ቤተ ክርስቲያናችን ፳፰ ቤቶቿን አስመለሰች
ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ወጪ ካስገነባቻቸውና በደርግ ዘመነ መንግሥት በግፍ ከተወረሱባት በርካታ ቤቶቿ መካከል ፳፰ቱን ማስመለሷን የሕንጻዎችና ቤቶች አስመላሽ ኰሚቴ ሰብሳቢ አስታወቁ፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ፣ የሕንጻዎችና ቤቶች አስመላሽ ኰሚቴ ሰብሳቢ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት አስመላሽ ኰሚቴው ባደረገው ያለሰለሰ ጥረት በሦስት ክፍለ ከተሞች ማለትም በልደታ ፲፰፤ በየካ ፭ እና በቂርቆስ ፭ በድምሩ ፳፰ ቤቶች ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለባለንብረቷ ለቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው ተረጋግጧል፡፡
አስመላሽ ኰሚቴው ባደረገው የማጣራት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ በየክፍለ ከተሞች በደርግ መንግሥት እንደ ተወረሱ የቀሩ ሁለት መቶ ሰማንያ ሦስት ሕንጻዎችና ቤቶች እንደሚገኙ፤ ከእነዚህ መካከልም አንድ መቶ ሠላሳ ሰባቱ ሕጋዊ ማረጋገጫ እንደ ተገኘላቸው የጠቆሙት የኰሚቴው ሰብሳቢ በአሁኑ ሰዓት ፳፰ቱ ቤቶች መመለሳቸውን አድንቀው ቀሪዎቹ አንድ መቶ ዘጠኙ ደግሞ እስከ ነሐሴ ወር ፳፻፰ ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ተመላሽ እንደሚኾኑ ጠቁመዋል፡፡
ለወደፊቱም ኹሉም ሕንፃዎችና ቤቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ ለማድረግ አስመላሽ ኰሚቴው ተግቶ እየሠራ መኾኑን ያስገነዘቡት ሰብሳቢው የተወረሱ ሕንፃዎችንና ቤቶችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ልዩ ልዩ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ኹሉ በቤተ ክርስቲያንና በአስመላሽ ኰሚቴው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በዐሥር ሚሊዮን ዐርባ ዘጠኝ ሺሕ ብር ወጪ የተገዙ ዐሥር ዘመናዊ መኪኖች ሥራ መጀመራቸውን መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
የመኪኖቹ ሙሉ ወጪ የቤተ ክርስቲያኗ መኾኑን የጠቀሱት መጋቤ ካህናት ዐሥሩም መኪኖች የመጓጓዣ እጥረት ላለባቸው አህጉረ ስብከትና የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውን አስታውሰው መኪኖቹ በአፋጣኝ ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ኹኔታ እንዲከናወን ያደርጋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም መኪኖቹ በፍጥነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ድጋፍ ላደረጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ለወደፊቱ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ለምታከናውናቸው ተግባራትና ንብረቶቿን ለማስመለስ ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት ‹‹መላው ሕዝበ ክርስቲያን በጸሎታቸውና በዐሳባቸው ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል›› ሲሉ ለምእመናን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