ቤተ ክርስቲያን
ካለፈው የቀጠለ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁ? የዓመቱ የማጠቃለያ ፈተና እንዴት ነበር? በየትምህርት ወቅት መምህራን ሲያስተምሯችሁ የነበረውን ዕውቀት በማስተዋል ሲከታተል የነበረ፣ ያልገባውን ጠይቆ የተረዳና በደንብ ያጠና ተማሪ በጥሩ ውጤተ ከክፍል ክፍል ይሸጋገራል፤ መቼም እናንተ ጎበዝ እንደሆናችሁ ተስፋችን እሙን ነው፤ መልካም!
እንግዲህ የዘንድሮ ዓመት የትምህርት ጊዜ ምዕራፍ ተጠናቋል፤ ትምህርተ ግን አላለቀምና ከተወሰኑ የዕረፍት ጊዜያት በኋላ ስለሚቀጥል በቀጣይ ስለምትገቡበት ክፍል ከወዲሁ በቂ ግንዛቤ ለመያዝ መጣር አለባችሁ!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በምሳሌው ‹‹ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፤ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ›› በማለት እንደ ነገረን አስተዋይና ጥበበኛ መሆን ይገባል፤ (ምሳ.፫፥፲፫) ለሁሉም ጊዜ እንዳለው የጨዋታና የትምህርት ጊዜያችንን መለየት አለብን፡፡ ይህን በማስተዋል ሚዛን መዝናችሁ ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙ! በፌዝ፣ በከንቱ ነገር አንዳች ጊዜ እንዳይባክንባችሁ በመጠንቀቅ ነገ መሆን የምትፈለጉትን ለመሆን ዛሬ በርትታችሁ ተማሩ!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አባቶች ምን ይላሉ መሰላችሁ? ‹‹አለማወቅ በጨለማ እንድንኖር ያደርጋል፤ መማርና ማውቅ ግን ጨለማን አስወግዶ እውነትን እንድናይ የሚያስችለንና ብርሃንን የሚያጎናጽፈን ነው፡፡›› ታዲያ ይህን ተምረንና አውቀን በጨለማ ከመኖር ይልቅ እውነትንና መልካም ነገርን የምናይበትን እውቀት መያዝ ይጠበቅብናል፤ መልካም!
ልጆች! ባለፈው ጊዜ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትርጉም እንዲሁም የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በማን፣ መቼና የት ቦታ እንደታነጸች ተመልክተናል፤ ዛሬ ደግሞ በያዝነው ቀጠሮ መሠረት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላሉት ሦስት ክፍላት ማለትም ስለቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት፣ መቅደስ አገልግሎትና ምሥጢራዊ ትርጉም እንማማራለን፤ መልካም ቆይታ!
ልጆች! ቤተ ክርስቲያን ሲታነጽ በሦስት ዓይነት ነው፤ እነርሱም
- ሰቀላ (ሞላላ) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ካሠራው ቤተ መቅደስ፣ ንግሥት እሌኒ፣ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ካሠሩት ቤተ መቅደስ የተወሰደ አሠራር ነው፡፡ ይህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ክፍላት ያሉት ሲሆን በመጋረጃ (በምሰሶ) ይከፋፈላል፤ የሚሠራለትም ጉልላት ከአንድ በላይ ነው፤ የበሩም ቁጥር የተወሰነ አይደለም፤ ለዚህ እንደማስረጃ የሚጠቀሱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል፣ ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ….ናቸው፡፡
