ነገረ ስቅለቱ ለክርስቶስ
በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና
የሊቃውንት ጉባኤ አባል
መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሰሙን መከራ) ባለቤቱ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቅዶ፣ ወስኖ እስከ መስቀል ድረስ በፈቃዱ መከራ የተቀበለበት ጊዜ ነው፡፡ ከሰሙነ ሕማማት ዕለታት መካከል ዕለተ ዓርብ የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹ዕለተ ድኅነት (የድኅነት ቀን)› ይባላል፡፡ አምላካችን ሥራውን ያለ ምክንያት አይሠራውምና ለሕማሙና ለሞቱ መንሥኤ ከኾኑት ጉዳዮች መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፤
አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ
‹‹የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሏቸው፤ ‹እነሆ ይህን ሰው ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፡፡ ምን እናድርግ? እንዲሁ ብንተወውም ዅሉ ያምንበታል፡፡ የሮም ሰዎችም መጥተው አገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል›፡፡ ሊቀ ካህናት ቀያፋም ‹ሕዝቡ ዅሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል› አላቸው፤›› (ዮሐ. ፲፩፥፵፯-፶) ተብሎ እንደ ተጻፈ ለጌታችን መከራ መቀበል አንዱ ምክንያት አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ ነው፡፡
በምስጋና ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱና ተአምራትን ማድረጉ
በዕለተ ሆሣዕና በሕፃናት አንደበት ሳይቀር በሕዝቡ ዅሉ እየተመሰገነ ጌታችን ወደ ቤቱ መቅደስ መግባቱና በዚያ ወቅት ያደረገው ተአምራት ሌላው የመከራው ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት፤ ልጆችንም በቤተ መቅደስ ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ› እያሉ ሲጮኹ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም፤›› እንዲል (ማቴ. ፳፩፥፲፭)፡፡
ስለዚህም በሆሣዕና ማግሥት (ሰኞ ዕለት) የአይሁድ ባለ ሥልጣናት ጌታችንን ለመግደል የአድማ ስብሰባ አድርገው ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ በድጋሜ ማክሰኞ ዕለት ተሰብስበው አሁንም ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ረቡዕ ተሰባሰቡ፤ በዚህ ዕለት ዅሉም አንድ ኾነው ይሙት በቃ የሚል ፍርድ በጌታችን ላይ ወስነው ስበሰባቸውን ደመደሙ (የመጋቢት ፳፫ እና ፳፬ ቀን ስንክሳር)፡፡
በዚህ ጊዜ ጌታችንን አሳልፎ የሚሰጣቸው ምሥጢረኛ ቤተሰብ የኾናቸውን ይሁዳን በማግኘታቸው ደስ አላቸው፡፡ ሠላሳ ብር ሊሰጡትም ተስማሙ፡፡ እርሱም ደስ ብሎት ሰው ሳይኖር አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ቦታ ይሻ ነበር፤ ከዚያም ጌታችንን ለአይሁድ አሳልፎ ሰጠው (ሉቃ. ፳፪፥፫-፮)፡፡
ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ‹‹ይህን አጥፍቶአል›› የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡ ‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡
አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታሕዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድ አታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይ ክርስቶስን መግደል አይገባንም፤ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡
ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ የተፈጸሙ ተአምራት
ጌታችን በተሰቀለ ጊዜም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤
፩. ፀሐይ ጨለመ፤
፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤
፫. ከዋክብት ረገፉ፤
፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤
፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤
፮. መቃብራት ተከፈቱ፤
፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡
ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤
፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤
፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤
፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤
፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤
፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››
፮. ‹‹ተጠማሁ››፤
፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡
ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቆየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡
በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ጌቴሴማኒ ይዞ ከሔደ በኋላ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ ‹‹ሰውነቴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች፤›› እያለ ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም እስኪወርድ ድረስ እየወደቀ እየተነሣ በስግደት በኀዘን እንደ መሠረተው ዅሉ፣ የክርስቶስ ተከታይ በሙሉ በኀዘን፣ በለቅሶ እየሰገደ የፈጣሪውን ውለታ የሚያስብበት፤ ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት ወቅት ነው – ሰሙነ ሕማማት (ማቴ. ፳፮፥፴፰፤ ማር. ፲፬፥፴፬፤ ሉቃ. ፳፪፥፵፬)፡፡
‹‹… ክርስቶስ ተሰቅለ በሥጋሁ በእንቲአነ ወአንትሙኒ ተወልተዉ በይእቲ ሕሊና እስመ ዘሐመ በሥጋሁ ድኅነ እምኃጣውኡ፤ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋው ከተሰቀለ እናንተም ይህችን አሳብ ጋሻ አድርጋችሁ ኑሩ፡፡ በሥጋው መከራ የተቀበለ ከኃጢአት ድኖአልና፤›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ አጥብቆ የመከረን ስለዚህ ነው (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፩)፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