ነጻነት
ዲያቆን ዳዊት አየለ
ግንቦት ፳፭፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ነጻነት ከሰው ልጅ አፈጣጠር ጋር የተያያዘ ግብር መሆኑን ማወቅ እጅጉን ተገቢ ነው። አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረው ሙሉ ነጻነት ያለው ፍጥረት አድርጎ ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ በተሰጠው አእምሮ የወደደውን (ክፉውን ከሻተ ክፉውን፣ መልካሙን ከሻተ መልካሙን) እንዲመርጥ የመምረጥ መብት ተሰጥቶታል። ፈጣሬ ዓለማት አምላካችን “እነሆ፥ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና ሞትን፥ መልካምነትንና ክፋትን አኑሬአለሁ። ዛሬ እኔ የማዝዝህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ብትሰማ፥ አምላክህን እግዚአብሔርንም ብትወድድ፥ በመንገዶቹም ሁሉ ብትሄድ፥ ሥርዓቱንና ፍርዱንም ብትጠብቅ በሕይወት ትኖራለህ፤ በቁጥርም ትበዛለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም ልትወርሳት በምትሄድበት በምድሪቱ ሁሉ ይባርክሃል። ልብህ ግን ቢስት፥ አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎች አማልክት ብትሰግድ፥ ብታመልካቸውም፥ ፈጽመህ እንደምትጠፋ እኔ ዛሬ እነግርሃለሁ…” በማለት የሰው ልጅ መጥፋትም ሆነ በሕይወት ከብሮ መኖር የራሱ ምርጫ እንጂ እርሱ እግዚአብሔር አስገድዶት እንዳልሆነ ይናገራል። (ዘዳ.፴÷፲፭-፲፰)
ነጻነት ማለት “አርነት፣ ነጻ መሆን፣ መለቀቅ፣ እንደ ልብ መሆን፣ አስገዳጅ አለመኖር፣ ከማንወደውና ከማንፈልገው አካል ወይም ሐሳብ ተጽእኖ ነጻ መሆንና በተሰጠን ልቦና አእምሮ አመዛዝነን መርምረን በራስ መወሰን መቻል” ማለት ሲሆን ለሰው ልጅ የተሰጠ የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ ነው፤ (መዝገበ ቃላት ደስታ ተክለ ወልድ፣ ገጽ ፰፻፸) ) ምክንያቱም ለእርሱ ወደንና ፈቅደን እንድንገዛለት ፍቅራችን ይገለጥ ዘንድ ነጻነትን ሰጠን። ተገደን ሳይሆን በፍቅር እንድንገዛለትና በሕይወት እንድንኖር የሚሻ አምላካችን ክርስቶስ እንዲህ ይላል፤ “ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ.፲፬፥፲፭)። በዚህም መሠረት ነጻነታችንን ተጠቅመን ማንም ሳያስገድደን እግዚአብሔርን እንወደዋለን፤ ስለምንወደውም ትእዛዙን እንጠብቃለን። የነጻነትን ነገር ብዙዎች የሚረዱት ሲያጧት ባርነትን ሲቀምሱና በባርነት ሲኖሩ ነው፤ ልክ እንደ መጀመሪያው ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን።
እንግዲህ የሰው ልጅ እንዲህ በነጻነት ተፈጥሮ በነጻ ፈቃዱ የፈጠረውን አምላክ ሲያመልክና ሲያመሰግን በገነት የቆየው ለሰባት ዓመታት ብቻ ነበር፤ ከሰባት ዓመታት በኋላ ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ የመጀመሪያ ሰዎች የሆኑ አዳምንና ሔዋንን ዕፀ በለስን እንዲበሉ አደረጋቸው፡፡ እንዲህ በማለት “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን፥ ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ፥ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ፥ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ”(ዘፍ.፫ ፥ ፭) እንዲሁም በሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አስተምህሮ “…ሰው ዕፀ በለስን የበላው ነጻ ፈቃዱን አለአግባብ ስለተጠቀመበት ነው።” (ኦሪት ዘፍጥረት ሊቁ እንዳስተማረው ድርሳን ፩-፲፰ እንደተባለ ዲያብሎስ በመከራቸው ምክር ከነጻነታቸው በማዋረድ የራሱና የሞት (ኀጢአት) ባሪያዎች አደረጋቸው። የሰው ልጅ ነጻነት በማጣት ከራሱ ውጭ ለሌላው አካል ባሪያ የመሆን ታሪክ በአዳምና በሔዋን መውደቅ ጀመረ፤ አወዳደቃቸውም ለኀጢአት ተገዝተው የሞት ሞት ተፈርዶባቸው ነበር፤ ይህም የመውደቅና ባርያ የመሆን ታሪክ እጅግ ለዘመናት የቆየ ያለ ወልደ እግዚአብሔር ክቡር ደምና ቅዱስ ሥጋው ነጻ መውጣት የማይቻልም ነበር።