- ክብ (ቤተ ንጉሥ) ቅርጽ ነገሥታቱ ቤተ መንግሥታቸውን አስመስለው የሚሠሩት ሲሆን በግድግዳ የተከፋፈሉ ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት፣ መቅደስ የተሠኙ ሦስት ክፍላት አሉት፤ ሦስት የመግቢያ በሮች ሲኖሩት በሰሜን አቅጣጫ ያለው ለወንድ ምእመናን መግቢያ፣ በደቡብ አቅጣጫ ያለው ለሴት ምእመናን መግቢያ፣ በምሥራቅ አቅጣጫ ያለው ደግሞ ለካህናት መግቢያ ያገለግላል፤ የዚህ ዓይነቱ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ማስረጃ የሚሆኑን እንጦጦ ማርያም ፣ግቢ ቅዱስ ገብርኤል፣ አራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም…. ተጠቃሽ ናቸው፡፡
- ዋሻ፡-ጥንት ከርስቲያኖች በዘመነ ሰማዕታት በዋሻ ሲሸሸጉ የጀመሩት የቤተ መቅደስ ዓይነት ነው፤ የመግበቢያ በሩ አንድ ሲሆን በውስጡ የያሉ ክፍላት የሚለያዩት በመጋረጃ ነው፡፡ ከበላዩ ጉልላት የሌለው ሲሆን የሚታነጸውም ተራራ በመፈልፈል ነው፤ አንዳንድ ጊዜም ለብቻው ከአለት ድንጋይ በመፈልፈል ሊታነጽ ይችላል፤ ለዚህ አብነት ማስረጃ የሚሆኑን የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስያናት፣ አዳዲ ማርያም፣ አቡነ ሃብተመርያም ገዳም (ደብረ ሊበኖስ) … ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ውድ የእግዚአበሔር ልጆች! ቤተ ክርስቲያን በሦስት ዓይነት መልኩ እንደሚታነጽ ተመለከትን፤ በውስጡም መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከወንባቸው ክፍላት አሉ፤ እነርሱን ደግሞ በጥቂቱ እንመልከት፡- - ቅኔ ማኅሌት፡- ስያሜው ከግብሩ (ከሥራው) የተወሰደ ነው፤ ሊቃውንት መዘምራን ስብሐተ እግዚአብሔር የሚያደርሱበትና ቅኔ የሚቀኙበት ክፍል ነው፤ በዚህ ክፍል ሰሜን መሥራቅ ሰዓታት ይቆምበታል፤ በነግህ ኪዳን ይደርስበታል፤ ወንዶች ምእመናን የሚያስቀድሱበት ነው፤ በዚህ ደቡብ ምሥራቅ ንዑስ ማዕዘን በኩል ሴት ምእመናን የሚቆሙበት ነው፤ ከውጭ ወደ ውስጥ (ቤተ ክርስቲያን) ሲገባ የሚገኝ ክፍል እንደመሆኑ ሦስት መግቢያ በሮችም አሉት፡፡
ቅድስት፡- የተለየ ማለት ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑ ማዕከላዊ ክፍል ነው፤ በዚህ ክፍል ምእመናን ይቆርቡበታል፤ በሥርዓተ ተክሊል ቁርባን የሚጋቡ ምእመናን ሥርዓተ ጸሎት ይፈጸምበታል፤ በስቅለት በዓል ዕለት ሥርዓተ ጸሎት ይካሄድበታል፤ (ይፈጸምበታል) በምዕራብ በኩል ቆሞሳት፣ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፤ በሰሜን በኩለ መነኰሳት የሚቆርቡ ወንዶች ምእመናን፣ በደቡብ በኩል ደናግል መነኰሳይት፣ የቀሳውስትና የዲያቆናት ሚስቶች ያስቀድሱበታል፤ በምስራቅ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ አራት በሮች ይኖሩታል፡፡ - መቅደስ፡-የቃልኪዳኑ ታቦት ያለበትና ንዋያተ ቅዱሳት የሚገኙበት ክፍል ሲሆን ከዲቁና እስከ ጵጵስና ማዕረገ ክህነት ያላቸው አገልጋዮች ብቻ ይገቡበታል፤ በምዕራብ፣ በሰሜንና፣ በደቡብ ሦስት በሮች ይኖሩታል፤ እያንዳንዱም በር መንጦላዕት (መጋረጃ) ይኖሩታል፡፡ እንግዲህ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ይህን ተረድተን ምሥጢሩን በማስተዋል መሆን አለበት፤ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎምን ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ›› በማለት እንደመከረን በቤተ እግዚአብሔር ስንመላለስ በማስተዋልና በትሕትና መሆን አለበት፡፡ (መክ. ፭፥፩)
አምላካችን እግዚአብሔር በማስተዋል፣ በጥበብና በትሕትና እንኖር ዘንድ ያበርታን፤ አሜን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!