓትየ። ከቁጣየ የተነሣ እሳት ትነዳለች እኮን።
፭) አላ፣ባሕቱ፣ዳእሙ…..እንጂ ይሆናሉ። ምሳሌ፡- አላ አድኅነነ ሲል አድነን እንጂ ማለት ነው። ‹ባሕቱ› ነገር ግን ተብሎ ይተረጎማል። ባሕቱ ይከልአኒ ርኅራኄየ ሲል ነገር ግን ቸርነቴ ይከለክለኛል ይላል።
፮) እፎ፣ኦ፣ሚ፣አይ፣ምንት….ምን፣ ምንድን ይሆናል። አይ እና ምንት ባለቤት ሲጠራ ቅጽል ባለቤት ሲቀር በቂ ይሆናሉ። በምሳሌ፡- ሲገቡ አይ ልቡና ሲል ምን ልቡና ነው ማለት ነው። ምንት ነገር ስንል ምን ነገር ነው ማለት ነው። ‹አይ እና ምንትን› ሁ፣ኑ፣ኬ፥መ ከኑ ጋራ ያጋንኗቸዋል። አይኑ፣ምንትኑ፣ምንትኬ፣ምንትኑመ እንላለን። ምንትኑመ ስንል ኑ በመ የቀና ትራስ ነው። ‹ኦ፣ሚ› አንቀጽ ያጎላምሳሉ። ምሳሌ፦ ኦ ኀያል ነገረ አበው እስመ ይመውእ ኵሎ እንላለን። ሁሉም ያሸንፋልና የአበው ነገር ምንኛ ኃያል ነው? ማለት ነው። ሚ መጠን ግርምት ዛቲ ዕለት ብንል ትርጉሙ ይህች ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት?። ‹እፎ› በተጨማሪ ኧረግ፣ምንኛ፣ለምን፣እንዴት ይሆናል። እፎ ኀደርከ ሲል እንዴት አደርክ ማለት ነው። እፎ/በእፎ ትፄእል ሊቀ ካህናቲሁ ለእግዚአብሔር ስንል ትርጉሙ የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ለምን ትሳደባለህ?
፯) አይ፣መኑ……ማን ይሆናሉ። ከተቀብዖ ከተጸውዖ ስም በቀር በሰዋስው ሁሉ ይነገራሉ። ምሳሌ፦ መነ ያፈቅር ንጉሥ ሲል ንጉሥ ማንን ይወዳል። አይ ይትፈቀር ሲል ማን ይወደዳል ይላል። ‹መኑ› በተለየ ከፊት ‹እለ› ን ፊት ለፊቱ እየጨመረ ይበዛል። እለመኑ ስንል እነማን ማለት ነው። እለመኑ ተጸውዑ ስንል እነማን ተጠሩ ማለት ነው።
፰) አይቴ፣አይ….የት፣ሄት ተብሎ ይተረጎማል። ኀበ አይቴ የሐውር ንጉሥ ሲል ንጉሥ ወዴት ይሄዳል።
፱) አይ፣ማእዜ….መች፣መቼ ይሆናል። ማእዜ ይመጽእ ክርስቶስ ስንል ክርስቶስ መቼ ይመጣል ማለት ነው። አይ፣ማእዜ ከአጎላማሽነት በተጨማሪ ይቀጸላል። በአይ ዕለት በማእዜ መዋዕል ሲል መቼ ቀን መቼ ዕለት ማለት ነው።
፲) ስፍን፣እስፍንቱ….ስንት፣ስንቶች ይሆናሉ።ስፍን በአንድ እስፍንቱ በብዙ ይነገራል። እስፍንቱ ኀልቁ ወእስፍንቱ ተርፉ ፭ቱኑ ወሚመ ፮ቱ። ስንቶች አለቁ ስንቶችስ ቀሩ አምስት ናቸውን ወይስ ስድስት እንላለን።
፲፩) ቦኑ…….በውኑ፣በእውነት ይሆናል። ቦኑ ለከንቱ ኪዳንኪ ኮነ ስንል ትርጉሙ በውኑ ኪዳንሽ ለከንቱ ሆነ? ይላል።
