ተዋሕዶ የአይፎን አፕሊኬሽን ተሻሽሎ አገልገሎት መስጠት ጀመረ::
አፕሊኬሽኑ ለሁሉም የአፕል ስልኮችና አይፓዶች በሚኾን መልኩ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡
ትምህርቶችን፣ ጸሎታትን፣ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን፣ የየዕለቱን ምንባባትና የአብያተ ክርስቲያናት መረጃዎችን ይዟል፡፡
ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በእጅ ስልክ አማካይነት ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ስብከቶችን፣ መዝሙራትንና ጸሎታትን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችለው ተዋሕዶ የአይፎን አፕሊኬሽን ተሻሽሎ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጠ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል ሙያ አገልግሎትና ዐቅም ግንባታ ክፍል ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ እንደገለጠው፤ በማእከሉ ታቅፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሞያቸው በሚያገለግሉ አባላት ቀደም ሲል የተዘጋጀው አፕሊኬሽኑ ለምእመናን ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ከተጠቃሚዎች በተሰጡ አስተያየቶችና በባለሞያዎቹ ምክርና ጥረት ለሁሉም የዓፕል ስልኮችና አይፓዶች በሚኾን መልኩ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡ በአዲስ መልክ የተሸሻለው ይህ አፕሊኬሽን ከበርካታ ትምህርቶች፣ ጸሎታት፣ መዝሙራት፣ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያን ካላንደር (በዓላትና አጽዋማት ማውጫ)፣ በየዕለቱ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትን እንዲሁም በአሜሪካ፣ በካናዳና አውሮፓ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን አድራሻና መሠረታዊ መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡
በተጨማሪም አፕሊኬሽኑ ልዩ ልዩ ዓመታዊ በዓላትÂ እና አጽዋማት ሲደርሱ ለተጠቃሚዎቹ ማስታወሻ እንዲልክ ኾኖ ተዘጋጅቷል፡፡ የማእከሉ ሙያና ዐቅም ማጎልበቻ ክፍል ምእመናን ይህንን አፕሊኬሽን እዚህ ላይ በመጫን እንዲገለገሉ፣ ላልሰሙትም እንዲያሰሙ ሲል ያበስራል፡፡