የሰው ልጅ እግዚአብሔር የሰጠውን ነጻነት በመነጠቅ በነጻ ፈቃዱ የዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ ከገነት ወደ ምድር ከተባረረ በኋላ ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲመጡ አንዱ የአንዱን ነጻነት መንፈግና ባሪያ ማድረግም ተለምዶ ነበር። በዘመነ ብሉይ ገና ከሞት ሞት ባርነት ነጻ ያልወጣ ሰው የሌላውን ነጻነት ሲነፍግና ባሪያ ሲያረገው ማየት እጅጉን የሚያሳዝን ነገር ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ትልልቅ ታሪኮች ውስጥ አንደኛውና ዋነኛው የእስራኤላውያን (ዕብራውያን) በግብፅ ምድር በባርነት ለአራት መቶ ሠላሳ ዘመናት መገዛታቸው ነበረ።
እስራኤላውያን (የያዕቆብ ልጆች) “…በምድር ሁሉ ራብ ጸንቶ በነበረበት…”ጊዜ የሚሸመት እህል መኖሩን ሰምተው ምድረ ግብፅ ወርደው ነበር፤ (ዘፍ.፵፩÷፶፯) የፈርዖን እንደራሴና ከዙፋኑ በቀር በሁሉም ነገር ላይ ገዥ አድርጎ በሾመው የያዕቆብ (ስሙ እስራኤል የተባለ) የገዛ ልጁ በሆነው ቅዱስ ዮሴፍ ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸው እህል ሸምተው ተመልሰው ዳግም አባታቸውንና ዘመዶቻቸውን ይዘው “…በከነዓን ሀገርም ያገኙትን ጥሪታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ…”እንደተባለ ወደ ግብፅ ወርደው መኖር ጀመሩ፤ (ዘፍ.፵፮÷፮) በዚያም “…በዙ፤ እጅግም ተባዙ…”(ዘፍ.፵፯÷፳፯)። ዮሴፍ ከሞተ በኋላ “በግብፅ ዮሴፍን ያላወቀ ንጉሥ ተነሣ፡፡ ”(ዘፀ ፩÷፰) እርሱም እስራኤላውያን በምድረ ግብፅ መብዛታቸውንና መበርታታቸውን ባየ ጊዜ ፈራ፤ ፈርቶም ዝም አላለም ሕዝቡንና ሹማምንቱን አስተባብሮ የባርነት ቀንበሩን በብዙ ሰቆቃዎች አከበደባቸው፤ መከራም አጸናባቸው፤ “ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በግፍ ገዙአቸው። በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም፥ በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር።”(ዘፀ.፩÷፲፫-፲፬)
እንዲህ ባለ መከራ ሳሉ “ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮሁም፤ ስለ ባርነታቸውም ጩሀታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም ጩሀታቸውን ሰማ…”(ዘፀ.፪÷፳፫-፳፬) ሰምቶም ዝም አላላቸውም፤ ለአብርሃም አባታቸው “…ደግሞም የሚያሰቃዩአቸውን እኔ እፈርድባቸዋለው።….” ብሎ በገባለት ቃልኪዳን መሠረት ሙሴን አስነስቶላቸው፤ (ዘፍ.፲፭÷፲፮) ተአምራዊ ኃይልን ሰጥቶት ፈርዖንን አስጨንቆት ሕዝቡን ከባርነት ነጻ እንዲወጡ አድርጓቸዋል፤ “እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ በሌሊት ከግብፅ ምድር ወጣ።” (ዘፀ.፲፭÷፲፮) ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ነጻነት አጥቶ በባርነት መኖር እጅግ መጎሳቆልና እግዚአብሔር አምላክን ለማምለክ እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑንና ነጻነት ምን ያክል ትልቅ ዋጋ እንዳለው ነው።
በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ በየሀገራቱና በየግዛቱ ልክ የእስራኤላውያንም ዓይነት ሆነ ከእርሱ የተለየ በሆነ መልኩ ሰዎችን ባርያ አድርገው ወይም በምርኮ የሚገዙና የሚያሠቃዩ አላውያንና ባርያ ወይም ምርኮኛ ሆነው የሚገዙ ምስኪናን ታሪክ በብዛት የነበረና አሁንም በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን መንፈሳዊውን ሕግ ብቻ ሳይሆን ዓለማዊውን መተዳደሪያ ሕግና ደምብ ጥሰው የሰው ልጅን ነጻነት የሚጋፉ ጥቂት አይደሉም፤ በዘመናችን እጅጉን አስከፊ የሆነው ነገር ደሞ የተፈጥሮ ሕግን እንኳ የሚጥሱ (ግብረ ሰዶማውያን) አያሌ መሆናቸው ነው።
