‹‹ባሕርም ሰገደችለት›› (ቅዱስ ያሬድ)

ሐምሌ ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

የእግዚአብሔር አምላክ ድንቅ ሥራ ከሚገለጽበት ተፈጥሮ መካከል አንዱ ባሕር ነው፡፡ ‹‹የውኃ ማጠራቀሚያውንም “ባሕር” ብሎ ጠራው፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ›› እንዲል፤ (ዘፍ. ፩፥፲)

ባሕር በስፍሐቱ መጠን ከማንኛውም የውኃ ሙላት ይበልጣል፤ በተለይም በዘመነ ክረምት የባሕር መሰልጠን (ሙላት) ይሆናል፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን፤ ይጸግቡ ርኁባን ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናብም በዘነበ ጊዜ ድሆች ደስ ይሰኛሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ምድር አየችው፤ አመሰገነችውም፤ ባሕርም ሰገደችለት›› በማለት እንደዘመረው በዘመነ ክረምት ባሕር ይሰለጥናል፡፡ (ድጓ ዘክረምት)

አምላካችን እግዚአብሔር ከፈጠረው ባሕር ሰዎች ብዙ ይጠቀማሉ፡፡ ባለሙያዎች በተገቢው መንገድ ውኃው ከማጠራቀሚያው ወስደው ካዘጋጁትና ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ከሆነ በኋላ በዋነኛነት ሰዎች ውኃን ለመጠጥና ለምግብ ማዘጋጃነት እንጠቀምበታለን፡፡ ይህም ለህልውናችን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም ለሰዎች መግቦት የተፈጠሩት ዕፅዋትና አዝርዕት ሁሉ የሚያብቡትና የሚያፈሩት በውኃ ነው፡፡ ውኃ ለሰው ልጅ የንጽሕና መጠበቂያ፣ አልባሳታትንና መጫሚያችን ማጽጃ እንዲሁም ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች (የቤትና የንግድ ቤቶች መሥሪያ) ይጠቅማል፡፡

በተጓዳኝም ባሕር በውስጡ የተለያዩ እንስሳት ማለት የዓሣ ዝርያዎች (ዓሣ፣ ዓሣ አንበሪ፣ሻርክ) የባሕር ውስጥ ኤሊና የሌሎች እንስሳት መኖሪያ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም አለ፥ ውኃ የሕይወት እስትንፋስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች… ታስገኝ፤ … እግዚአብሔርም ታላላቅ አንባሪዎችን፥ ውኃ ያስገኘውን ተንቀሳቃሽ ሕያው ፍጥረትን ሁሉ በየወገኑ… ፈጠረ›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳-፳፩)

ባሕር ለእንስሳቱ መኖሪያ እንደሆነ ሁሉ እኛ ሰዎች በምንኖርባት ዓለምም ይመሰላል፤ በተለይም አሁን የምንኖርባትና ችግር መከራ የበዛባትን ዓለም እንደሚመሰል በማቴዎስ ወንጌል ላይ የተገለጸውን ቃል ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፤ ‹‹እነሆም፥ የባሕሩ ማዕበል ታንኳውን እስኪደፍነው ድረስ በባሕሩ ውስጥ ታላቅ መናወጥ ሆነ፤›› ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚያን ጊዜ ተኝቶ ነበር፡፡ ደቀ መዝሙርቱም ቀሰቀሱትና ‹‹አቤቱ! እንዳንሞት አድነን አሉት፤ እርሱም፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ ምን ያስፈራችኋል? አላቸው፤ ተነሥቶም ነፋሳትንና የባሕሩን ማዕበል ገሠጸው›› እንዲል፤ ባሕር የተባለው ይህ ዓለም ነውና እኛ ሰዎችም አሁን ያለብንን ችግርና መከራን ለማለፍ በእምነት ጸንተን መጓዝ እንዳለብን በዚህ እንረዳለን፡፡ (ማቴ.፰፥፳፬-፳፮)

በባሕር ውስጥ የሚኖሩ የባሕር እንስሳትም ለሰው ልጅ ያላቸው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ዓሣ ለሰው ልጅ መግቦት ይውላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአንድ ባሕር ውስጥ የምግብ ጨው ይገኛል፡፡ (ዮሐ. ፳፩፥፭-፮)

የባሕር ውኃ ሙላት ለእርሻ ያለው ጠቀሜታም ከፍተኛ ነው፡፡ በመስኖ ሥራ የውኃ ሙላቱን ለግብርናና ለእህል፣ ለዕፅዋት፣ ለፍራፍሬ ምርት እንዲሁም ለተለያዩ አዝርዕት ምርቶች ይጠቅማል፡፡ ገበሬው አርሶ ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ የሚረዳው ዋነኛ ግብአት የውኃ ሙላት ነው፡፡

በኦሪት ዘዳግም ‹‹የባሕሩም ሀብት፥ በባሕር ዳር የሚኖሩ ሰዎችም ገንዘብ ይመግብሃል›› ተብሎ እንደተጻፈ ባሕር የተለያዩ የሀብት ምንጭች ነው፡፡ አንድ ዓሣ አስጋሪ በባሕር ውስጥ ዓሣዎችን ይዞ በመሸጥ ሊተዳደርም ሆነ ሀብት ሊያካብት ይችላል፤ የሰዎች የዓሣ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ የዓሣ ሽያጭ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከባሕር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ማእድናት እና የከበሩ ድንጋዮች ለተለያዩ የቤት መሥሪያና ማስዋብያ እንዲሁም ለጌጣ ጌጥ መሥሪያ ይውላሉ፡፡ እንደሚታወቀው የቤት ግንባታ ዓይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረና ተፈላጊ በመሆኑ ሰዎች በተለይም ባለ ጸጋዎች በዘመናዊ ምርቶች ቤታቸውን ለማስዋብ ተፈላጊውን ዋጋ ይከፍላሉ፤ በዚህም የባሕር ማእድናት ዋጋ ጨምሯል፤ ስለዚህም ባሕር የነጋዴዎች የሀብት ምንጭ መሆኑን እንረዳለን፡፡ (ዘዳ. ፴፫፥፲፱)

በመሆኑም እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን በምክንያት ፈጥሯልና እኛ ሰዎች ይህን ተረድተንና የእርሱን ድንቅ ሥራ አክብረን በተገቢው መንገድ ልንገለገል ይገባል፡፡ ከላይ እንደተመለከትነውም ባሕር ለሰው ልጅ ብዙ ጥቅም አለው፤ በውስጡ ያሉትንም የተፈጥሮ ሀብት በተገቢው መንገድ ለመጠቀም የተፈጠሩበትን ምክንያት ማወቅ ያስፈልጋል፤ ስለዚህም የባሕርን ተፈጥሮና ሌሎች የባሕር ሀብቶችን ባለ መጉዳትና ባለ መበዝበዝ በሚገባ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር