‹‹ተዝካረ ዕረፍቱ ለቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ››
ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ግንቦት ፲፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ዐሥራ ሁለተኛው የቊስጥንጥንያ መንበር የነበረ፣ ከአራቱ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያን ዐቃቢያነ እምነት ከሆኑት ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያና ከቅዱስ ባስልዮስ ጋር በግብር የተካከለ፣ በገዳማዊ ሕይወቱ ብሕትው፣ በንጽሕናው ተአማኒ፣ በአእምሮ ምጡቅ፣ በአንደበቱ ርቱዕ፣ በስብከቱ መገሥጽ፣ በፍርዱ ፈታሒ በጽድቅ፣ በመግቦቱ አበ ምንዱባን (የድኆች አባት) በጥብቅናው ድምፀ ግፉዓን፣ በጥቡዕነቱ መገሥጽ፣ በክህነቱ የቤተ ክርስቲያን መዓዛ፣ የዓለም ሁሉ መምህር የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕረፍቱ መታሰቢያ በግንቦት ፲፪ ቀን ሆነ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአንጾኪያ ከተማ ከአባቱ ከአስፋኒዶስ ከእናቱ ከአትናስያ (አንቱሳ) ተወለደ። ምንም እንኳን አባቱ ገና እንደ ተወለደ በሕፃንነቱ በሞት ቢለየውም እናቱ አንቱሳ እንደ እናትም እንደ አባትም ሆና በጥሩ ሥነ ምግባር አሳደገችው። የአንጾኪያ ሰዎች በአሕዛባዊ ግብርና ፍልስፍና በተበከለችና ሰዎች በአሕዛባዊነትና በክርስቲያንነት መካከል በሚወላወሉባት ከተማ አንቱሳ ልጇን በምግብሩ የቀና በሃይማኖቱ የጸና ለማድረግ ሕይወቷን በሙሉ መሥዋዕት አድርጋ ዳግመኛ ሳታገባ የልጇን የወደ ፊት ትልቅነት እየተመለከተች አሳደገችው።
ቅዱስ ዮሐንስ በእናቱ ብርቱ ጥረት የመንፈሳዊነት መርሖችን፣ ግብረ ገብነትን ከእናቱ እየተማረ ያደገ ሲሆን የግሪክ ጥንታዊ ትምህርቶችን ስመ ጥር በሆኑ የግሪክ ትምህርት ቤቶች ተማረ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሥነ ንግግር ጥበብን ከሊባንዮስ፣ ፍልስፍናን ከአንድራጋትዮስ ተምሯል። በንግግር ክህሎቱም እጅግ የታወቀ የረቀቀ አንደበተ ርቱዕ ሆነ። ምንም እንኳን እናቱ የክርስትና ትምህርትን ብታስተምረውም ጥምቀተ ክርስትና ስላልተፈጸመለት ግን ሙሉ ሰው አልነበረም። የሕግ ትምህርትን የተማረና ጠበቃ ቢሆንም የሥራ ባልደረቦቹ ድኃ ሲበድሉ፣ ፍርድ ሲያጓድሉና ወንጀለኛውን ሲያጸድቁ መመልከቱ የዘወትር ሕመሙ ሆነ። በዚህም ይህን ሥራውን እየጠላው መጣ።
በመጨረሻም ነፍስን አጠጥቶ የሚያረካ የሕይወት ምንጭ ወደ ሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተመለሰ። የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከመላጥዮስ ሦስት ዓመት ተምሮ በሊቀ ጳጳሱ እጅ በዕለተ ፋሲካ በ፳፫ ዓመቱ ተጠመቀ።የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ጰላድዮስ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተጠመቀ በኋላ ስላለው ሕይወት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል። “ዮሐንስ ከተጠመቀበት ሰዓት ጀምሮ መማልን፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ክፉ መነጋገርን ወይም ሐሰት መናገርን፣ ወይም መሳደብን ወይም የፌዝ ንግግርን መታገስን አቆመ።” በሕይወቱም ፍቅረ እግዚአብሔርና ቅናተ ቤተ ክርስቲያን በውስጡ ይቀጣጠል ጀመር። ከዚህም በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በላዩ ላይ ወርዶ አደረበትና ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ። ዲያቆን ሆኖ ሳለም የቤተ ክርስቲያንን መጽሐፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ተረጎመ።
