“ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰)
ዲያቆን ልሳነጽድቅ ኪዳነ
ስለ እመቤታችን ምሥጋና በአግባቡ ለመረዳት ቅዱሳት መጻሕፍት በሰከነ አእምሮ ከማጥናት እና ከማንበብ ባለፈ ድንግልን ለማመስገን የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መሠረት መሆኑ የታወቀ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው›› (ሮሜ፡፰፥፬) እንዳለው ያለ መንፈስ ቅዱስ መሪነት ማንኛውም ተግባር ማከናወን እና የተቃና እውነተኛ ሕይወት መምራት አይቻልም፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሕይወትን መምራት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ምልክት ነው፡፡ ለእመቤታችን ምስጋና፣ ስግደት ስለ ማቅረብ ስለ አማላጅነቷ እንዲሁም ክብሯን ለመቀበል የሚታወኩትን ስንመለከት ከአእምሮ በላይ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ አሠራርን አለማስተዋላቸውንና የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናቸውን እንረዳለን፡፡ እመቤታችንን ለማመስገን የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ረዳትነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ቅድስት ድንግል ማርያምን ማመስገን አይቻልም፡፡
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያት ዜናቸው አንቺ ነሽ›› ያላትን እመቤታችንን አበው በሱባኤያቸው መልስ ያገኙባትን አለመቀበል የአእምሮ ይቡስነት (ድንቁርና) ተጭኖታል ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘማክሰኞ ፮)
ቅዱሳት መጻሕፍት በመተባበር የሚመሠክሩት እመቤታችንን ለማመስገን የመንፈስ ቅዱስ ረድኤት አስፈላጊ ስለ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም በአጭሩ ሁለት ምስክርነት ማለትም ከሰማያውያን ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል እና ከምድራውያን የቅድስት ኤልሳቤጥ ምስክርነት እናያለን፡፡
ቅዱስ ገብርኤል የተላከው ከእግዚአብሔር ለመሆኑ እያንዳንዱ ያቀረበው ምስጋናና አክብሮት ምስክር ነው፡፡ ቃሉም የሚለው ‹‹ወበሳድስ ወርኀ ተፈነወ ገብርኤል መልእክ እምኀበ እግዚአብሔር፤ በስድስተኛው ወር ገብርኤል መልአክ ከእግዚአብሔር ተላከ›› ….የተላከው ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እርሷ ገብቶ እየወደቀ እየተነሳ ክብርት ልዕልት ንጽህት መሆኗን እና ስለ ተሰጣት ጸጋ ተጠንቅቆ በቅደም ተከተል የተናገረው እንዲህ በማለት ነበር ‹‹ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ›› አላት፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱)
ሌላ ምስክርነት ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለእመቤታችን ያቀረበችው ምስጋና ነው፡፡ ስለ ድንግል ማርያም እና ስለ ልጇ ወዳጅዋ የመሰከረችው በመንፈስ ቅዱስ ተመርታ ነበር። ይህም ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ እንዲህ በማለት ምስክርነቱን ይሰጣል ‹‹ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማሕጸኗ ውስጥ በደስታ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት››። ድምጿን አሰምታ እንዲህ አለች ‹‹አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታየ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮየ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅጸኔ በደስታ ዘልዋልና››። ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማል እና ያመነች ብጽዕት ናት። (ሉቃ.፩፥፵፩-፵፮)
የፅንሱ በማኅፀን መዝለል እና ማመስገን፣ የቅዱስ ገብርኤል የምስጋና አቀራረብና ምስክርነት እንዲሁም እመቤታችን እና የመልአኩ ቃለ ተዋስኦ ምስጋናዋ ከእግዚአብሔር ስለ መሆኑ በቂ ማሳያ ነው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል›› ማለትም ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ያፌት እና ትውልደ ካም ያመሰግኑኛል ብላለች። (ሉቃ.፩፥፵፰)
