ትኩረት ለፊደላት
ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም.
በዳዊት ደስታ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን በርካታ ነገሮችን አበርክታለች፡፡ ከዚህም ካበረከተቻቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል እንዲኖራት በማድረግ ነው፡፡ የቅርሳቅርስ ጥናት ሊቃውንትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚያረጋግጡት የአጻጻፍ ስልት በኢትዮጵያ የተጀመረው ከጌታ ልደት በፊት እንደነበር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጭር የታሪክ የሃይማኖትና የሥርዐት መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ /ገጽ. 9-11/
በአክሱም ዘመነ መንግሥት የሳባውያንና የአግዓዝያን ፊደላት በኅብረት ይሠራባቸው ነበር፡፡ በአክሱም ዘመነ መንግሥት ግን የግእዝ ፊደልና የግእዝ ቋንቋ እያደገ ስለመጣ በክርስቲያን ነገሥታት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በሐውልቶችና በሌላም መዛግብት የተጻፉ ጽሑፎች በግእዝ ፊደልና በግእዝ ቋንቋ ተጽፈው እናገኛለን፡፡ የጽሑፍ መሠረት የሆነው ፊደልና የጽሑፍ ስልት በደንብ የታወቀው የክርስትና ሃይማኖት ማለት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በኢትዮጵያ መስፋፋት በጀመረበት ወቅት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
የፊደል መነሻ
የግእዝ ፊደል መነሻ መልክእንና ቅርፅን በመስጠት እንዲስፋፋ ያደረጉት በአክሱም ዘመነ መንግሥት የነበሩ የቤተ ክርስቲያን /የቤተ ክህነት/ ሰዎች መሆናቸው የታመነ ነው፡፡ በሥነ ጽሑፍ የምትታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ መሠረቷና መነሻዋ ፊደል ነው፡፡ ፊደል ያልተቀረፀለት ፣ጽሑፍ ያልተሰጠው ማንኛውም ቋንቋ ሁሉ መሠረት ስለሌለው የሚሰጠው አገልግሎት ያልተሟላ ነው፡፡ መሠረታዊ ቋንቋ ታሪካዊ ቋንቋ ተብሎ የሚሰየመው ፊደል ተቀርጾለት የምርምርና የሥነ ጽሑፍ መሠረት በመሆን ለትውልድ ሲተላለፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የታሪክ ማኅደር እንደመሆኗ ለግእዝና ለአማርኛ ቋንቋ መሠረትና መነሻ የሆነውን ፊደል ቅርጽና መልክ ሰጥታ ሕዝቡ እንዲጠቀምበት፣ ሥነ ጽሑፍ እንዲስፋፋና ታሪክ እንዲመዘገብ፣ ያለፈውን የማንነት አሻራ እንድናውቅ፣ አሁን ያለንበትን እንድንረዳና ወደፊት ስለሚሆነውም ዝግጅት እንድናደርግ በፊደል አማካኝነት ድርሳናትን ጽፈን እንጠቀም ዘንድ ፊደል መጠቀም ተጀመረ፡፡
ምክንያተ ጽሕፈት
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በመስከረም ወር ስለ ኢትዮጵያ ፊደል መሻሻል በሚዩዚክ ሜይዴይ አዘጋጅነት ለውይይት የሚረዳ መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አማርኛ ፊደል ለመሻሻሉ መነሻ ያሉትን ምክንያትና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማንሳት አሁን ያለው እየተገለገልንበት ያለው ፊደል ችግር አለው ያሉበትን ምክንያት አቅርበዋል፡፡ ፊደላቱ ተመሳሳይነት ድምጽ ስላላቸው ሊቀነሱ ይገባል በማለት ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡በዕለቱ የተለያዩ ምሑራን በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ስለነበር ጽሑፍ አቅራቢውን ሞግተዋቸዋል፡፡ የእኛም ዝግጅት ክፍል ፊደላት መቀነሳቸው/መሻሻላቸው/ የሚያመጣው ችግር ምን እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመጠየቅ ምላሻቸውን አአስነብበናችሁ ነበር፡፡ ከዚህም በተለጨማሪ የቋንቋ ባለሙያዎች በእንደዚሁ ዓይነት የውይይት መድረኮች በመገኘት ምላሽ ሰጥተው በጽድፎቻቸውም በመጽሐፋቻቸውም ትክክለኛውን ለንባብ አብቅተውልናል፡፡
ይኼ ጽሑፍ የግእዝ ፊደል አመጣጥን የሚተርክ ሳይሆን ፊደላቱ ይሻሻሉ የተባለበትን መንገድ መሠረት አድርገን ምላሽ ብለን የምናስበውን የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም ነው፡፡ ተመሳሳይነት ያላቸውን ፊደላት ይቀነሱ፣ ይሻሻሉ…ወዘተ የሚሉ አሳቦች መቅረብ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም እነ ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” በሚል መጽሐፋቸው የተወጠነው፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል የተዋሀደው ፊደላትን የመቀነስ ዘመቻ በመጽሔቶችና ጋዜጦች ብቻ ሳይሆን በጥናታዊ ጽሑፎችና በፈጠራ ድርሰቶች ሳይቀር ይዞታውን እያስፋፋ እንደመጣ /ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ሥዩም፣ ትንሣኤ አማርኛ፣ ግእዝ መዝገበ ቃላት/ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል፡፡
የዚህ ፊደል የማሻሻል ዘመቻ የፊደል ገበታችን አካል የሆኑት “ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ ሠ፣ሰ፣አ፣ዐ እና ጸ” ፊደላቱ ከትውልዱ አእምሮ ውስጥ መፋቅ /መጥፋት/አለባቸው የሚል አሳብ የያዘ ይመስላል፡፡ ይህን ዘመቻ በመቃወም ብዙ ሊቃውንት ብዕራቸውን አንስተዋል፣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በኅትመት ውጤቶቹ በሆኑት ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ላይ የቋንቋ ምሁራንና የቤተ ክርስቲያናችንን ሊቃውንት በማናገር ምላሽ ብሎ ያሰበውን በተከታታይ ኅትመቶች አስነብቦናል፡፡
እነዚህ ፊደላት ተመሳሳይነት አላቸው የተባሉት የ“ሀ፣ ሐ፣ ኀ፤ ሠ፣ ሰ፤ አ፣ ዐ እና ጸ፣ ፀ” ፊደላት ቀደም ባለው ጊዜ በግእዝ፣ በተለይ ደግሞ በትግርኛ ቋንቋዎች የየራሳቸው መካነ ንባብና ድምፀት ስላላቸውና እልፍ አእላፋት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም ስለተሠሩባቸው ፊደላቱን መቀነስ ኪሣራ እንጂ ትርፍ የለውም የሚል አስተያየት ከብዙ ምሁራን ተሰጥቶበጣል ፡፡