፲፪) ኦ…….ሆይ ይሆናል። ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ስንል ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን ይላል።
፲፫) እስኩ፣ዮጊ…..እስኪ ይሆናሉ። በፊት በኋላ በካልዓይ በሣልሳይ ይነገራሉ። እስኩ/ዮጊ ነጽር ሲል እስኪ እይ ተብሎ ይተረጎማል። ረድ እስኩ እመስቀልከ ሲል እስኪ ከመስቀልህ ውረድ ማለት ነው።
፲፬) ድኅሪተ፣ግንጵሊተ፣ግፍትኢተ…. የኋሊት የእንግርግሪት ይሆናሉ። አሰርዎ ድኅሪተ ሲል የእንግርግሪት/ የኋሊት አሰሩት ማለት ነው።
፲፭) ግድመ….እግድሞ፣አግድሞ ይሆናል። ይትናገር ግድመ ግድመ ሲል እግድም እግድም ይናገራል ማለት ነው።
፲፮) ህየ፣ለፌ፣ከሀ፣ከሀከ…..ያ ወዲያ ይሆናሉ። ለፌ፣ዝየ…ይህ ወዲህ ይሆናሉ። እምህየ ንበር ስንል ከዚያ ተቀመጥ ማለት ነው። ህየ ንሰግድ ኩልነ ስንል በዚያ ሁላችን እንሰግዳለን ማለት ነው።
፲፯) ቅድመ፣መቅድመ፣ቀዳሚ፣ አቅዲሙ፣ ቀዲሙ……… ፊት፣ በፊት፣ ቀድሞ፣ ተቀድሞ፣ አስቀድሞ፣ ተቀዳድሞ አቀዳድሞ ይሆናሉ። ለምሳሌ፡- ቀዲሙ ዜነወነ ስንል አስቀድሞ/ቀድሞ ነገረን ማለት ነው።
፲፰) ድኅረ፣ደኀሪ፣ድኀሪተ….ተከትሎ አስከትሎ፣ ተከታትሎ፣ አከታትሎ ይሆናሉ። ምሳሌ፡- ባዕል አምጽአ ድኀሪተ ነዳየ ቤቶ ሲል። ሀብታም ድሃን ወደ ቤቱ አስከትሎ አመጣ እንላለን።
፲፱) ትካት፣ዓለም፣….ድሮ ይሆናሉ። በቀዳማይ በካልዓይ በፊት በኋላ ይነገራሉ። ሰብአ ዓለም/ሰብአ ትካት ስንል የድሮ ሰዎች ማለት ነው።
፳) ትማልም፣አስፌር፣አሜር አምና ይሆናሉ። እምትካት እስከ አስፌር ሲል ከድሮ እስከ አምና ማለት ነው።
፳፩) ዮም፣ይእዜ…..ዛሬ ይሆናሉ። ቤዛ ኵሉ ዓለም ዮም ተወልደ ስንል የዓለም መድኃኒት ዛሬ ተወለደ ማለት ነው።
፳፪) ሳኒታ፣ጌሠም……ነገ ይሆናሉ። ምሳሌ ኢትበሉ ለጌሠም ስንል ለነገ አትበሉ ማለት ነው። ሳኒታ ተለይቶ ማግሥት ይሆናል። ነጋዲ ይመጽእ በሳኒታ ሲል ነጋዴ በማግሥት ይመጣል ማለት ነው።
፳፫) ዓዲ፣ዮጊ፣ዮም፣ናሁ….አሁን ይሆናል። ናሁ መጽአ ስንል አሁን መጣ ማለት ነው።
፳፬) ዓዲ…..ገና ይሆናል። ዓዲ ኢመጽአ ስንል ገና አልመጣም ማለት ነው።
፳፭) አዲ፣ካእበ፣ዳግመ…..ዳግመኛ ይሆናሉ። ምሳሌ፡- ይሁዳ ቀተለ አባሁ ወዓዲ አውሰበ እሞ ወካዕበ/ወዳግመ አስቀለ እግዚኡ ስንል ይሁዳ አባቱን ገደለ ዳግመኛ እናቱን አገባ ዳግመኛም ጌታውን አሰቀለ ይላል።