ከእግዚአብሔር የተላከ ብርሃናዊ መልአክ ካመሰገናትና በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘች ቅድስት ኤልሳቤጥ ካወደሰቻት በማኅፀን ያለ ፅንስም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ከሰገደ ዛሬም እመቤታችንን ማመስገን የእግዚአብሔር ልጅ መሆንና ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የመቀበል አንዱ ምልክት ነው፡፡ እመቤታችን አለማመስገን ከእግዚአብሔር ልጅነት መውጣት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ እግዚአብሔር የተቀበላቸውን እና ያከበራቸውን አለመቀበል እንዲሁም አለማክበር የእግዚአብሔርን ፍቃድ አለመፈጸምና እግዚአብሔርን አለማክበር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ነበር ያለው ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል›› (ማቴ. ፲፥፵)
ስለዚህም እመቤታችንን ማመን ማለት ክብሯን ንጽህናዋን፣ ቅድስናዋን እና ምስጋናዋን መቀበል ማለት ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የምናየው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚከተለው ይሆናል። በኦሪት ዘጸኣት እንደምንመለከው ‹‹በዚያን ቀን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው ፤…እግዚአብሔር በእንዴት ያለ ታላቅ ኃይል ግብጻውያንን እንዳሸነፈ እስራኤላውያን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን ፈሩ በእግዚአብሔር እና በሙሴ አመኑ›› አሁን እስራኤላያን በሙሴ እና በእግዚአብሔር አመኑ ተብሎ መጸፉ እስራኤላውያን ሙሴ እና እግዚአብሔርን አስተካክለው አመለኩ እንዲሁም ሙሴን እንደ እግዚአብሔር አዩት ማለት አይደለም። አስራኤላውያን በእግዚእብሔር ያመኑበት ማመን እና በሙሴ ያመኑበት ማመን የተለየ መሆኑ አስተዋይ ሰው ልብ ይለዋል። (ዘጸ. ፬፥፩ ፤ ዮሐ. ፭፥፮)
እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምናመሰግናት ስለተሰጣት ጸጋ እና ክብር ነው። የተሰጣት ክብር ደግሞ ከጸጋ ባለቤት ከልዑል እግዚአብሔር መሆኑን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ስለ ተሰጣትም የእግዚአብሔር ጸጋ የሔዋን መርገም በእርሷ ላይ ተቋረጠ እንዲህ ያለ ስጦታ ለአዳም እና ለዘሩ እስከ ዘለዓለም ለሌላ አልተሰጠም።›› በዚህ ብቻ ሳይሆን ስለ ንጽሕኗዋ፣ ስለ ቅድስናዋ ጭምር ምስጋና እናቀርባለን።
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ከመውደዱ የተነሳ እመቤቴ ምስጋናዋ እንደሰማይ ኮከብ እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለብሼው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤ እያለ ሲመኝ ይኖር ነበረ። የሚሹትን መግለጽ ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና፤ ገልጾለት * ከአራት ሺህ በላይ ድርሰት ደርሷል። አኃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ እስኪል ድረስ ። ሊቁ ያቀረበው ምስጋና መነሻው መንፈስ ቅዱስ እንደነበረ የሚከተለውን የአበው ትርጉም እንመልከት፡። “የነግህ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን ትመጣለች የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል። በዚያም ላይ ሁና ሰላም ለከ ኦፍቁርየ ኤፍሬም ትለዋለች፤ እርሱም ታጥቆ እጆ ነሥቶ ይቆማል። ወድሰኒ ትለዋለች፤ እፎ እክል ወዶሶኪ ዘኢይክሉ ሰማያውያን ወምድራውያን። ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት ሰማያውያን መላእክተ አንቺን ማመስግን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል አላት። በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ ተናገር፤ መንፈስ ቅዱስ እንዳናገረህ ተናገር አለችው። በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና …ከዚህም በኋላ ባርክኒ ይላታል፤ በረከተ ወልድየ ወአቡሁ መንፈስ ቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ ትልዋለች ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀመራል።
ስለ እመቤታችን ምስጋና እኛ ሊቁን ተከትለን “ብጽዕት አንቲ ኦ እግዝእትነ ማርያም ወላደተ አምላክ፤ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ንዕድ ነሽ ክብር ነሽ። እስመ ብዓንኪ ዘአልቦ ትርጓሜ። ለምስጋናሽ ምሳሌ የለውምና። በማለት ክብሯን፣ በምስጋናዋን ከማግነን ሌላ ምን እንላልን። ሰው ሁኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚል እያለን የባሕርያችን መመኪያ ድንግል ማርያምን በማመስገን እና በመማጸን በርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጸንተን ለመኖር ያብቃን፤ አሜን፡፡