ተጠያቂው ማነው?
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፳፬፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
መምሬ እውነቱ ከንስሓ ልጆቻቸው ጋር በመሆን ሕሙማንን ለመጠየቅ በያዙት መርሐ ግብር መሠረት ከምእመናኑ ተወካዮች እና ከማኅበረ ካህናቱ ተወካዮች ጋር የተቃጠሩበት ሰዓት እስኪደርስ ከግቢያቸው ካለው ዛፍ ሥር ተቀምጠው ሌሎቹን በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም በጸበል ቦታ እንዲሁም በማረሚያ ቤት ያሉትን ሄደው አጽናንተዋል፤ የዛሬ ቀጠሯቸው ደግሞ የሕይወት ውጣ ውረድ ጫና ፈጥሮባቸው ለአእምሮ መቃወስ የተዳረጉ፣ በጭንቀት አዘቅት ሰጥመው ሰውን በሚጎዱ ሱስ ተጠምደው ያሉና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በዘመናዊ ሆስፒታል ያሉትን ወገኖች በማጽናት የተወሰነ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ መምሬ እውነቱ ወደዚህ ሥፍራ ለመሄድ ያቀዱት አንድ የንስሓ ልጃቸው አባት በልጃቸው የደረሰውን አሳዛኝ የሕይወት ገጠመኝ ስላጫወቷቸውና ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ የሕይወት ቀውስ የደረሰባቸውን ከዚህ የጭንቀት አዘቅት እንዲወጡ በጸሎትም፣ በምክርም ለማገዝ በማለት ነበር!
መምሬ እውነቱ ቁጭ ብለው የሰሙትን ታሪክ እያሰላሰሉ በሐሳብ ነጉደዋል፤ ወላጅ ልጆችን በአግባቡ አርሞና ቀጥቶ ባለማሳደጉ ልጆች በተሳሳተ መንግድ ተጉዘው በማደጋቸው ለራሳቸው፣ ለቤተሰብና አልፎም ለአገር ራስ ምታት እንደሚሆኑ ከሰሙት ታሪክ ተረድተዋል፡፡ መምሬ እውነቱ ሁል ጊዜ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለወላጆች! ‹‹ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፤ ታዲያ ወላጅ ባለ አደራ እንደ መሆኑ በእንክብካቤ የአቅሙን እያደረገ ማሳደግ አለበት! በሥነ ምግባር ተኮትኩተው ያድጉ ዘንድ ቤተ እግዚአብሔር ስንመጣ ይዘናቸው ልንመጣ ይገባል፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዚህ አብነታችን ናት፤ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ትወስደው ነበር …›› በማለት አባታዊ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ!
የንስሓ ልጃቸው ያጫወቷቸው ታሪክ ግን ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ ወጣቱ በልጅነቱ እምብዛም የእነርሱ ክትትል አልነበረውም፤ ወላጅ በቅርበት ሆኖ ባለመከታተሉ በመንፈሳዊውም ሆነ በፍልስፍናው ዓለም ትምህርቱ ደካማ ከመሆኑ በተጓዳኝ ለሕይወቱ መስመር መሳት ጉልህ አስተዋጽኦ ሆኗል፤ የእርሳቸው የልጅ ልጅ ግርማዬ ዕድለኛ ነው፡፡ ለብዙዎች አርአያ የሆኑ አባት አሉት፤ ቀጥ ብሎ ሳይጣመም ያድግ ዘንድ ክፉና ደጉን እያሳወቁ አሳድገውታል፡፡ የልጃቸው ምኞት ተሳክቶላት እንደ አባቷ ልጇ ግርማዬ በቤተ መቅደስ የሚያገለግል ሆኖላታል፡፡ እርሳቸውም ፈለጋቸውን የሚከተል እንዳወጡለት ስም ግርማ የሚሆናቸው የልጅ ልጃቸውን እየተጓዘበት ያለውን ቀና መንገድ በማየታቸው ለዚህ ያበቃላቸውን ፈጣሪ ሁሌ ያመሰግናሉ፤ መጨረሻውን ያሳምርለት ዘንድ በጸሎትም፣ በምክርም ያግዙታል፤ እርሱም አላሳፈሩቸውም፤ በመንፈሳዊውም ሆነ በፍልስፍናው ዓለም የሚያኮራ ውጤትን በማስመዝገብ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአያቱ ለወ/ሮ ማዕረግ ነሽና ለመምሬ እውነቱ ገና በልጅነቱ ኩራት እየሆነ ነው፡፡