በሀገራችን በኢትዮጵያ ብንመለከት እጅግ ብዙ ጊዜ ነጻነታችንን ሊነጥቁን የሚችሉ ታሪኮች ተከስቷል፤ ከነዚህም መካከል ዓለም ያወቀው የጥቁር ሰዎች ሁሉ ኩራት የሆነው የአድዋ ድል ታሪክ ከነበሩት ክስተቶች እጅግ ታላቁ ነበር፤ አባቶቻችን ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን (የኢትዮጵያ ገበዝ) ይዘው በጸሎትና በተጋድሎ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ሀገራችንን ነጻነቷን ጠብቀው አስጠብቀው ለዛሬ አድርሰውልናል።
አሁን ባለንበት ጊዜ በሀገራችን ሕገ መንግሥት መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እምነቱንና አመለካከቱን በነጻነት ማስኬድ እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፳፯ ይደነግጋል፤ ነገር ግን ይሄን የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በሚጻረር መልኩ የመንግሥት አካል ነን ከሚሉ ሰዎች ኦርቶዶክሳውያንን ነጥሎ ማጥቃትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ታዝዘው ( ለምሳሌ ‘ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቁር ልበሱ ካለ ቀኖና ነው’) በሥርዓቱ መሠረት የሚመላለሱትንና የሃይማኖት መምህራን ሆነው ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ዶግማ የሚሟገቱትን የእምነት ነጻነታቸውን በመንፈግ ለእስር መዳረግ፣ ማፈንና መጨቆን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን የሆኑ የመገናኛ ብዙኃንን ማገድ መዝጋት ከቀደሙት አላውያን ነገሥታት ታሪክ ጋር መዛመድ ነው። እኛ ክርስቲያኖች በሕጉ መሠረት እየተመላለስን ሕጉ እስኪከበርልን በሃይማኖታችን ጸንተን “ሥጋችሁን የሚገድሉትን አትፍሩአቸው፤ ከዚህም የበለጠ ማድረግ የሚችሉት የላቸውም። ነገር ግን፤ የምትፈሩትን አሳያችኋለው፤ እናንተስ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ሊጥል ሥልጣን ያለውን ፍሩት፤…”(ሉቃ.፲፪÷፬-፭) ባለንና በሞቱ ሞትን ሽሮ በትንሣኤው ከባርነት ነጻ አውጥቶን አማናዊውን ነጻነት በሰጠን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል መሠረት እንመላለሳለን። የጌታችን ወንድም የተባለው ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብም በስደቱ በመገፋቱ እንዳናዝን እንዲህ “ወንድሞች ሆይ፥ ልዩ ልዩ መክራ በሚመጣባችሁ ጊዜ በሁሉ ደስ ይበላችሁ። በሃይማኖታችሁ የሚመጣው ፈተና ትዕግሥትን እንደሚያደርግላችሁ ዐውቃችሁ፥ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ጤነኞች ትሆኑ ዘንድ ትዕግሥት ፍጹም ግብር አላት” በማለት ያጽናናል። (ያዕ.፩÷፫)
አማናዊው ነጻነት ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣንበት ነው፤ ጌታችን በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሆኖ በቆረሰልን ቅዱስ ሥጋው ባፈሰሰልን ክቡር ደሙ የዕዳ ደብዳቤያችንን ደምስሶልን፣ በሞቱ ሞትን ሽሮልን፣ ዲያብሎስን “ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው።”(ቆላ.