ትምህርት ቤቱ በ፳፻፱ ዓ.ም ሥራ እንደሚጀምር ተገለጠ

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በይብረሁ ይጥና

በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ነቀምቴ ከተማ በምስካበ ቅዱሳን ዑራኤል ወሳሙኤል ገዳም ሀገረ ስብከቱና ማኅበረ ቅዱሳን በጋራ ያስገነቡት ትምህርት ቤት በ፳፻፱ ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሥራ እንደሚጀምር ተገለጠ፡፡

school

ሀገረ ስብከቱ ዘመናዊ ት/ቤት ሲገነባ የመጀመሪያው መኾኑን የጠቀሱት የምሥራቅና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ስምዖን ‹‹መረዳዳቱ፣ አንድነቱና መፈቃቀሩ ካለ ከዚህ የበለጠ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ሌሎችንም የልማት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል!›› ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በኵረ ትጉሃን ቀሲስ ገናናው አክሊሉ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፻፰ ዓ.ም ለመገንባት ዕቅድ ከያዘላቸው ፕሮጀክቶች መካከል ይህ የፈለገ ጥበብ መዋዕለ ሕፃናት ት/ቤት ፕሮጀክት አንዱ መኾኑን የገለጡት በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲ/ን አእምሮ ይኄይስ የፕሮጀክቱ ግብ በሥነ ምግባር የበለጸገ የሰው ኃይል ማፍራትና ከት/ቤቱ በሚገኘው ገቢም የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በድምሩ ፻፳ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችለው ትምህርት ቤቱ የመማሪያ፤ ለመምህራን ቢሮና ለሕፃናት ማረፊያ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት ክፍሎች፤ መጸዳጃ ቤትና የንጹሕ ውኃ ቧንቧዎች እንደ ተዘጋጁለት፤ ት/ቤቱን ለማስገንባትም ከአንድ ሚሊዮን ሰባ አምስት ሺሕ ብር በላይ ወጪ እንደ ተደረገና ከዚህ ውስጥ ከስምንት መቶ ሺሕ ብር በላይ የሚኾነው ወጪ በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል፤ ቀሪው ደግሞ በሀገረ ስብከቱ እንደ ተሸፈነ በምረቃው ዕለት ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዕለቱ ካነጋገርናቸው አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ላእከ ምእመናን ሽፈራው በቀለና ወ/ሮ መሠረት ታደሰ ቤተ ክርስቲያን የልማት ምሳሌና አርአያ መኾኗን ጠቅሰው ትምህርት ቤቱ በአካባቢያቸው መገንባቱ ልጆቻቸው በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉና ለአገራቸው ጥሩ ዜጋ እንዲኾኑ በማስቻል ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