መምሬ እውነቱ ይህን እያሰላሰሉ ሳለ ግርማዬ የተፈጨ ዱቄት ተሸክሞ ከፊት ወ/ሮ ማዕረግነሽ ከኋላው ሆነው የግቢውን በር ከፍተው ገቡ፤ መምሬ እውነቱ ባዩት ነገር ደስታቸው ገደብ አጣ፤ ትንሹ ግርማዬ አድጎ ለቁም ነገር ደርሶ አያቱን ማገልገል ጀምሮ ከወ/ሮ ማዕረግ ነሽ ትከሻ ከመታዘሉ አልፎ ሸክማቸውን የሚያግዝ ሆኖ ሲመለከቱት በዝምታ የደስታን ዕንባ አነቡ፤ ዓይኖቻቸውን ወደ ላይ አቅንተው እጆቻቸውን ዘርግተው “ተመስገን ጌታዬ ምን ተስኖህ! ትንሹ ግርማዬ አድጎ ክብሬን ለማገዝ በቃ ..” አሉ፡፡ ሳይታወቃቸው ከዓይናቸው የወጣውን ዕንባ በጋቢያቸው ዕራፊ ጠርገው መጣችሁ እሳይ! አሉ፡፡ ወ/ሮ ማዕረግነሽ “አዎ ቆይተን አዘገየንዎት!” አሉ፤ መምሬ እውነቱ ፈጠን ብለው “አይ ክብሬ ሰዓቱ ገና ነው፤ እንግዶቹም ገና አልመጡም! ብለው የማጽናኛ ቃላቸውን አስተላለፉ፡፡ ወ/ሮ ማዕረግነሽ ‹‹..እንግዲያውስ ደኅና… ስትመጡ በዚሁ ይዘዋቸው ይምጡ፡፡ ምሳ አዘጋጅቼ እጠብቃለው፡፡ ከድካማቸው አረፍ ብለው ምሳ በልተው ጥማቸውን አርክተው ይሄዳሉ!›› ብለው ወደ ኩሽና አመሩ፡፡ መምሬ እውነቱ “ደኅና እንዳልሽ! ይዤአቸው እመጣለው ..›› አሉ፡፡
ግርማዬ የተሸከመውን ዱቄት አውርዶ ልብሱን እያራገፈ ወደ መምሬ እውነቱ መጣ ጎንበስ ብሎ ጉልበታቸውን ሳመ፤ መስቀል ተሳልሞ ከሥራቸው ቁጭ አለ፤ ወደ ከላይ አሻቦ እያያቸው “አያቴ ትምህርት እንዲሆነኝ የማታውን ታሪክ እንግዶቹ እስኪመጡ አይነግሩኝም” አለ፡፡ ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ መምሬ እውነቱ ቁልቁል እየተመለከቱ “ልጄ አብዛኛውን ታሪክ ሰምተኸዋል፤ ለአንተ መማሪያንት እኮ የአያትህ የክብሬ ታሪክ ትልቀ ምሳሌህ ይሆናል፡፡ የልጅነቷ ታሪክ የወላጆቿን የልጅ አስተዳደግ ነግራህ የለ! አሉ፡፡ ግን ደግሞ ማታ የጀመርኩልህ ታሪክ አንተ ወደፊት ለመሆን ያሰብከውን መልካም ሕይወት መሠረት የሚጣለው አሁን ከልጅነትህ በመሆኑ ለትምህርት ያህል ካቆምኩባት ላውጋህ” ..አሉና ለአፍተ ዝም ብለው ተመስጠው ቆዩ፡፡
ግርማዬ አሻቅቦ እያያቸው ከአንደበታቸውን የሚወጣውን ለማድመጥ ይጠባበቅ ጀመር፤ “እናም” አሉ መምሬ እውነቱ ..ቁልቁል ግርማዬን እየተመለከቱ “ልጅ የወላጁን ምክር ካልሰማ፣ ወላጅ ልጆችን በአግባቡ ካልቀጣ መጨረሻ ጉዳቱ ለሁሉ ነው! በእርግጥ አባቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያሟሉለት ነበር፡፡ ግን ደግሞ ለልጅ ቁስን ሟሟላት፣ የሚበላውን፣ የሚጠጣውን መስጠት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ምግባርን ማስተማር ለልጆች ጊዜ መድቦ አብሮ መዋል የ”ት ገቡ? ምን ሲሠሩ ዋሉ? ወዴት ነው የሚሄዱት? ከነማን ጋር ነው የሚውሉት?” በማለት በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ወሳኙ እርሱ ነውና!” አሉ፡፡
አሁንም ሩቅ ማሰብ ጀመሩ! እርሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ወ/ሮ ምዕረግነሽ የልጅ ልጃቸውን ግርማዬን ለማሳደግ ያደረጉትን ውጣ ውረድ አስታወሱ “ልጅን ማሳደግ ቀላል አይደለም! በጣም ከባድ ነው! በእርግጥ መምሬ እውነቱም ሆነ ወ/ሮ ማዕረግነሽ ልጅ የማሳደግ ሥርዓቱን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ከግርማዬ በፊት የራሳቸውን ልጆች በሥርዓት አሳድገው ለቁም ነገር ያበቁ ናቸው፡፡ ግርማዬ ግን የአደራ ልጅ ከመሆኑም በተጓዳኝ የአያትነትን ማዕረግ ያዩበት ስለ ነበር መክፈል የሚገባቸውን መሥዋዕትነት ከፍለው በሥርዓት አሳድገውታል፡፡ እርሱም በአያቶቹ እጅ በማደጉ በዕድለኛነቱ ሁል ጊዜ ይኮራል!