፪÷፲፬) በትንሣኤው ብርሃንን ሰጥቶን ከዘለዓለም ሞት ወደ ዘለዓለም ሕይወት የመጣንበት ነው አማናዊው ነጻነት። በዚህ ዓለም በሥጋዊ ነጻነት ብንኖር የነፍስ ነጻነቷን ካላስጠበቅን በሰማይ ቤት ለሚኖረን ሕይወት ወይም መንግሥቱን መውረስ የዚህ ዓለም ነጻነት ዋስትና ሊሆነን አይችልም። በሥጋዊ ሐሳብና ፍላጎት ሳይሆን ሥጋችንን ለነፍሳችን አስገዝተን በመንፈሳዊ መንገድ በመመላለስ ክርስቶስ የሰጠንን አማናዊውን ነጻነታችንን ልንጠብቅና ልናስጠብቅ ይገባናል፤ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “ወንድሞቻችን፥ አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ፡፡”(ሮሜ ፰÷፲፪-፲፫) እንዲሁም “ወንድሞች ሆይ÷ እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋልና፤ ነገር ግን ለሥጋችሁ ፈቃድ ነጻነታችሁን ምክንያት አታድርጉላት” በማለት ነጻ መውጣት ማለት ለዚህ ዓለም ምቹ ሰው መሆን አርነቱን ምክንያት እያደረጉ በሥጋ ፈቃድና መንገድ መጓዝ ማለት እንዳልሆነና ሥጋን ለነፍስ አስገዝቶ በነፍስና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መጓዝ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡(ገላ. ፭፥፲፫)
በኀጢአት ወድቆ ባርያው የሆነ ሰው ነጻነቱን ከኅሊናው ጀምሮ ያጣል፤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚለው “ኃጢአትን የሠራ ሰው ምናልባት ከሰዎች እይታ ይሰወር ይሆናል። ጻድቅና እውነተኛ መስሎም ሊመላለስ ይችል ይሆናል። ከዚህ ዳኛና ከሳሽ (ከኅሊና) ግን ወዴትም ማምለጥ አይችልም። በሄደበት ሁሉ እየተከተለ ይወቅሷል፤ ያስፈራሯል፤ ያስጨንቋል፤ አምርሮም ይገርፏል፤ ያለ አንዳች ዕረፍት በሕዝብ፣ በጓደኞቹ መካከል፣ ምግብ ሊበላ ሲቀመጥ፣ ሲተኛና ሲነሣ ላጠፋው ጥፋት ንስሓ ሊገባ እንደሚገባው እንዲሁም ኃጥአት ከጥንተ ተፈጥሮው ጋር እንደማይስማማና የሚያስከትለውን ቅጣት ይነግሯል።” ይህም ሰው ኃጢአት አድርጎ ከኅሊናው ነጻነት ለማግኘት ወዴትም ማምለጥ እንደማይችል ያሳያል ከንስሓ በቀር እንዲሁም ኃጢአት ሊቁ እንዳለው “ተወዳጆች ሆይ! እንደ ኃጢአት ክፉ የለም። አንድ ጊዜ ሲሠሩት በሐፍረት ካባ የሚያከናንብ ብቻ አይደለምና፤ አስቀድሞ ከነበረው ማስተዋልና ማገናዘብም ያዋርዳል እንጂ” የኃጢአትን ክፋት ተረድተን የግብፅ ምድር ባርነት ከተባለው ኀጢአት፣ ሲዖልና የዲያብሎስ አገዛዝ ነጻ ያወጣንን አምላካችንን ተዘክሮቱን (እግዚአብሔርን ማሰብን) ገንዘብ አድርገን እርሱን እንዳንዘነጋ በጥንቃቄ መመላለስ የነጻነታችን መጠበቂያ ትልቁ መንገድ ነው። (ኦሪት ዘዳግም (፮ ፥ ፲፪)፣ ኦሪት ዘፍጥረት ሊቁ እንዳስተማረው ድርሳን ፩-፲፰ )
አማናዊው ነጻነት ከሥጋዊ ፍላጎቶችና የዓለም ከሆኑ ነግሮች ነጻ መውጣትና መራቅ እንደሆነ አቡነ ሺኖዳ እንዲህ ይላሉ፤ “በሥጋ ሳለን መንፈሳችንን ከዚህ ሥጋ ተጽእኖ ማላቀቅ መቻል አለብን ስንል፦ በአጠቃላይ በዓለም ካሉ ነገሮች መራቅ እንድንችል ነው። ስለዚህ ሰው ይህን አደረገ ማለት በእግዚአብሔር ልጆች ሕይወት ውስጥ ያለውን ሰላምና ነጻነት ያገኛል ማለት ነው።”(የመንፈስ ነጻነት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ)። ስለዚህ በእግዚአብሔር ልጆች (ትእዛዙን ጠብቀው በሕጉ የሚሄዱ) ዘንድ ያለውን ደስታና ነጻነት ለማግኘት እራሳችንን ዕለት ዕለት በንስሓ ሕይወት እየመራንና ከኃጢአት እሥራት ነፍሳችንን ነጻ እያወጣን፣ መንፈሳችንን ከትዕቢት፣ ከውዳሴ ከንቱ፣ ነቀፌታ፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከምድራዊ ምኞቶች፣ ከስሜት ሕዋሳት ተጽእኖ፣ ከኃጢአት ግብር ሁሉና መንገድ ነጻ ማውጣት አለብን፤ ያኔ ነው አማናዊውን ነጻነት ገንዘብ የምናረገውም ለመንግሥተ እግዚአብሔርም በቅተን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ” እንባላለን። (ማቴ.፳፭÷፴፬)
ነጻነታችንን በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ያወጀልንን አምላካችንን አስበን በነጻ ፈቃዳችን ወደነው ትእዛዙን ጠብቀን ነጻነታችንን አስጠብቀን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!