ከዚህ በመነሣት የፊደል ይቀነሱ፣ይሻሻሉ የሚሉት ጥያቄዎች ስናጤነው አንድን ፊደል በሌላ ፊደል ማጣፋት፣ ከቃላት ወይም ሐረጋት ፍቺ እንዲያጡ ወይም የተዛባ ፍቺ እንዲሰጡ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም አንድ ቀላል ምሳሌ ማንሳት እንችላለን፡፡ በግእዝ ቋንቋ “ሠረቀ” ማለት ወጣ፣ ታየ፣ ተገለጠ ማለት ሲሆን፣ “ሰረቀ” ማለት ደግሞ ሰረቀ፣ ቀጠፈ፣ አበላሸ ማለት ነው፡፡ የቃሉ ማእከላዊ ድምፅ “ረ” በሁለቱም አይጠብቀም፡፡ ጠብቆ ከተነበበ ስድብ ይሆናል፡፡ “ሠረቀ” የሚለውን ቃል የተወሰኑ ሰዎች ሲጠሩበት እናውቃለን፡፡ የአባት ስም ብርሃን፣ ፀሐይ ሕይወት ወዘተ ቢሆንና ሙሉ ስም አድርገን ስንጠራቸው ሠረቀ ብርሃን፣ ሠረቀ ፀሐይ፣ ሠረቀ ሕይወት እንላቸዋለን፡፡ ነገር ግን ንጉሡን “ሠ” በእሳቱ “ሰ” ቀይረን ብንጽፍ “ሌባው ብርሃን፣ ሌባው ፀሐይ. . .” እያልን የስድብ ቃል/ትርጉም/ ስለሚያመጣ ፊደላቱን አገባባቸውን የሚሰጡትን ትርጉም ካላወቅን ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡
ሌላው ግእዝ “ሀ” በራብዕ “ሃ” አና “አ” በ”ኣ” መተካቱ ደግሞ “ሳይቸግር ጨው ብድር” የሚለውን የሀገራችንን አባባል የሚያስታውሰን ይመስለኛል፡፡ ሌላም እንመልከት ሀብታም ስንል ባለፀጋ ማለት ሲሆን ‹‹ሐብታም›› ካልን ደግሞ ዘማዊ ይሆናል፡፡ሰገል ጥበብ ማለት ሲሆን ሠገል ጥንቆላ ማለት ነው፡፡ ሰብዓ ፸ ቁጥር ሲሆን ሰብአ ሰዎች ማለት ነው፡፡ ሰአለ ለመነ ማለት ሲሆን ሠዓለ ሲሆን ደግሞ ሥዕል ሳለ ማለት ነው፡፡ ፊደላቱ አንዱ ባንዱ መቀየራቸው ወይም መተካታቸው ችግሮች እንደሚፈጥሩ ከላይ ያየነው ምሳሌ ጥሩ አድርጎ ያስረዳናል፡፡
ለዚህም አንዱ ከሌላው የሚሰጠውን የተለየ ትርጉም አለማወቅ የሚያመጣውን ችግርን አስመልክቶ ወጣቱ ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም “ሶልያና” በተሰኘው የግጥም የድምፅ መድብሉ በቅኔ መልክ ያቀረበውን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ የግጥሙ ርእስ “እሳቱ ሰ” የሚል ነው፡፡
“ይኼው በጉብዝናም በፈቃድ ስተት
ትርጓሜው አይደለም አንድ ነው ማለት
እጽፋለሁ ጽፈት እስታለሁ ስተት
እሳት ስባል ንጉሥ፣ ንጉሥ ስባል እሳት”
እያለ ገጣሚው ፊደላት ያለ አገባባቸው ቢገቡ፣ የሚፈጥረውን የአሳብና የትርጉም ስሕተት እንደሚያመጣ ከፊደል ገበታ እንዲሠረዙ መደረጉ ያሳደረበትን የቁጭት ስሜት አሰምቶናል፡፡ ፊደላችን ይቀነስ፣ ይሻሻል የሚሉ አሳቦችን ከማንሳት በፊት ቀድሞ ሊነሣ የሚገባው ፊደላቱ የሚሰጡትን ድምጽና ትርጉም ማወቅ ከዚያም መቀነሳቸው ወይም መሻሻላቸው በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ማየት ያስፈልጋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ የታሪክና የቅርስ ማጥፋት ሥራ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ፊደላቱ የሚሰጡትን ድምጽና ትርጉም አውቆ የአንዱ ፊደል መውጣት መሻሻል ለረጅም ዘመናት የተጻፉ መጻሕፍት የአሳብ፣ የትርጉም፣ የቅርስ ጥፋት እንደሚያመጣ ማወቅ ይሻል፡፡ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዳግም ጥያቄ በማያስነሳ መልኩ ትክክለኛውን ነገር ሊያስቀምጡና ጥናት በማጥናት ምላሻቸውን ሊሰጡ ይገባል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ባለድርሻ የሆነችው ቅደስት ቤተ ክርስትያን ምላሿን ማሳወቅ እንደሚገባት የጥያቄው መብዛት አፋጣኝ እንደሆነ ያመላክታል፡፡