እናም “ልጄ ከክፉ ባልንጀራ ጋር ገጥሞ በትምህርቱ መቀጠል ተሣነው፡፡ ዐሥረኛ ክፍል ሲደርስ አቆመ፤ አባቱ የቅርብ የሚላቸውን ዘመዶቹን ጠይቆ በመኪና ገራጅ ውስጥ ሥራ አስቀጠረው፤ ግን ምን ዋጋ አለው! ቀድሞ በሱስ ተጠምዶ ስለ ነበር በሚያገኘው ገንዘብ ይጠጣበትና ያጨስበት ጀመር፡፡ ገንዘብ ያጣም ጊዜ ወደ ስርቆት ገባ፡፡ በዚህ አመሉም ከሥራው ተባረረ፡፡ አንድ ጊዜ በሱሱ ተጠምዷልና የቤተሰቦቹን እቃና የዘመዶቹን ንብረት መስረቅ ጀመረ፡፡ አባቱ በጣም ተጨነቀ፡፡ ቀድሞ ያላሳሰበው የልጁ ጉዳይ መከራው ለእርሱም ሲተርፍ ተጨነቀ ! አበው በብሒላቸው “ራስን መቻል ሌላውን መርዳት ነው” ይላሉ፡፡ ልጆች በሥርዓት አድገው ለቁም ነገር ሲበቁ የወላጅን ስም በመልካም ሲያስጠሩ ያኔ ጥቅሙ ለራስም ጭምረ ነው! እናም ልጄ በጥፋቱ ተከሶ ከማረሚያ ቤት ገባ ከዚያም የእርምት ጊዜውን ጨርሶ ወጣ፡፡ ግን ከጥፋ ባለመመለሱ በሱሰኝነት በመጠመዱ በመጨረሻ ለአእምሮ ጭንቀት ተዳርጎ ከሱሰኝነት ማገገሚያ የሕክምና ቦታ ገባ፡፡ እንግዲህ በዚያ ቆይታው መጠነኛ ለውጥ እያመጣ ነው !” አሉና አሁንም ከቁዘማቸው ገቡ፡፡
በውስጣቸው “ለዚህ ልጅ ሕይወት መስመር መሳት እውን ወላጅ ብቻ ተጠያቂ ነውን አሉ! በውስጣቸው ሐሳብ ፈልቆ ይሟገታቸው ጀመር፡፡ “የለም የለም! ወላጅ ብቻ አይደለም፡፡ ጎረቤትም ልጆች ሲያጠፉ ከቻለ መምከር አልያም ለወላጅ በጊዜ ማሳወቅ ይገባቸዋል! መምህራንም እንዲሁ ተማሪዎች የጠባይ ለውጥ ሲታይባቸው፣ በትምህርታቸው ደከም ሲሉ በጊዜው መምከር አልያም ለወላጅ ማሳወቅ ነበረባቸው!” አሉ፡፡ እናትና አባት ይውለዱ እንጂi ልጆች ሲያድጉ ለቁም ነገር ሲበቁ የሚያገለግሉት ማኅበረሰቡን እንደመሆኑ ሁሉም የድረሻን ሊወጣ ይገባል! ውስጣቸው ሐሳብ እያፈለቀ ተሟገተባቸው፡፡ ግርማዬ የአያቱን ዝምታ ለመስበር “አያቴ ቃለ ሕይወት ያሰማልን! እንግዶቹም መጥተዋል” አለ! መምሬ እውነቱ ከሰመመናቸው ነቅተው ከተቀመጡበት በመነሣት “መጣችሁ! በሉ እናዝግም” አሉ፡፡ ግረማዬን እና ወ/ሮ ማዕረግ ነሽን ተሰናብተው ከሰዎቹ ጋር ተያይዘው ወደ ሆስፒታል አመሩ፡፡ እንደ ደረሱ ከክፍል ክፍል እየተዘዋወሩ “ፈጣሪ ይማራችሁ፤ ለአስተማሚዎችም ጽናቱን ትዕግሥቱን ያድላችሁ!” በማለት መልካም ምኞታቸውን እየገለጡ ለጥየቃ ከያዙት ስጦታ ለገሡ፡፡