፳፮) እንከ፣እምዮም፣እምይእዜ…. እንግዲህ እንግዲያ እንግዲያው እንኪያ እንኪያው ይሆናሉ። እምዮምሰ/እምይእዜሰ ይኩን ፍሥሓ ስንል እንግዲህስ ደስታ ይሁን ማለት ነው።
፳፯) ትራስ የሚሆኑ ቀለማት ፲፫ ናቸው። እኒህም ሀ፣ሁ፣ሂ፣መ፣ሰ፣ሶ፣ነ፣ኑ፣ኒ፣አ፣ኢ፣ ኬ፣ያ፣ዮ ናቸው። ሲገቡም መነሀ ሶበሁ ምትሂ እምነ ምንትኑ ምንትኒ አኮአ እፎኢ እፎኑመ እመሰ አድኅንሶ ውእቱኬ እንላለን።
፳፰) ኵሎ ጊዜ፣ኵሎ አሚረ፣ኵሎ ዕለተ፣ ኵሎ ሰዓተ…..ሁልጊዜ ይሆናሉ። ኵሎጊዜ እሴብሐከ ስንል ሁልጊዜ አመሰግንሀለሁ ማለት ነው።
፳፱) ወትረ፣ውቱረ፣ዘልፈ፣ለዝሉፉ፣ ዝሉፈ….ዘወትር፣አዘውትሮ ይሆናሉ። ይእዜኒ ወዘልፈኒ ስንል ዛሬም ዘወትርም ማለት ነው።
፴) ናሁ፣ነዋ፣ነየ….እነሆ ይሆናሉ። በፊትም በኋላም ይነገራሉ። ናሁ ተወልደ መድኃኔዓለም እነሆ የዓለም መድኃኒት ተወለደ። ‹ነየ› አቤት ይሆናል፤ ምሥጢሩ አለሁ ነው።
፴፩) አው፣ዮጊ፣ ሚመ እመ አኮ፣ ሶበ አኮ……ወይ፣ባይሆን፥ ካልሆነ ይሆናሉ። ሶበ አኮ እግዚአብሔር ምስሌነ ስንል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ኖሮ ተብሎ ይተረጎማል።
፴፪) ክመ…..መቼም፣መች ይሆናል። አንተሰ አንተ ክመ ስንል አንተ ግን መቼም አንተ ነህ ይላል። ‹ክመ› ብቻ ሲሆን ቅጽል ነው። ክመ አብርሃም እንተ ርእዮሙ ለሥላሴ ብንል ሥላሴን ያያቸው አብርሃም ብቻ ነው ማለት ነው።
፴፫) ጽመ፣ክመ…..ዝም ብሎ፣ቀስ ብሎ ይሆናሉ። መጽአ ክመ ቢል ዝም ብሎ/ቀስ ብሎ መጣ ይላል።
፴፬) ወ…..ግን ይሆናል። ያዕቆብሀ አፍቀርኩ ወኤሳውሀ ጸላእኩ ሲል ያዕቆብን ወደድኩ ኤሳውን ግን ጠላሁ ማለት ነው። ወ ‹ውጥን ጨራሽ› ይሆናል። ትኤምኀክሙ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወማርቆስ ወልድየ ስንል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም ትላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላም ይላችኋል ማለት ነው ። ወ ‹እንጂ› ይሆናል። ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ ስንል አያዩም እንጂ ዓይን አላቸው ማለት ነው። ወ ‹ቅጽል› ይሆናል። እስመ ኀልቀ ኀጥእ ወኢይትሜሀር ስንል የሚማር ኃጥእ አልቋልና እንላለን። ‹ወ› እና ተብሎ ይተረጎማል። ማርታ ወማርያም ስንል ማርያምና ማርታ ማለት ነው።
