ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የኖላዊነት ተልእኮው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰባክያነ ወንጌል፤ በተለይ ምእመናንን በቅርበት የመከታተል ሓላፊነት ያለባቸው የእግዚአብሔር እንደራሴዎች፣ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃዎች የኾኑ ካህናት የነፍስ ልጆቻቸውን ተግተው በማስተማር የኖላዊነት ተልእኮአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አሳሰቡ፡፡
ብፁዕነታቸው ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በ፳፻፱ ዓ.ም ርክበ ካህናት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን መሠረት በማድረግ በተለይ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴዎችን፣ ዐቂበ ምእመናንን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎትና የልማት ሥራዎችን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹ቅዱስ ሲኖዶስን የሚመራውና ሥራውን የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ሰው ምክንያት ነው›› ያሉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመጨረሻው ወሳኝ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ ለምእመናን ሕይወት የሚጠቅሙ መመርያዎችን በየጊዜው ሲያወጣ እና ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ አክብሮ መቀበል ክርስቲያናዊ ግዴታ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ መመርያዎቹና ውሳኔዎቹ በተግባር ላይ እንዲውሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ተወግዘው ከተለዩ መናፍቃን በተጨማሪ በብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከት ደቡብ ምዕራብ ሸዋም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ የኾኑ ትምህርቶችንና መዝሙሮችንም በስውር ሲያስተምሩ፤ ሲዘምሩ የነበሩ ዘጠኝ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችን አውግዘው መለየታቸውን ብፁዕነታቸው አውስተው፣ በሦስት መንገዶች ማለትም አውግዞ በመለየት፤ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማገድ እና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሀገረ ስብከታቸው በመናፍቃኑ ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡
የኑፋቄ ትምህርት እንደሚሰጡ ሕጋዊ ማስረጃ ቀርቦባቸው ከአሁን በፊትም ኾነ በዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የተለዩ መናፍቃን ጥፋታቸውን አምነው፣ ስሕተታቸውን አርመው በንስሐ ለመመለስ ዝግጁ ከኾኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በይቅርታ እንደምትቀበላቸው፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በመተላለፍ ምእመናንን ማሰናከላቸውን ከቀጠሉ ግን በሕግ እንደምትጠይቃቸው አስረድተዋል፡፡
ሐዋርያዊ ተልእኮን በሚመለከትም ማኅበረ ቅዱሳን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በማዘጋጀት በአማርኛ ቋንቋ እና አፋን ኦሮሞ ትምህርተ ወንጌል ከመስጠቱ ባሻገር ምእመናንን በማስተባበር ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ ድጋፍ በማድረጉ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን መደሰታቸውን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ይበልጥ ለማፋጠን ይቻል ዘንድ ማኅበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትንና መንፈሳውያን መዝሙራትን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በማሠራጨት አገልግሎቱን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡
የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በስፋት ማዳረስ፣ የአብነት ት/ቤቶችን ማስፋፋት፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እና ገቢ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶችን መተግበር ወደፊት ሊከናወኑ የታቃዱ ተግባራት መኾናቸውን ያስታወቁት ብፁዕነታቸው፣ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ለመደገፍ ሲባል በወሊሶ ከተማ ለሚገነባው ባለ አራት ፎቅ ዅለገብ ሕንጻ ግንባታም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርግ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ‹‹ዘመኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና የበዛበት፤ ከውስጥም ከውጪም ጠላቶች የበረከቱበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ትክክለኛ ሰባኪ እና የቤተ ክርስቲያን ልጅ መስለው በቅዱሳን ስም የሚሰበሰበውን ገንዘቧን እየበሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እየጎዱ ያሉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንም እየበዙ ነው፡፡ ስለኾነም ሰባክያነ ወንጌል፣ ቀሳውስት እና ዲያቆናት፣ እንደዚሁም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ምእመናኑን በሥርዓት ሊያስተምሩ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ከኑፋቄ ትምህርት አራማጆች ሊጠነቀቅ፤ በቃለ እግዚአብሔር በመጎልበትም ራሱን ከስሕተት ሊጠብቅ ይገባል›› በማለት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