ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ መናፍቃንን አወገዙ
ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ በአህጉረ ስብከታቸው የተሐድሶ ኑፋቄን ሲያስተምሩ የተገኙ መናፍቃንን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ለዩ፡፡
ተወግዘው የተለዩት ግለሰቦች ‹ምስሉ ፈረደ›፣ ‹ፍጥረቱ አሸናፊ›፣ ‹ያሬድ ተፈራ›፣ ‹በኃይሉ ሰፊው› እና ‹እኩለ ሌሊት አሸብር› እንደሚባሉ፤ ከእነርሱ መካከልም ምስሉ ፈረደ እና ፍጥረቱ አሸናፊ መዓርገ ቅስና፤ ያሬድ ተፈራ እና እና በኃይሉ ሰፊው መዓርገ ዲቁና እንደ ነበራቸውና ሥልጣነ ክህነታቸው እንደ ተያዘ፤ የሰንበት ት/ቤት አገልጋይ የነበረውን እኩለ ሌሊት አሸብርን ጨምሮ ከዚህ በኋላ ዅሉም ግለሰቦች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት እንደ ተለዩና ‹አቶ› ተብለው እንደሚጠሩ ብፁዕነታቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ለማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ግለሰቦቹ ተወግዘው እንዲለዩ የተደረገው የኑፋቄ ትምህርት በማስተማር ሕዝበ ክርስቲያኑን ሲያደናግሩ ከመቆየታቸው ባሻገር ራሳቸውን ‹ተሐድሶ› ብለው በመሰየም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር የሚቃረን ትምህርት ሲሰጡ በማስረጃ በመረጋገጡ ነው፡፡
በመጨረሻም እግዚአብሔር አምላክ የሰዉን ልጅ ድኅነት እንጂ ጥፋቱን የማይፈቅድ መኾኑን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው ለብዙኃኑ ድኅነት ሲባል ጥቂቶችን አውግዞ መለየት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም የግለሰቦቹን ቃለ ውግዘት ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚያቀርቡ በመጥቀስ ተወግዘው የተለዩትም ይኹን በማስጠንቀቂያ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ከስሕተታቸው ተመልሰው ንስሐ ቢገቡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደምትቀበላቸው አሳስበዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በቍጥር 148/11/2010፣ በቀን 01/03/2010 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ በተሐድሶ ኑፋቄ ውስጥ ኾነው ሕዝበ ክርስቲያኑን እያደናገሩ የሚገኙ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትንና ምእመናንን በአጠቃላይ የዐሥራ ሦስት ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ከክህነት አገልግሎት፤ ምእመናኑ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አባልነት መታገዳቸውን ያሳወቀ ሲኾን፣ በደብዳቤው ከተጠቀሱ ግለሰቦች መካከልም ምስሉ ፈረደ እና ፍጥረቱ አሸናፊ ይገኙበታል፡፡
በተያያዘ ዜና የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በቀን 22/03/2010 ዓ.ም ለ15ቱም የሀገረ ስብከቱ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በላከው ደብዳቤ መ/ር አዲስ ይርጋለም፣ ቀሲስ ካሡ ተካ፣ መ/ር ዓይነኵሉ ዓለሙ፣ መ/ር ኢሳይያስ ጌታቸው እና መ/ር ጎርፉ ባሩዳ የተባሉ አምስት አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም ኾነ በሌላ ቦታ ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳይሰጡ አግዷቸዋል፡፡