፴፭) ወ፣ሂ፣ኒ፣ጥቀ…..ስንኳን ይሆናሉ። ለምሳሌ፡- ኢይትዔረይዋ ለማርያም ደናግለ ሴሎ ጥቀ መላእክት/ወመላእክት/መላእክትኒ/መላእክትሂ ኢይትዔረይዋ እንላለን። ትርጉሙ የሴሎ ደናግል ማርያምን አይተካከሏትም። መላእክት ስንኳን አይተካከሏትም።
ተጨማሪ ምሳሌ፡- ሰሎሞን ጥቀ ኢለብሰ ከመ ፩ እም እሉ፤ ሰሎሞን እንኳን ከእነዚህ እንደ አንዱ እንላለን።
፴፮) እንዳኢ….እንጃ ይሆናል። እወ፣አማን፣አሜን….አዎን እውነት ይሆናል። ‹እንበየ› እንቢ ይሆናል። እንበየ ለጋኔን ስንል ጋኔንን እንቢ በሉት ማለት ነው። ‹ኦሆ› እሺ፣በጄ፥በጎ ይሆናል። ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔርን እሺ በሉት ማለት ነው።
፴፯) አሌ፣ወይ፣ዬ፣ሰይ….ወዮ ይሆናሉ። አሌ ለክሙ ሲል ወዮላችሁ እንላለን። ሰይ ሊተ ብሎ ወዮልኝ እንላለን።
፴፰) እንቋዕ እንቋዕ….እሰይ እሰይ ይሆናል። ምሥጢሩ ደስ አለኝ ነው። እንቋዕ እንቋዕ ርኢናሁ በአዕይንቲነ እንላለን። እሰይ እሰይ በዓይናችን አየነው ማለት ነው።
፴፱) በሐ…..እንዴት ዋልክ፣እንዴት አደርክ ማለት ነው። ‹ህንክ› እንካ ይሆናል። ‹ሀብ፣ነዓ› ና ይሆናሉ።
፵) እግዚኦ…..አቤቱ ይሆናል። እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ስንል አቤቱ ይቅር በለን እንላለን።
፵፩) እንቋዕ…..እንኳን ይሆናል። እንቋዕ አብጽሐክሙ ስንል እንኳን አደረሳችሁ እንላለን።
፵፪) ህቀ፣በህቁ፣ብዙኀ፣ፈድፋደ፣ ጥቀ እጅግ ይሆናሉ። ጥቀ ይትሌዐል ሲል እጅግ ከፍ ከፍ ይላል ተብሎ ይተረጎማል።
፵፫) ንስቲተ፣ውኀደ፣ኅዳጠ…ጥቂት ይሆናሉ።ንስቲተ ለሴት እንጂ ለወንድ አይሆንም። ትበልዕ ንስቲተ ስንል ጥቂት ትበላለች ማለት ነው።
የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ።
፩. እንቋዕ ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አብጽሐክሙ
፪. አሌ ለነ
፫. አንትሙሂ ተሐውሩ ግድመ ግድመ
፬. ሰማይ ወምድር የኀልፍ
፭. ነዋ ወልድኪ ነያ እምከ
የሚከተሉትን የአማርኛ ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉሙ።
፩. ሞት ሳይመጣ እንዋደድ
፪. ስምህ ማን ነው?
፫. የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው?
፬. ዕድሜህ ስንት ነው?
፭. ከትላንት እስከዛሬ
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።