‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ›› (ዮሐ. ፲፬፥፲፭)
አምላካችን እግዚአብሔርንን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው በበጎ ተግባር እና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ከታነጽን ነው። እርሱን ስንወድ ፈቃዱን እና ትእዛዛቱን እንፈጽማለን። ትምህርተ ወንጌልን ከሕፃንነታችን ከተማርንበት ጊዜ ጀምሮ የእርሱ ፍጥረት መሆናችን አውቀንና ወደን ማገልገል እንዳለብንም እንረዳለን። እግዚአብሔርን መውድድ እና በትእዛዛቱ መኖር የተፈጠርንበት ምክንያት ነውና።
አምላክነቱን አውቀን ግን ኃጢአትን በመምረጥ ሕጉንና ትእዛዙን ብንጥስ ፈቃዱን ትተን የእኛን ፈቃድ ፈጽመፈልና እግዚአብሔርን በተግባራችን ‹‹አንወድህም›› እያልነው እንደሆነ ማወቅ አለብን። እግዚአብሔርን መውደድ ከሁሉም በፊት እርሱን ማስቀደም፣ በእያንዳንዱ ሐሳባችን እና ውሳኔያችንም እርሱ እንዲጨመርልን መፍቀድ ነው፡፡ በመንገዱ እንድንጓዝም አምላክነቱን ወደን መቀበል አለብን፡፡
ሰው አምላኩ እግዚአብሔርን ከወደደ ሁለተናውን ለእርሱ ይሰጣል፤ ከኃጢአት የነጻ ሆኖ ልበ ንጽሕ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ከፈጣሪያችን ስለምንረቅ ለሌላ ባዕድ ነገር ተገዢ እንሆናለን፡፡ ክርስቶስን በሙሉ ልባችን፤፣ ነፍሳችን፣ ኃይላችን ከወደድነው ግን ፍቅሩን ተረድተን ሁለመናችን ለእርሱ እንሰጣለን፤ እርሱም ደግሞ ከእኛ ጋር ይሆናል።
‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች በፈተና እንደሚወድቁ ያውቃል፤ ሆኖም ቸር በመሆኑ ይቅር ይለናል›› የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሊያጋጥሙን ይችላል። እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ መሆኑን አንጠራጠርም፤ ነገር ግን የምንወደው ከሆን እርሱን ማሳዘን የለብንም፤ ከኃጢአት ስንርቅ ከእርሱ ጋራ በሰላም መኖር እንችላለን፤ በዚህኛውም ሆነ በኋላኛ ዓለም በፍቅርና በሰላም እንኖራለን። የፈጣሪያችንን ምሕረት እና ይቅርታውን እየተማጸንን በመኖር ኃጢአትን ከሕይወታችን ማስወገድ እንችላለን፤ በክርስቶስ ክርስቲያን ሆነን ከእርሱ ጋርም በአንድነት እንኑር።
ጌታችን ኢየሱስን መውደድ በምድር እያለን እንጂ ከሕልፈታችን በኋላ አይደለም፡፡ በእውነት መንገዱ በመጓዝ፣ ክርስቶስ እኛን እንዳፈቀረንና እንደሚያፈቅረን ሁሉ እኛም እርሱን ልናፈቅረው ይገባል፡፡ ትእዛዛቱም እንደሚሉት ባልንጀራዎቻችንን እንደራሳችን ስንወድ እርሱን እንደወደድን ይሆናል። ጌታችን ስለእኛ በምድር ሥቃይና መከራን የተቀበለልን በፍቅሩ ሳቢያ ነው፤ ፍቅር በክርስቶስ ዘንድ ምን ያህል ክቡር መሆኑን ተገንዝበን እኛም ለፍቅር ተገዝተን እንኑር።
አእምሮአችንንና ልባችንን በክርስቶስ ፍቅር ካስገዛን ለሰዎች እና ለነገሮች በጎ እይታ ስለሚኖረን ቅዱሳንም በእርሱ አንደበት እንደተናገሩት እኛም እንዲሁ ማድረግ እንችላለን። እግዚአብሔር አብንና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለመውደድ ጌታችን ክርስቶስን ከልብ መውደድና በሕጉም መመራት ያስፈልጋል።
‹‹ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?›› እንደተባለው ለእግዚአብሔር የሚኖረን ፍቅርና ኃጢአት በልባችን ውስጥ በአንድ ላይ መኖር አይችሉም፤ ለሁለት ጌቶች ልንገዛ አንችልም፤ ምክንያቱም አንድ አምላክ እግዚአብሔርን አለማመን እንዲሁም ለሰይጣን መገዛትን ስለሚያስከተል ለጥፋታትም ይዳርጋል። ክርስቶስን የሚወድ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው የሚችለውን ነገር ሁሉ መተው ይኖርበታል። እርሱን መውደዳችን በጎ አስተሳሰባችንና የኑሮ ዘይቤያችንን መልካም ያደርገዋል። (፪ቆሮ. ፮፥፲፬)
ጌታችን ክርስቶስን የመውደዳችን መጠን ወንጌልን የማወቅ እና ትእዛዙን የመፈጸማችን ልኬት ነው። እርሱ ራሱ በፈቀደው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በኩል እንደሚመራን አድርገን መኖር ያስፈልገናል። ለሐዋርያቱ ‹‹እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል›› እንዳላቸው ሁሉ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን የሚሰማ እርሱን መስማት መሆኑን ሳናመነታ ይህንን ከፈጸምን ክርስቶስን እንወደዋለን ማለት ነው። (ሉቃ. ፲፥፲፮)
ነገር ግን ኃጢአት በሥጋችን ላይ ከነገሠ ጌታችን ኢየሱስ አይመራንም፤ ለጥፋታችንም የምንጠየቀው እኛው ነን፤ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚሆን ነገር ሁሉ አዘጋጅቶ ነውና የፈጠረልን ዛሬ በመንፈሳዊ ዓይናችን እግዚአብሔርን እያየንና እየታዘዝን ከተጓዝን በጊዜያዊና ሥጋዊ ኑሯችን የጀመርነውን ደስታ ነገ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም እንቀጥለዋለን።
ጌታችን ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚወደን የምናውቀው በመስቀል ላይ ስለተሰቀለልንና ሕይወቱን ስለኛ ያሳለፈበትን መሥዋዕት በመመልከት ነው።
ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሆነን ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ›› ብለን በእርሱ እንመካ፤ ፈቃዱንም እንፈጽም። (ሮሜ. ፰፥፴፭‐፴፱)