ታላቁ የቅኔ ጉባኤ ቤት በእሳት ወደመ

chegodie

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቋሪት ወረዳ ቤተ ክህነት ልዩ ስሙ ፈንገጣ በሚባል ቀበሌ በጨጎዴ ሐና የተቋቋመው፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ሲያፈራ የኖረውና እስከ አሁን ድረስም ሊቃውንትን የመተካት ተልእኮውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው የቅኔ ምስክር ጉባኤ ቤት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ድንገት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ወደመ፡፡

100_0718

የጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ከከፊል ደቀ መዛሙርታቸው ጋር (ጉባኤ ቤቱ በእሳት ከመቃጠሉ በፊት)

በቦታው የተገኙ የዓይን እማኞች እንደሚያስረዱት በአካባቢው ያለው የአየር ጠባይዕ ነፋሻ ከመኾኑ፣ ጉባኤ ቤቱ ከእንጨትና ከሣር ከመሠራቱ ባሻገር ደቀ መዛሙርቱ ለክብረ በዓል በወጡበትና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን በሔዱበት ሰዓት ቃጠሎው መከሠቱ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡፡

ድንገት በደረሰው በዚህ የእሳት ቃጠሎ ሁለት መቶ ሃያ አምስት የደቀ መዛሙርት መኖሪያ ጎጆዎች፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍት፣ ምግብ እና አልባሳት በአጠቃላይ ከሰባት መቶ ስልሳ ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የፍኖተ ሰላም ማእከል የላከልን ዘገባ ያመላክታል፡፡

ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ጉባኤ ቤቱ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ የሚደርሱ ደቀ መዛሙርት ይማሩበት የነበረ ሲኾን በአሁኑ ሰዓትም በከፊል ከቃጠሎው በተረፈው የጉባኤ ቤቱ ማኅበር ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

chegodie

የእሳት ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት በከፊል

የቋሪት ወረዳ ማእከል ከቦታው ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጸው እሳቱ የተነሣው ከጉባኤ ቤቱ አጥር አካባቢ ሲኾን፣ እሳቱ በምን ምክንያትና በማን አማካይነት እንደ ተለኮሰ ለማረጋገጥ መንሥኤው በፖሊስ በመጣራት ላይ ይገኛል፡፡

ለደቀ መዛሙርቱ ምግብ፣ መጠለያና አልባሳት ድጋፍ ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚገባም የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ከፍኖተ ሰላም ማእከልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ውይይት በማካሔድ ላይ እንደሚገኝ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ አያና በላቸው ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ጉባኤ ቤቱን ወደ ነበረበት ህልውና ለመመለስ፤ ደቀ መዛሙርቱን ከመበተንና የጉባኤውን ወንበርም ከመታጠፍ ለመታደግ እንችል ዘንድ ‹‹መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፋችሁ አይለየን?›› ሲሉ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው በጉባኤ ቤቱ ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ቤት ላይ በደረሰው ጉዳት ለጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው፣ ለደቀ መዛሙርቱና ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን መጽናናትን ይመኛል፡፡