ዮሐንስ ገና በታናሽነት ዕድሜው መንኩሶ የዚህን ኃላፊ ዓለም ጣዕም ንቆ መኖር ጀመረ። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል›› በማለት እንደ ተናገር ዮሐንስም የዚችን ዓለም ጣዕም ናቀ። (፩ኛዮሐ.፪፥፲፭) የከበረ የባለጸጋ ልጅ ቢሆንም ሃብቱ አላሳሳውም። ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም፤ ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ እንጅ ከዚያም በምንኵስና ሥራ በመጠመድ ፍጹም ገድልን እየተጋደለ ኖረ።
የፍልስፍና ትምህርትን ከአንድራጋቶስ የንግግር ጥበብን ከሊባንዮስ አብሮት ከተማረው ጓደኛው ከታላቁ ባስልዮስ ጋር አብረው እውነተኛውን ሕይወትና ፍልስፍና መኖር ጀመሩ። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ›› በማለት እንደ ገለጸው። (መዝ.፲፰፥፳፭-፳፮) የሁለቱ የጓደኝነት ሕይወትም በንጽሕና ያሸበረቀ እንደ ዕንቁ የሚያበራ እንደ ወርቅ የጠራ ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ጓደኛው ቅዱስ ባስልዮስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ ‹‹እርሱ ከክብር ወደ ክብር ከቅድስና ወደ ቅድስና ከፍ እያለ ሄደ፡፡›› በዚህም ለክህነት ሲታጩ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹እኔ ለክህነት የበቃሁ አይደለሁም፤ ወንድሜ ግን ክህነት ይገባዋል›› በማለት አብረው ከጸናበት አቋሙ ከቅዱስ ባስልዮስ ጋር ለጊዜው ቢስማሙም በኋላ ግን ቅዱስ ባስልዮስ ለጊዜው አሠረ ክህነትን ሊቀበል እንደ ቀረ በእንተ ክህነተ የተሰኘው መጽሐፉ ይነግረናል።
ክህነት ምን ያህል የከበረ እንደሆነም በቅዳሴው ‹‹ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር በልዕልና የሚቀመጥ እርሱ በዚያች ሰዓት በሁሉም ካህናት እጅ ይያዛል፤ ሊቀበሉትና ሊዋሐዱት ለሚፈልጉትም ለሁሉም ራሱን ይሰጣል። ወዮ የእግዚአብሔር ቸርነት ምን ይደንቅ? ምን ይረቅ? መጠንና ልክ የሌለውን እሳት በእጁ የሚይዝ ካህን!›› በማለት የክህነትን ታላቅነት አሳይቷል፡፡ ለወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ በላከው መልእክቱ ደግሞ ‹‹ክርስቶስ እንደሚፈልገው አድርጌ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት የበቃሁ ሆኜ ሳለሁ እምቢ ብዬ ሸሽቼ ቢሆን ኖሮ አነጋገሬ ሰዎችን ሊያጠራጥራቸው በቻለም ነበር። ነገር ግን የመንፈሴ ደካማነት ለዚህ አገልግሎት የማልጠቅም ስለሚያደርገኝ ንግግሬ ለምን በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል? መንጋው በደኅናና በጥሩ ምግብና ላይ ሳለ የጥበቃውን ኃላፊነት ብወስድና ከዚያ በኋላ ግን በእኔ አላዋቂነትና ጥበብ የለሽነት ምክንያት ባጠፋቸው እነርሱን ለማዳንና ለመቤዠት ሲል ራሱን የሰጠላቸውን እግዚአብሔርን በራሴ ላይ አነሳሳዋለሁ ብዬ እፈራለሁና›› ሲል ተናግሯል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከክህነት ሸሽቶ መኖር ቢፈልግም ወደ ክህነት መምጣቱ አልቀረም። በአንዲት ሌሊትም ሲጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ እንደ በረድ ነጭ በሆነ ልብስ ተገለጠለት፤ ቅዱስ ዮሐንስም ሲያየው ደንግጦ በምድር ላይ ወደቀ፤ መልአኩም አርአያውን ለውጦ እንደ ሰው ሆኖ ታየው፤ ‹‹ወዳጄ አዲስ ዳንኤል ሆይ፤ አትፍራ፤ ተነሣ›› አለው። መልአኩ አዲስ ዳንኤል ብሎ የተጠራበት ምክንያት የናቡከደነፆር ራእይ ንባቡ ከነትርጓሜው ከጠፋ በኋላ ንባቡ ከነትርጓሜው በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት እንደተናገረ እርሱም ራእየ ዮሐንስን ንባቡ ከነትርጓሜው ከጠፋ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት ተርጉሞታልና። ዳግመኛም ዳንኤል ጸዋሚ ተሐራሚ እንደሆነ ሁሉ እርሱም ጸዋሚ ተሐራሚ በመሆኑ ዳንኤል ሐዲስ ብሎታል።