በመጨረሻ ድብርቱ በተወሰነ መልኩ የለቀቃቸው፣ ጭንቀት የቀለለላቸው ካሉበት ክፍል የምክር አገልግሎት ሰጪው የሕክምና ባለሞያ እየመራቸው ገቡ፡፡ መምሬ እውነቱ አባታዊ ምክራቸውን ይለግሡ ለታማሚዎች ጸሎት ያደርጉ ዘንድ ተጋበዙ! ሰላምታ ሰጥተው ምክራቸውን ጀመሩ! “መቼም ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ሁላችንም ነን፤ ካህኑ ኤሊ ልጆቹን አፍኒንና ፊንሃስን በአግባቡ ባለመምከሩ ባለመቅጣቱ ጉዳቱ ከእነርሱ አልፎ ለቤተሰባቸው አልፎም ለአገር ተረፈ፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች አገር ተረክበው ቁም ነገር በሚሠሩበት ጊዜያቸው በአጉል ሱስ ተጠምደው ለበሽታ ተዳረጉ!” አሉ፡፡ ወደ ታማሚ ወጣቶች እየተመለከቱ “ልጆቼ አባቶቻችንን ከትላንት በንዘገይም ከነርሱ እንቀድማለን›› ይላሉ፡፡ ከትናንት ዘግይታችኋል፤ ነገን ግን መቅደም ትችላላችሁ! ያለፈው ጉዟችሁ ከጨለማው ሕይወት ከቷችኋል፤ ስለዚህ ከዚህ ተምራችሁ ያለፈውን ጥፋት ላለመድገም ጣሩ በእርግጥ በአንድ ጊዜ ከዚህ ሱስ ፣ከዚህ ድብርትና ጭንቀት አልገባችሁም! በአንድ ጊዜም ልርሳው ብትሉ በሥጋዊ አስተሳሰብ ይከብዳል ! በእምነትና በተስፋ ከሆነ ግን በጸሎት፣ በጾም፣ በጸበል በመጠመቅ ልታርቁት ይቻላችኋል:: ..ጌታችን ‹‹ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” (እንዳለን በሱስ ተጠምዳችሁ የገጠማችሁን ደዌ በእምነት ማራቅ ትችላላችሁ:: ያላችሁበት ሁኔታን የሚፈልገው ማንም የለም! ስለዚህ ቁረጡ! ወስኑ ሁሉን በሚያስችል አምላክ ሁሉን ትችላላችሁ!
ቅድስት አትናስያ የተባለች ሴት ከመልካም ሕይወት ወጥታ በማይገባ ሕይወት ውስጥ ነበረች፡፡ በኋላም ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር የዚህች ሴት ሕይወት አሳስቦት ካለችበት የኃጢአት ሥፍራ ድረስ ሄዶ መንገዷን እንድታስተካክል መከሯት፤ እርሳም የጊዜ ቀጠሮ አልሰጠችም፤ ተከትላው ምሕረትን ፍለጋ ተጓዘች፤ በመንገድም ሳለች ከድካሟ የተነሣ ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች (ዐረፈች)፡። ቅዱስ ዮሐንስ አጺርም በጣም አዘነ! በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር “አትዘን” አለው፡፡ “አንተን ተከትላ ከቤቷ ስትወጣ አንድ እግሯ ደጇን በረገጠ ጊዜ ምሬአታለው” አለው! አያችሁ የፈጣሪን ምሕረት! እኛ ከዚህ ለመውጠት ከቆረጥን ምሕረቱ ቅርብ ነውና ሊታደገን ፈጣን ነው! እናም ፍጠኑ የመዳን ቀን አሁን ነው!
መምሬ እውነቱ ለአስታማሚ ቤተሰቦችና ለታማሚዎች የሚሆኑ ምክሮችን በሚገባ አስተለለፉ! “እከሌ እንዲህ አደረገ! እከሌ እንዲህ ነው!” ከማለት ይልቅ “ለዚህ ጥፋት የእኔም አስተዋጽኦ አለበት” በማለት ብዙዎች ወደ ራሳቸው እንዲመለከቱ አደረጉ !ጸሎት አድርገውላቸውና መልካም ምኞታቸውን ገልጠው ወደ ቀያቸው አመሩ፡፡
ወስበሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!