ንስሐን በአስተርጓሚ
ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንጻ ፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሒድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተገኝተው ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ በጠረፋማ አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በቋንቋቸው የሚያስተምሯቸውና ንስሐ የሚሰጧቸው ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት በብዛት እንደሚያስፈልጓቸው ገለጹ፡፡
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች ነን፤ እንደ ሰባቱ ኅብረ ቀለማት መልካችን ዝጕርጕር ነው›› ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰብና ቋንቋ መገኛ መኾኗን አድንቀው በኢትዮጵያ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚገኙ አብዛኞቹ ምእመናን ከአባቶች ካህናት ጋር በቋንቋቸው መግባባት ባለመቻላቸው ንስሐ የሚቀበሉት በአስተርጓሚ በመኾኑ ምእመናኑ ኀጢአታቸውን ሰው እንዳይሰማባቸው ሲሉ ለአስተርጓሚዎች በአግባቡ ላይናገሩ እንደሚችሉ፣ ይህም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት መሰናክል እንደሚኾን በአንዳንድ የሀገረ ስብከታቸው አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ አስገንዝበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ቀደም ሲል እንደ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየጠረፋማ አካባቢዎች በእግራቸው እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክ ያጠመቋቸው ብዙ ሺሕ ምእመናን ቢኖሩም ነገር ግን በቋንቋቸው ወንጌልን የሚሰብኩላቸውና ንስሐ የሚሰጧቸው መምህራንና ካህናት ባለመገኘታቸው የተነሣ ወደ ሌላ እምነት እየተወሰዱ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹በጠረፋማው የአገራችን ክፍል የሚኖሩ ወገኖች የሚጠይቃቸው አጥተዋልና ልንደርስላቸው ይገባል›› የሚሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ማሠልጠኛ ተቋማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን በየቦታው በማስፋፋት በልዩ ልዩ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉ ሰባክያነ ወንጌልንና ካህናትን ማሠልጠን ለዚህ ዅሉ ችግር መፍትሔ እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ ‹‹ዘፀአት›› በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ዲያቆን ብርሃኑ አድማስም የእስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት ታሪክ መነሻ አድርገው እያንዳንዱ ምእመን በፈቃዱ ከተያዘበት የሕሊና ባርነት ነጻ በመውጣት ራሱን ከጥፋትና ከኑፋቄ ከመጠበቅ ባሻገር ሌሎችንም ወደ ክርስትና ሃይማኖት በመመለስ ክርስቲያናዊ ግዴታውን መወጣት እንደሚኖርበት አስተምረዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ አቶ ታምሩ ለጋ በበኩላቸው ማኅበሩ ከአሁን በፊት አዳዲስ አማንያንን በማስጠመቅ፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማስገንባትና ሰበክያነ ወንጌልን በማሠልጠን በጠረፋማ አካባቢዎች ላከናወናቸው ተግባራት ዅሉ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ የሚገኙ አባቶች በጸሎትና በምክር፤ በጎ አድራጊ ምእመናን በዐሳብ፣ በቍሳቍስ አቅርቦት፣ በገንዘብና በጕልበት ላደረጉት ዕገዛና ድጋፍ ምስጋናቸውን በእግዚአብሔር ስም ካቀረቡ በኋላ ማኅበሩ ለወደፊቱ በሰፊው ዐቅዶ ለሚተገብረው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብርም ምእመናን ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ባዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር ገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን መደገፍ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመርዳት ስለሚያስችል ዅሉም ሕዝበ ክርስቲያን የበኩሉን ድርሻ ቢወጣ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስቀጠልና የመናፍቃንን ተጽዕኖ መግታት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ‹‹የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን?›› /ዘፍ.፵፫፥፳፯/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ የቅዱሳን አባቶችን ሕይወታቸውንና የትሩፋት ሥራቸውን በማስረዳት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ቅዱሳት መካናትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን መከባከብና መጠበቅ ተገቢ ተግባር መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