የቅዱስ ዮሐንስም ልቡናው ተጽናንቶ ‹‹ጌታዬ አንተ ማን ነህ? ግርማህ አስፈርቶኛልና›› አለው የእግዚአብሔር መልአክም ‹‹ትሠራው ዘንድ የሚገባህን ልነግርህ ወደ አንተ የተላኩ ነኝ›› አለው። ‹‹አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘህን ለመሥራት ልብህን አበርታ፤ ቃልህ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአራቱ ማእዘን ይደርሳልና። እልፍ አእላፍትም ትምህርትህን ተቀብለው ትእዛዝህን ሰምተው ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ተመልሰው ይድናሉና። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የጸና የብርሃን ዓምድ ትሆናለህ። እነሆ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ ወደ አንተ ይመጣል፤ የሚያዝዝህንም አድርግ፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነውና ልትተላለፍ አይገባህም›› አለው፡፡ ከዚያም በኋላ ያ መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው። በማግሥቱም ሊቀ ጳጳሳቱ መጣ ከእርሱ ጋራም ካህናት አሉ ቅዱስ ዮሐንስንም ይዞ ቅስና ሾመው።
የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ባረፈ ጊዜ ንጉሥ አርቃዲዮስ ልኮ አስመጥቶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በቊስጥንጥንያ ላይ ሊቀ ጵጵስና እንዲሾም አደረገው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደ አባቶቹ በጵጵስናው ሥራ ጸና፤ ሕይወትነት ባላቸው ትምህርቶችና ተግሣጾች ሕዝቡን ሁልጊዜ የሚያስተምር ሆነ። ማንንም ሳይፈራ ሕግ ተላላፊዎችን ከቤተ መንግሥትም ከቤተ ክህነት ወገንም ይገሥፃቸው ጀመር። በዚህም ፊት አይቶ የማያዳላ መምህና መገሥፅ በመባል የሚታወቅ ሆነ። አንድ ቀን የንጉሥ አርቃዲዮስ ሚስት አውዶክስያ የአንዲት ድኃ መበለት ቦታዋን በግፍ ወሰደች፤ ያች መበለትም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጥታ ንግሥቲቱ ቦታዋን እንደ ነጠቀቻት ነገረችው። እርሱም ‹‹የድኃዋን ቦታ መልሽላት›› ብሎ ከብዙ ምክር ጋር እንድትመልስላት ንግሥቲቱን ለመናት፤ እርሷ ግን እንቢ አለች። ቅዱስ ዮሐንስም ስለ አንዲት መበለት ንግሥቲቱን ሳያፍርና ሳይፈራ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበል አውግዞ ለያት። ንግሥቲቱም እርሱ ከሹመት የሚሻርበትን ነገር መሥራት ጀመረች፤ ስለ ክፉ ሥራቸው ከሹመታቸው እርሱ የሻራቸውን ኤጲስቆጶሳት ሰበሰበች፤ እነርሱም ንግሥቲቱን ስለተቃወመ ስደት እንደሚገባው ተስማምተው ጻፉ፤ እርሷም አጥራክያ ወደ ሚባል ደሴት ሰደደችው።
የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስደት በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ በንጉሥ አርቃድዮስ ላይም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ፤ ‹‹ከዚህ ከክፉ ሥራ ተጠበቅ፤ ትእዛዛችንንም ተቀብለህ የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ ካልመለስከው በአንተና በእኛ መካከል ሰላም አይኖርም።›› መልእክታቸውንም ባነበበ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ሚስቱንም አግዶ ልኮ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ከስደቱ መለሰው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ንግሥቲቱ ወደ ክፋቷ ተመልሳ ሁለተኛ ወደ አጥራክያ ደሴት ሰደደችውና በዚያው ዐረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
ምንጭ፡-ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት ፲፪፤ ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (የታሪክ አምድ)፤በእንተ ክህነት በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ኪዴ እንደተረጎመው፤ ጽዋኤ በዲያቆን ታደሰ ወርቁ፤የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